ምዕራፍ 72 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
በኢያሪኮ በባለ ጠጋው ቤት
ነገር ግን በኢያሪኮ ኢየሱስን ለማግኘት የጓጓው ሰው ዕውሩ በርጤሜዎስ ብቻ አልነበረም። በዚያች ከተማ በዚያ አገር ክፍል ባሉት ቀራጮች ሁሉ ላይ አለቃ የነበረ ዘኬዎስ የሚባል እጅግ ባለ ጠጋ ሰው ይኖር ነበር። ኢየሱስ ከሌሎች አይሁድ ተለይቶ ለቀራጮች ወዳጅ እንደ ሆነ ሰምቶ ነበርና ሊያየው እጅግ ተመኘ። ዘኬዎስ ግን ቁመቱ አጭር ነበረ፤ በሕዝቡም መካከል ኢየሱስን የሚያይበት ምንም ዕድል አልነበረውም፤ ስለዚህ ወደ ፊት ሮጦ በመንገዱ ዳር በቆመ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ፤ ከቅርንጫፎቹም መካከል ሆኖ የሚያልፈውን ሕዝብ ወደ ታች ቍልቍል ሊያይ ቻለ።
ኢየሱስም ከዛፉ ትይዩ በደረሰ ጊዜ ቆመ፤ አሻቅቦም ዘኬዎስን አየና እንዲህ አለው፦
«ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ!»
ታላቁ መምህር በኢያሪኮ ካሉት ቤቶች ሁሉ መርጦ በእርሱ ቤት ለመቆየት በመፈለጉ ተገረመ፤ ደስም አለው። ወርዶም ከኢየሱስ ጋር ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡ ሁሉ ግን እንዲህ እያሉ ማጕረምረም ጀመሩ፦
«ኃጢአተኛ ወደ ሆነ ሰው ቤት ሊጠይቅ ገባ!»
ብዙዎቹ ቀራጮች ክፉዎች ስለ ነበሩና ሕዝቡን ይዘርፉ ስለ ነበሩ ሁሉም ክፉዎች እንደ ሆኑ ቈጥረው ነበርና።
ዘኬዎስም ምን እንደ ተሰማቸውና ምን እንደሚሉ ዐወቀ፤ ስለዚህ ወደ ፊት ወጥቶ በኢየሱስ ፊት ቆመና እንዲህ አለ፦
«መምህር ሆይ፥ ስማኝ! ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ድሆችን ለመርዳት እሰጣለሁ፤ ማንንም ዘርፌ ወይም አታልዬ እንደ ሆነ ካጣው አራት እጥፍ እመልስለታለሁ!»
ኢየሱስም «ይህ ዘኬዎስ ደግሞ እውነተኛ የአባታችን የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ በዚህ ቤት አንድ ሰው ከኃጢአቱ ዳነ» አለ። «የሰው ልጅ የጠፉትን ሊፈልግና ሊያድናቸው መጥቷልና።»
ሕዝቡም ሲሰሙ ሳሉ ቀጥሎ ምሳሌ ነገራቸው፤ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ የእግዚአብሔር መንግሥት ወዲያው እንድትቋቋም ይጠብቁ እንደ ነበሩ ዐውቆ ነበርና። ይህም «የምናኑ ምሳሌ» ነው።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «አንድ መኰንን ንጉሥ ሆኖ ተመልሶ የገዛ አገሩን ሊገዛ ወደ ሩቅ ከተማ ሊሄድ ነበረ። ከመሄዱም በፊት ከባሪያዎቹ ዐሥሩን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው አምስት መቶ ዶላር ሰጥቶ ‹እስክመለስ ድረስ በዚህ ነግዱ› አላቸው። ከዚያም ሄደ።»
«የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና በኋላው ወደዚያች ሩቅ ከተማ መልእክተኞችን ልከው ‹ይህ ሰው በላያችን ንጉሥ እንዲሆን አንወድም› አሉ።»
«ይሁን እንጂ መኰንኑ ንጉሥ ሆኖ አገሩን ሊገዛ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚያም እያንዳንዳቸው ገዝተውና ሸጠው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ ገንዘቡን የሰጣቸውን ባሪያዎች አስጠራ። የመጀመሪያውም ባሪያ መጥቶ እንዲህ አለ፦»
«‹ጌታዬ ሆይ፥ የሰጠኸኝ አምስት መቶ ዶላር አምስት ሺህ ዶላር አተረፈ።›»
«ንጉሡም ‹መልካም አደረግህ፥ አንተ በጎ ባሪያ፤ በጥቂቱ ይህን ያህል ጠቢብና የታመንህ ስለ ሆንህ በመንግሥቴ ባሉ በዐሥር ከተሞች ላይ ገዥ አደርግሃለሁ› አለው።»
«ከዚያም ሌላው ባሪያ መጥቶ ‹ጌታዬ ሆይ፥ አምስት መቶ ዶላርህ የሰጠኸኝን አምስት እጥፍ አተረፈ። እነሆ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ዶላር› አለ።»
«ንጉሡም ‹መልካም ነው፤ አንተም በአምስት ከተሞች ላይ ገዥ ትሆናለህ› ብሎ መለሰለት።»
«ቀጥሎም ከባሪያዎቹ አንዱ መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‹ጌታዬ ሆይ፥ እነሆ አምስት መቶ ዶላርህ፥ ልክ እንደ ሰጠኸኝ ነው። በጨርቅ ጠቅልዬ በደኅና ጠብቄልሃለሁ። አንተ እንዲህ ያለ ጨካኝና ራስ ወዳድ ሰው ስለ ሆንህ ፈርቼሃለሁና። ያላኖርኸውን ትወስዳለህ፤ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ።›»
«ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ ‹አንተ የማትረባ ባሪያ! አፍህ በተናገረው ቃል እፈርድብሃለሁ። ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ዐወቅህን? ይህን ካወቅህ ታዲያ ገንዘቤን ለምን በባንክ አላስቀመጥኸውም? ያን ጊዜ ወደ ቤት በተመለስሁ ጊዜ ወለዱን፥ ማለትም በማበደር የተገኘውን ትርፍ፥ እወስድ ነበር።›»
«ከዚያም በዚያ ቆመው የነበሩትን ‹አምስቱን መቶ ዶላር ውሰዱበትና አምስት ሺህ ዶላር ላለው ስጡት!› አላቸው።»
«እነርሱም ‹ጌታችን ሆይ፥ እርሱ እኮ አምስት ሺህ ዶላር አለው! ለምን ለእርሱ ትሰጠዋለህ?› አሉት።»
«ንጉሡም ‹ሊሰጠው የሚገባበት ምክንያት ይኸው ነው› አለ። ‹እላችኋለሁ፥ ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው ጥቂቱ ስንኳ ይወሰድበታል።›»
«ንጉሡም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ ‹አሁንም እነዚህን ጠላቶቼን፥ ንጉሥ እንድሆናቸው እንደማይወዱ የላኩብኝን እነዚያን ሰዎች ያዙአቸው፤ በሰንሰለትም አስራችሁ ወደዚህ አምጡአቸው። በፊቴም ይገደሉ!›»
ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው የተራራ መንገድ ወደ ላይ ወጣ።