የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በበሩ አጠገብ የነበረው ዕውር

ምዕራፍ 71 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

በበሩ አጠገብ የነበረው ዕውር

ኢየሱስ በዮርዳኖስ ምሥራቅ በኩል ባለችው በፔሪያ አገር የስብከቱን ሥራ አሁን ጨረሰ። በኢየሩሳሌም ወደሚከበረው ወደ ፋሲካ በዓል ይወጡ ከነበሩ ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ሌላ ቤተ ራባ ወደምትባል ስፍራ፥ ማለትም «መሻገሪያው» ወደሚባለው፥ ወደ ወንዙ መጣ። ይህም ስም የተሰጣት በገሊላ ባሕር አጠገብ እንዳለችው እንደ ቤተ ራባ ወንዙ እጅግ ሰፊ ቢሆንም ጥልቀቱ ጥቂት ስለ ሆነ ሰዎች በእግራቸው ሊሻገሩት ይችሉ ስለ ነበረ ነው። ይህቺ ቤተ ራባ ከአርባ ዓመት ገደማ በፊት በታላቁ ሄሮድስ ተሠርታ ካጌጠችው ከኢያሪኮ ከተማ ትይዩ ነበረች።

ኢየሱስ በወንዙ አጠገብ ከመቆሙ ከሺህ ዓመት በላይ አስቀድሞ፥ እግዚአብሔር ውኃውን በከለከለ ጊዜ እስራኤላውያን ወደ ምድሪቱ ለመግባት በእግራቸው ተሻግረውት ነበር። ኢየሱስ ቢወድ በውኃው ላይ ሊራመድ በቻለ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ለሌሎች ተአምር ቢያደርግም ለራሱ ፈጽሞ ተአምር አላደረገም። በዚያን ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ ልብሳቸውን በራሳቸው ላይ ይዘው ወንዙን በእግር ተሻገሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ በመሻገሪያ ጀልባ ተሻገሩ። ኢየሱስ ወንዙን በየትኛው መንገድ እንደ ተሻገረ አልተነገረንም።

ከዮርዳኖስ ወንዝ በምዕራብ በኩል ስድስት ማይል ርቃ ኢያሪኮ ነበረች፤ ኢየሱስም ብዙ ሕዝብ ከብቦት ወደ እርስዋ መጣ። ወደ ኢያሪኮ በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር በበሩ አጠገብ ተቀምጦ ከሚያልፉት ሰዎች ጥቂት ሳንቲም ይለምን ነበር። የዚህም ዕውር ስም በርጤሜዎስ ነበረ፤ ትርጓሜውም «የጤሜዎስ ልጅ» ማለት ነው። የብዙ ሰዎችን የእግር ኮቴና ድምፅ በሰማ ጊዜ ይህ ሁሉ ሕዝብ ለምን እንደሚመጣ ጠየቀ። እነርሱም እንዲህ አሉት፦

«የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል።»

በርጤሜዎስ ስለ ኢየሱስና ብዙ ዕውሮችንና አንካሶችን ለምጻሞችንም ስለ መፈወሱ ስለ መልካም ሥራው ሰምቶ ነበር። ኢየሱስ በእርሱ በኩል አልፎ ቢፈውሰው ብሎ ብዙ ጊዜ ተመኝቶ ነበር። አሁንም ኢየሱስ በእውነት እየመጣ እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦

«የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ! የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ!»

ከፊት የነበሩት ሰዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን ይህ የሕይወቱ ዕድል እንደ ሆነ ተሰማውና «የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ!» እያለ መጮኹን ቀጠለ።

ኢየሱስም ቆመና በአጠገቡ ያሉትን «ሂዱ፥ ይህን ሰው ወደ እኔ አምጡት» አላቸው።

እነርሱም በርጤሜዎስን «አይዞህ፤ ተነሥተህ ወደ ኢየሱስ ሂድ፤ ይጠራሃልና!» አሉት።

በርጤሜዎስ ወደ ኢየሱስ ለመድረስ እጅግ ስለ ቸኰለ ብድግ ብሎ ተነሣ፤ መደረቢያውንም ወርውሮ በመሬት ላይ ተወው፤ እነርሱም ወደ ጌታ መሩት። በቀረበም ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦

«ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?»

እርሱም «ጌታ ሆይ፥ ዳግመኛ ማየት እንድችል አድርገኝ!» ብሎ መለሰ።

ኢየሱስም «እይ፤ እምነትህ አድኖሃል» አለው።

ወዲያውም ዓይኖቹ በሩ፤ እግዚአብሔርንም በታላቅ ድምፅ እያመሰገነ ኢየሱስን ከሚከተሉት ሕዝብ ጋር ተቀላቀለ። ይህንም ድንቅ ሥራ ያዩ ሁሉ ደግሞ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።


ቀዳሚ ቀጣይ