የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ስለ ጸሎት የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች

ምዕራፍ 68 · 1 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

ስለ ጸሎት የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሳይታክቱ ዘወትር ሊጸልዩ እንጂ ተስፋ ሊቈርጡ እንደማይገባቸው ለማሳየት አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ይህ ምሳሌ «የዓመፀኛው ዳኛ ምሳሌ» ይባላል።

እንዲህ አለ፦ «በአንዲት ከተማ በፍርዱ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የማይጥር፥ ይልቁንም ብዙ ጊዜ ዓመፀኛና ክፉ የሆነ አንድ ዳኛ ነበረ፤ እግዚአብሔርን አይፈራም፥ ሰዎችም ስለ እርሱ የሚሉትን ከቶ ግድ አይለውም ነበርና። በዚያችም ከተማ ወደዚህ ዳኛ ብዙ ጊዜ እየመጣች ደጋግማ፦ ‹የበደለኝን ሰው ፍረድብኝ፤ መብቴን አስከብርልኝ!› እያለች የምትጮኽ አንዲት መበለት ነበረች።»

«ዳኛው ለጥቂት ጊዜ ምንም አልሰማትም፤ ትክክልና ስሕተት ለእርሱ አንድ ነበሩና። ከዚያ በኋላ ግን ዳኛው በልቡ እንዲህ አለ፦

‹ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ግድ ባይለኝ፥ ይህች መበለት እጅግ ስለምታስቸግረኝና ዕረፍት ስለምትነሣኝ የለመነችውን አደርግላታለሁ፤ በየቀኑ መምጣቷና መብቷን እየጠየቀች መጮኋ ሰልችቶኛልና።›»

ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ይህ ዓመፀኛ ዳኛ የሚለውን ስሙ። ስለ ትክክልና ስሕተት ግድ የሌለው ሰው በመጨረሻ ልመናን የሚመልስ ከሆነ፥ በሰማይ ያለው አባታችሁማ ልጆቹ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ሲጮኹ፥ ለጸሎታቸው መልስ ብዙ ያቈያቸው ቢመስልም፥ እንዴት አብልጦ አይሰማቸውም? እላችኋለሁ፥ እግዚአብሔር ይፈርድላቸዋል፥ ጸሎታቸውንም ይመልሳል፤ ያውም ፈጥኖ! ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ እርሱን የሚጠባበቁትንና በእርሱ የሚያምኑትን በምድር ያገኝ ይሆንን?»

ደግሞም ኢየሱስ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎችን ለሚንቁ ሰዎች አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ይህም «የፈሪሳዊውና የቀራጩ» ምሳሌ ነው።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ፈሪሳዊ ነበረ፤ ሁለተኛው ደግሞ ቀራጭ ነበረ። ፈሪሳዊው ቆሞ ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን ለራሱ እንዲህ ባሉ ቃላት ይጸልይ ጀመር፦

‹እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌሎች ሰዎች፥ እንደ ሌቦችና በደለኞች ክፉዎችም፥ ወይም ደግሞ እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ። እግዚአብሔርን እንደማመልክ ለማሳየት በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ ምንም ምግብ አልበላም፤ ከማገኘውም ሁሉ ዐሥረኛውን ለእግዚአብሔር ቤት እሰጣለሁ።›

ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም። ደረቱንም እየደቃ እንዲህ አለ፦

‹እግዚአብሔር ሆይ፥ ማረኝ፥ ኃጢአቴንም ይቅር በለኝ!›»

ኢየሱስም አለ፦ «እላችኋለሁ፥ ከፈሪሳዊው ይልቅ ይህ ቀራጭ ኃጢአቱ ተሰርዮለት ወደ ቤቱ ሄደ። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ ግን ከፍ ይላል።»


ቀዳሚ ቀጣይ