ምዕራፍ 70 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
በወይኑ አትክልት የሠሩ ሠራተኞች
ኢየሱስ «ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ፤ በዚህ ዓለም ዝቅተኞች የሆኑ አንዳንዶችም በእግዚአብሔር መንግሥት ከፍተኞች ይሆናሉ» ሲል ምን ማለቱ እንደ ሆነ በምሳሌ አስረዳ። ይህም ምሳሌ «በወይኑ አትክልት የሚሠሩ ሠራተኞች» የሚባለው ነው።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «የወይን አትክልት ያለው አንድ ሰው ነበረ። በወይን አትክልቱ የሚሠሩለት ሰዎች አስፈለጉት፤ አንድ ቀንም ማልዶ በጠዋት ሊቀጥራቸው ወጣ። አንዳንድ ሰዎችም አግኝተውት ለአንድ ቀን ሥራ ዐሥራ አምስት ሳንቲም ሊቀበሉ ተስማሙ፤ እርሱም ወደ ወይን አትክልቱ ላካቸው። በሦስት ሰዓት ገደማ በገበያ ስፍራ ሲያልፍ ሌሎች ሰዎች ሥራ እየጠበቁ ቆመው አየና እንዲህ አላቸው፦»
«‹እናንተም ወደ ወይን አትክልቴ ሄዳችሁ ሥሩ፤ የሚገባውንም ሁሉ እከፍላችኋለሁ።›»
«ቀትር ላይ ደግሞ ወጣ፤ ሥራ የሚፈልጉ ሰዎችንም አገኘና ‹የሚገባውን ደመወዝ እከፍላችኋለሁ› ብሎ እነርሱንም ወደ ወይን አትክልቱ ላካቸው። ዘጠኝ ሰዓት ላይም እንደ ገና ሌሎችን አግኝቶ ያንኑ ተስፋ ሰጥቶ እነርሱንም ላካቸው። ቀኑ ሊያልቅ በተቃረበ ጊዜ በአሥራ አንድ ሰዓት ወደ ገበያው ስፍራ ሄደ፤ በዚያም ቆመው የነበሩ ሰዎችን አገኘ። እነዚህንም ሰዎች ‹ምንም ሳትሠሩ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ?› አላቸው። እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፦»
«‹መሥራትማ ደስ ባለን ነበር፤ ነገር ግን የሚቀጥረን ሰው አጣን።›»
«እርሱም ‹እናንተም ደግሞ ወደ ወይን አትክልቴ ሂዱ፤ የሚገባውንም እከፍላችኋለሁ› አላቸው።»
«በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን እንዲህ አለው፦ ‹አሁን ሠራተኞቹን ሰብስበህ ደመወዛቸውን ክፈላቸው። በመጨረሻ ለሥራ ከመጡት ጀምር፤ ቀጥሎም በዘጠኝ ሰዓት ወደ ወይን አትክልቱ ለገቡት ክፈል፤ እንዲህ እያልህ ሂደህ ቀድመው ለሥራ በወጡት ጨርስ።›»
«ስለዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩትና አንድ ሰዓት ብቻ የሠሩት በመጀመሪያ ቀረቡ፤ ለእያንዳንዳቸውም የሙሉ ቀን ሥራ ደመወዝ ዐሥራ አምስት ሳንቲም ተከፈላቸው። ፊተኞቹም በመጡ ጊዜ ብዙ ሰዓት ስለ ሠሩ አብዝተው የሚቀበሉ መሰላቸው፤ ነገር ግን እያንዳንዳቸው እንደ ተስማሙት ዐሥራ አምስት ሳንቲማቸውን ተቀበሉ። እነዚህም ሰዎች በወይኑ አትክልት ጌታ ላይ አጕረመረሙ።»
«‹ቀኑ ሊያልቅ ሲል በመጨረሻ የመጡት እነዚያ ሰዎች፥ ከባዱን ሥራና የቀኑን ሐሩር ከተሸከምነው ከእኛ ጋር እኩል ተደረጉ› አሉ። ‹ይህ ትክክል አይደለም!›»
«ጌታውም ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‹ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም። በቀን ዐሥራ አምስት ሳንቲም ልትሠራ ከእኔ ጋር አልተስማማህምን? ደመወዝህን ውሰድና ሂድ። ለዚህ ለኋለኛው ሰው እንደ አንተ ልሰጠው ወድጃለሁ። በገዛ ገንዘቤ የወደድሁትን ላደርግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ቸር ስለ ሆንሁ ትቀናለህን?›»
ኢየሱስም «እንዲሁ ፊተኞች የሚሆኑ ኋለኞች አሉ፤ ኋለኞች የሚሆኑ ፊተኞችም አሉ» አለ።
ይህ ምሳሌ እግዚአብሔር ዋጋውን የሚሰጥበት መንገድ ከሰዎች መንገድ እንዴት እንደሚለይ ያሳያል። ሰዎች የሚከፍሉት ለተሠራው ሥራ ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መሥራት ቢችሉም ባይችሉም ለእርሱ ለመሥራት ፈቃደኞች ለሆኑት ዋጋቸውን ይሰጣል፤ ሰዎች ሥራውን ሲያዩ እግዚአብሔር ልብን ያያልና።
