የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ገንዘብን ለሚወዱ የተነገረ ምሳሌ

ምዕራፍ 67 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ገንዘብን ለሚወዱ የተነገረ ምሳሌ

ኢየሱስ ፈሪሳውያን ወደ ምኵራብ ዘወትር ቢሄዱም የሕጋቸውንም ሥርዓት በጥንቃቄ ቢጠብቁም፥ በልባቸው ግን ገንዘብን የሚወዱ እንደ ሆኑ፥ ለእግዚአብሔርም ሳይሆን ለዚህ ዓለም ነገር እንደሚኖሩ ያውቅ ነበር። ስለዚህ በድንገት ድሀ ስለ ሆነ ባለ ጠጋና ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ድሀ አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ይህም «የባለ ጠጋውና የአልዓዛር ምሳሌ» ይባላል።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «እንደ ንጉሥ ቀይ ልብስ የሚለብስ፥ በታላቅና ባማረ ቤት የሚኖር፥ የሚያገለግሉትም ብዙ አገልጋዮች ያሉት፥ ዕለት ዕለትም ምርጥ በሆነ መብል የሚደሰት አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ። በባለ ጠጋው ቤት ደጅ አጠገብ በየማለዳው አልዓዛር የሚባል አንድ ድሀ ለማኝ ይጣል ነበር፤ እርሱም በቍስል የተሸፈነ ነበረ፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪና ቍርስራሽ ለመብላት ይደሰት ነበር። የመንገድ ውሾችም እየመጡ ቍስሎቹን ይልሱ ነበር።»

«ከጥቂት ጊዜ በኋላ ድሀው ሞተ፤ ነፍሱም የእግዚአብሔር ሕዝብ አባት ከሆነው ከአብርሃም ጋር በሰማይ እንድትኖር በመላእክት ተወሰደች፤ በድህነቱ ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ሁልጊዜ እየጣረ ለእግዚአብሔር ኖሮ ነበርና። ባለ ጠጋውም ደግሞ ሞተ፥ ተቀበረም። ነገር ግን አብርሃም በደስታ ወደሚኖርበት ምድር ሊወስዱት ምንም መላእክት አልመጡም። ነፍሱ ወደ ወዮታና ወደ ኀዘን ወደ ሥቃይም ስፍራ ሄደች፤ ይህም ባለ ጠጋ ስለ ነበረ አይደለም፥ ነገር ግን በሀብቱ ሳለ እግዚአብሔርን ከቶ ስላላሰበ ነው።»

«ባለ ጠጋው በሥቃይ ሳለ ዓይኑን አቅንቶ በሩቅ አብርሃምን አየ፥ አልዓዛርንም በእቅፉ።»

«‹አብርሃም አባት ሆይ፥› ብሎ ጮኸ፥ ‹ማረኝ፤ በዚህ ነበልባል እቃጠላለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ ምላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ!›»

«አብርሃምም መለሰ፦ ‹ልጄ ሆይ፥ አንተ በምድር በሕይወት ሳለህ ደስታህን ሁሉ እንደ ተቀበልህ፥ አልዓዛር ግን በሕይወቱ ድህነትንና ሕመምን እንደ ተቀበለ አስብ። አሁን አልዓዛር ስለ መከራው ሁሉ መጽናናትን አገኘ፥ አንተም በጭንቅ ውስጥ ነህ። ከዚህም ሁሉ በላይ፥ በሰማይ ባለነው በእኛና በኃጢአተኞች መኖሪያ ባለኸው በአንተ መካከል ማንም ከእኛ ወደ አንተ ሊሄድ ወይም ከአንተ ወደ እኛ ሊመጣ የማይሻገረው ታላቅ ሸለቆ፥ ጥልቅ ገደል አለ።›»

«አንድ ጊዜ ባለ ጠጋ የነበረው አሁን ግን እንዲህ የደኸየው ሰው እንዲህ አለ፦ ‹ነገሩ እንዲህ ከሆነ አልዓዛርም ወደ እኔ ሊመጣ ካልቻለ፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ አልዓዛርን ወደ አባቴ ቤት እንድትልከው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ የሚያስፈራ የሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ጊዜው ሳያልፍ ይንገራቸው።›»

«አብርሃምም፦ ‹የሙሴ መጻሕፍትና የነቢያት ሁሉ ቃል አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ› አለ።»

«እርሱም፦ ‹አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ወደ እነርሱ ቢሄድ ከኃጢአት ተመልሰው ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ› አለ።»

«አብርሃምም፦ ‹ሙሴንና ነቢያትን የማይሰሙ ከሆኑ፥ ከሙታን አንዱ እንኳ ቢነሣ አያምኑም› አለው።»

የኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይህን ምሳሌ በሰሙ ጊዜ፦ «ጌታ ሆይ፥ እምነታችንን አጽናልን!» አሉት።

ኢየሱስም አለ፦ «የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ‹ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል› ብትሉት ይታዘዝላችሁ ነበር።»

«ከእናንተ የሚያርስ ወይም በጎችን የሚጠብቅ አገልጋይ ያለው ማን ነው፥ ከእርሻ ሲመለስ ‹ወዲያው ና፥ ለእራትህ በማዕድ ተቀመጥ› የሚለው? ይልቁንስ አገልጋዩን ‹እራቴን አሰናዳልኝ፤ ከዚያም እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ልታገለግለኝ ተዘጋጅ፤ ከዚያ በኋላ አንተ እራትህን ልትበላ ትችላለህ› ይለዋል።»

«ጌታ አገልጋዩን የታዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን? እንግዲህ ለእናንተም እንዲሁ ነው፤ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ ‹አገልጋዮች ብቻ ነን፤ ልናደርገው ከሚገባን በላይ ምንም አላደረግንም› በሉ።»


ቀዳሚ ቀጣይ