ምዕራፍ 74 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የሆሣዕና እሑድ
ኢየሱስ በቢታንያ እንዳለ የሚናገረው ወሬ ተሰማ፤ ብዙም ሳይቈይ መንደሩ እርሱን ለማየት በሚጓጉ ሰዎች ተጨናነቀ። ከእነርሱ ብዙዎቹ ለፋሲካ በዓል ከገጠር ወደ ኢየሩሳሌም የወጡ ሰዎች ነበሩ፤ አብዛኞቹም ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ተስፋ የተሰጠበት የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ ለማመን የተዘጋጁ ነበሩ። አንዳንዶቹ ወደ ቢታንያ የመጡት ኢየሱስን ለማየት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ከሞት ወደ ሕይወት ያስነሣውን ሰው አልዓዛርን ደግሞ ለማየት ነበር። ኢየሱስን ለመግደል አስቀድመው የወሰኑትና እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ለይሁዳ የከፈሉት አለቆች እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦
«እነዚህ ሰዎች የናዝሬቱን ኢየሱስን ንጉሥ እንዳያደርጉት ልንከለክል ብንሻ ኢየሱስን መግደል ብቻ አይበቃም፤ በእርሱ ምክንያት ብዙዎች ኢየሱስን ይከተላሉና አስቀድመን አልዓዛርን መግደል አለብን።»
በስምዖን ቤት ከተደረገው እራት በኋላ ባለው ጠዋት ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ወሰነ። ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦
«ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለችው ወደሚቀጥለው መንደር ሂዱ፤ በዳርዋም አህያ ታስራ፥ ከእርስዋም ጋር ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ‹ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?› ቢላችሁ፥ ‹ለጌታ ያስፈልጉታል፤ ወዲያውም ይመልሳቸዋል› በሉት፤ አህያዪቱንና ውርንጫውንም እንድትወስዱ ይፈቅድላችኋል።»
ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ወደ መንደሩ ሄዱ፤ ኢየሱስ እንደ ተናገረውም በአንድ ቤት ፊት ለፊት በመንገድ ላይ አህያና ውርንጫ ታስረው አገኙ። እየፈቱአቸውም ሳሉ በአጠገቡ ቆሞ የነበረው ባለቤታቸው እንዲህ አለ፦
«አህያዪቱን የምትፈቱ ምን እያደረጋችሁ ነው?»
ደቀ መዛሙርቱም፦ «ለጌታ ያስፈልገዋል» ብለው መለሱ፤ ሰውዬውም ይህን በሰማ ጊዜ አህያዪቱንና ውርንጫውን እንዲወስዱ ፈቀደላቸው። በቢታንያ ወዳለው ወደ ኢየሱስ አመጡአቸው፤ ለኢየሱስ መቀመጫ እንዲሆን በውርንጫው ላይ ልብሳቸውን ጣሉበት፤ እርሱም ከዚህ በፊት ማንም ባልተቀመጠበት ውርንጫ ላይ ተቀመጠ። ሕዝቡም ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ባዩ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሄዱ፤ አንዳንዶቹ ቀድመው ሌሎቹም ተከትለው ይሄዱ ነበር። በፊት የነበሩት በኢየሱስ ፊት ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ከሜዳ ቅጠሎችን በምድር ላይ ጣሉ፤ ብዙዎችም ከመንገድ ዳር ካሉት ዛፎች የተቈረጡትን የዘንባባ ዝንጣፊዎች ያውለበልቡ ነበር።
በቢታንያና በኢየሩሳሌም መካከል ወዳለው ወደ ደብረ ዘይት ራስ ገና ሳይደርሱ ኢየሱስን ለማየት ከከተማው የወጡ ሌሎች ብዙ ሰዎች ተገናኙአቸው። ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት እንዲህ እያሉ ጮኹ፦
«ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ ለንጉሡ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት! ሆሣዕና በአርያም!»