ኢየሱስ ቀን በቀን ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ነበር፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱና ይከተሉት የነበረው ሕዝብ ሁሉ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ እንደሚነግሥ አጥብቀው ይጠብቁ ነበር። እርሱ በዚያ ሊሞት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚወጣ ከዚህ በፊት ከአንድ ጊዜ በላይ ነግሯቸው ነበር፤ ነገር ግን አሳባቸው በዙፋንና በመንግሥት በዓለማዊም ሥልጣን ላይ እጅግ ተተክሎ ስለ ነበረ ቃሉን ሊያስተውሉ አልቻሉም።
አሁንም ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ከሕዝቡ ለይቶ ወደ እርሱ ጠራቸው።
እንዲህም አለ፦ «ስሙ! እነሆ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ በዚያም ስለ ሰው ልጅ በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል። ለጠላቶቹ ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ለሕግ መምህራን ይሰጣል፤ እነርሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ እንዲዘብቱበትና እንዲገርፉት በመስቀልም ላይ ተቸንክሮ እንዲሞት ለሮማውያን አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል።»
ደቀ መዛሙርቱ ግን የዚህ ቃል ትርጕም አልገባቸውም። ዙፋኑን ይዞ ሊገዛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚወጣ እንደ ቀድሞው እርግጠኞች ነበሩ፤ በመንግሥቱ ስላሉት ታላላቅ ሹመቶችና ማን እንደሚይዛቸው እንኳ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረቡ ሳሉ፥ ገና በፔሪያ አገር ሳሉ፥ አንዲት ሴት ከሁለት ልጆችዋ ጋር ወደ ኢየሱስ መጣች። የዚህች ሴት ስም ሰሎሜ ነበረ፤ እርስዋም የዘብዴዎስ ሚስትና ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዋነኞቹ የሆኑት የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ነበረች። በኢየሱስ ፊት እስከ ምድር ድረስ ሰግዳ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።
ኢየሱስም «ምን ትፈልጊያለሽ?» አላት።
ሰሎሜም «እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ በመንግሥትህ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ እንዲቀመጡ ቃል ግባልኝ» አለችው።
ኢየሱስም መልሶ «የምትለምኑትን አታውቁም» አለ። «እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁን? ወደ እኔ የሚመጣውንስ ያንኑ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?»
ሁለቱም ሰዎች «አዎን፥ እንችላለን!» አሉ።
ኢየሱስም «ጽዋዬን በእርግጥ ትጠጣላችሁ፤ በጥምቀቴም ትጠመቃላችሁ» አለ። «ነገር ግን በቀኜና በግራዬ ማን እንደሚቀመጥ መናገር የእኔ አይደለም። እነዚያ ስፍራዎች አባቴ ለመረጣቸው ይሰጣሉ።»
ኢየሱስ በጽዋውና በጥምቀቱ መከራውንና ሞቱን ማለቱ ነበር፤ ያዕቆብና ዮሐንስ ግን ይህን አላወቁም። ሌሎቹ ዐሥሩ ደቀ መዛሙርትም ይህን በሰሙ ጊዜ ሁለቱ ወንድማማች ከእነርሱ ቀድመው ለመገኘት በመሞከራቸው እጅግ ተቈጡአቸው። ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦
«በዚህ ዓለም አሕዛብ ዘንድ ገዦቻቸው እንዲሠለጥኑባቸው፥ ታላላቆቻቸውም ሕዝቡን እንዲያስገዙ ታውቃላችሁ። በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ መሆን የለበትም። ከእናንተ ማንም ታላቅ ሊሆን የሚወድ ለሌሎቹ አገልጋይ ይሁን፤ ፊተኛ ሊሆን የሚወድም እንደ ባሪያ ይሁን። የሰው ልጅ ሊያገለግል ብዙዎችንም ያድን ዘንድ ሕይወቱን አሳልፎ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣምና።»