የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ሕፃናቱና ባለ ጠጋው ጐበዝ

ምዕራፍ 69 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ሕፃናቱና ባለ ጠጋው ጐበዝ

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ገና በፔሪያ ምድር በማለፍ ላይ ሳለ፥ በአንድ ስፍራ አባቶችና እናቶች እጁን በራሳቸው ላይ እንዲጭንና እንዲባርካቸው እየለመኑ ሕፃናቶቻቸውን ወደ እርሱ አመጡ። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲያደርጉ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም።

«እነዚህን ሕፃናት ውሰዱ!» አሉ። «ጌታ እነርሱን ለማየት በሚበልጡ ነገሮች እጅግ ተይዞአል!»

ኢየሱስ ግን ሰማቸው፥ ተቈጣም፤ በወላጆቹና በልጆቻቸው ላይ ሳይሆን በደቀ መዛሙርቱ ላይ ነበር።

እንዲህም አለ፦ «ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ፤ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ሕፃን ለሆኑት ብቻ ትመጣለችና። እውነት እላችኋለሁ፥ ራሱን እንደ ሕፃን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማይሰጥ ሁሉ ከቶ ወደ መንግሥቱ አይገባም።»

ከዚያም ሕፃናቱን አቅፎ እጁን በላያቸው ጫነ፥ ባረካቸውም። ከዚያ በኋላ ከዚያ ስፍራ ሄደ።

ብዙም ሳይቈይ በከተማው ምኵራብ ከመሪዎቹ አንዱ የሆነ አንድ ጐበዝ እየሮጠ መጥቶ በኢየሱስ ፊት ሰገደ። ጐበዙም፦ «ቸር መምህር ሆይ፥ እድንና የዘላለም ሕይወት አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ? ንገረኝ» አለው።

ኢየሱስም መለሰ፦ «‹ቸር› ስለ ምን ትለኛለህ? በእውነት ቸር የሆነ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው። ትድን ዘንድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ ብቻ ይበቃሃል። ትእዛዛቱ ምን እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ ጠብቃቸው።»

ጐበዙም፦ «የትኞቹን ትእዛዛት ማለትህ ነው?» ብሎ ጠየቀ። የእግዚአብሔርን ሕግ ያስተምሩ እንደ ነበሩት እንደ ብዙዎቹ ጻፎች ኢየሱስም የራሱ የሆኑ ልዩ ሥርዓቶች የሰጠ መስሎት ነበር።

ኢየሱስም፦ «የእግዚአብሔርን ዐሥርቱን ትእዛዛት ማለቴ ነው፤ ለምሳሌ ‹አትስረቅ፤ አትግደል፤ በሐሰት አትመስክር፤ አባትህንና እናትህን አክብር› የሚሉትንና የመሳሰሉትን» አለው።

ጐበዙም፦ «መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ። ሌላ ምን ይጐድለኛል?» አለ።

ኢየሱስ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዲህ የሚጓጓውን ይህን ጐበዝ ሲመለከት ወደደው፥ ከደቀ መዛሙርቱም መካከል እንዲሆን በተለየ ሁኔታ ተመኘ።

ጐበዙንም፦ «ፍጹም ልትሆን በእውነት ብትወድ አንድ ነገር ይጐድልሃል። ያለህን ሁሉ ሽጥ፥ ገንዘቡንም ሁሉ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ፥ ከደቀ መዛሙርቴም አንዱ ሁን» አለው።

ጐበዙ ያን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተስፋ ቈረጠ፤ ኢየሱስ የለመነውን ለማድረግ ሳይፈቅድ ዘወር ብሎ ሄደ፤ እጅግ ባለ ጠጋ ነበረና፥ ገንዘቡንም ይወድ ነበር። ከእነርሱ ከተለየ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘወር አለ፦

ኢየሱስም፦ «ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው!» አለ።

ደቀ መዛሙርቱ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደነቁ፤ አይሁድ ሁሉ ሀብት ማግኘት የእግዚአብሔር ልዩ ሞገስ ምልክት ነው ብለው ያስቡ ነበርና። ለእነዚህ ቃሎች እንዴት እንደሚመልሱ ሳያውቁ ዝም ብለው ቆመው ሳሉ ኢየሱስ ደግሞ እንዲህ አለ፦

«ልጆች ሆይ፥ በሀብታቸው ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው! ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል!»

በዚህም ተገረሙና፦ «እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል?» አሉ።

ኢየሱስም፦ «በሰው ዘንድ የማይቻለው በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል» ብሎ መለሰ።

ስምዖን ጴጥሮስም፦ «እኛ ግን ሁሉን ትተን ተከተልንህ። ስለዚህ ሁሉ በመንግሥቱ ምን እናገኛለን?» አለ።

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ እንደ ነበሩት ሕዝብ ሁሉ፥ እዚያ መንግሥቱን እንደሚያቆምና ለደቀ መዛሙርቱም ብዙ ዋጋ እንደሚሰጣቸው ያስብ ነበር።

ኢየሱስም መለሰ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ የተከተላችሁኝ እናንተ፥ በአዲሱ መንግሥት የሰው ልጅ በዙፋኑ በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደቀ መዛሙርቴ ዐሥራ ሁለቱ ሰዎች በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እየገዛችሁ በዐሥራ ሁለት ዙፋኖች ትቀመጣላችሁ። ስለ እኔና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ ቤትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን የተወ ሁሉ በዚህ ሕይወት ካጣው መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወትን ያገኛል። ነገር ግን በዚህ ዓለም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች በመንግሥቱ ኋለኞች ይሆናሉ፤ እዚህ የተዋረዱ አንዳንዶችም በዚያ ከሁሉ የሚበልጡ ይሆናሉ።»


ቀዳሚ ቀጣይ