ይህ ሁሉ ሕዝብ አሁን በመጨረሻ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደምትቆምና ኢየሱስም ክርስቶስና ንጉሥ እንደሚሆን አምኖ ነበርና። በሕዝቡ መካከል ግን የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑ አንዳንድ ፈሪሳውያን ነበሩ፤ እነርሱም ሕዝቡ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን እያውለበለበ ኢየሱስን እንደ ንጉሥ በእልልታ ሲቀበለው ባዩ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። እነዚህም ሰዎች ኢየሱስ በውርንጫው ላይ ሆኖ ሲሄድ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦
«መምህር ሆይ፥ ተከታዮችህ ይህን ጩኸት እንዲያቆሙ ንገራቸው!»
ኢየሱስም፦ «እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ!» ብሎ መለሰ።
ብዙም ሳይቈዩ ወደ ደብረ ዘይት ራስ ደረሱ፤ በዚያን ጊዜም ቤተ መቅደሱና የኢየሩሳሌም ከተማ በፊታቸው ታዩ።
ኢየሱስም ከተማዪቱን ሲመለከት እንባ በዓይኖቹ ሞላ፤ እንዲህም አለ፦
«ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም ሆይ! አሁንም ቢሆን ገና ጊዜ ሳለ ለሰላምሽ የሚሆነውን ብታውቂ ኖሮ! አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል! ጠላቶችሽ ቅጥርና ምሽግ የሚሠሩብሽ፥ በየበኵሉም የሚከቡሽ፥ አንቺንና ልጆችሽንም ወደ ትቢያ የሚጥሉሽ ጊዜ ይመጣል። በአንቺም ውስጥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ ይህም ሁሉ ጌታ በጐበኘሽ ጊዜ ስላላስተዋልሽ ነው።»
ኢየሱስም ከደብረ ዘይት ወረደ፥ የቄድሮንንም ወንዝ ሸለቆ ተሻገረ። በቤተ መቅደሱ በር ከውርንጫው ጀርባ ወረደ፤ ከአህያዪቱም ጋር ወደ ባለቤቱ መለሰው። ወደ ከተማዪቱና ወደ ቤተ መቅደሱ በገባ ጊዜ ታላቅ ሁከት ሆነ፤ ሕዝቡ በየስፍራው እርሱን ለመቀበል ይጐርፍ ነበር።
«ይህ ማን ነው?» አሉ፤ ሕዝቡም፦ «ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው!» ብለው መለሱ።
ፈሪሳውያንም እርስ በርሳቸው፦ «ምንም ልናደርግ አንችልም! እነሆ፥ ዓለሙ ሁሉ ኢየሱስን ተከትሎ ሄዶአል!» ተባባሉ።
የኢየሱስ ወዳጆችም ጠላቶችም ሁሉ ከተማዪቱን ተቈጣጥሮ እንደ ንጉሥ ይሠራል ብለው ይጠብቁ ነበር። ኢየሱስ ግን ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በዙሪያው ተመላለሰ እንጂ ሌላ አላደረገም። በዚያን ጊዜ መሸ፤ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቢታንያ ተመለሰ።
ከዚያ ጊዜ ዐርባ ዓመት በኋላ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ላይ ይደርሳሉ ብሎ የተናገራቸው አስፈሪ ነገሮች በእርግጥ ተፈጸሙ። አይሁድ በሮማውያን ላይ ተነሥተው ጦርነት ገጠሙአቸው። ብርቱ የሮም ሠራዊት መጥቶ በምድሩ ሁሉ ላይ ተሰራጨ፤ በየስፍራውም ጥፋትንና ሞትን አመጣ። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከበቡ፤ ማንም እንዳይወጣም እንዳይገባም በዙሪያዋ ጠንካራ ቅጥር ሠሩ። ሕዝቡም በራብ እስኪደክሙና ከዚያ ወዲያ መዋጋት እስኪያቅታቸው ድረስ ተስፋ በቈረጠ ብርታት ተዋጉ። በመጨረሻም ሮማውያን ሰብረው ወደ ቤተ መቅደሱ ገቡ፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሉ። ቤተ መቅደሱም ከተማዪቱም ሁሉ ፈጽመው ጠፉ፤ ቍጥር የሌላቸው ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ ሌሎች ብዙ ሺዎችም ለባርነት ተሸጡ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፥ ኢየሱስ ከተወለደ ከሰባ ዓመት፥ በመስቀል ላይ ከሞተም ከዐርባ ዓመት በኋላ፥ አይሁድ የራሳቸው የሆነ ምድርም ከተማም አልነበራቸውም።