የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የዐመፀኛው መጋቢ ምሳሌ

ምዕራፍ 66 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

የዐመፀኛው መጋቢ ምሳሌ

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ «ዐመፀኛው መጋቢ» የሚለውን ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። መጋቢ ማለት በሚቀጥረው በሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ማንኛውንም ንግድ ወይም መሬት ወይም ቤት የሚያስተዳድር ሰው ነው። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦

«ንግዱን ሁሉ የሚያስተዳድርለት መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ። አንድ ሰውም መጋቢው እያታለለውና ገንዘቡን ያለ አግባብ እየተጠቀመበት እንደ ሆነ ለባለ ጠጋው ነገረው። ጌታውም መጋቢውን አስጠርቶ እንዲህ አለው፦»

«‹ይህ ስለ አንተ የምሰማው ምንድር ነው? ከእንግዲህ ወዲህ መጋቢዬ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሒሳብ አስረክብ።›»

«መጋቢውም በመጀመሪያ በዚህ እጅግ ታወከ፤ የመጋቢነት ሹመቱ ቢወሰድበት እንዴት እንደሚኖር አላወቀም።»

«በልቡም እንዲህ አለ፦ ‹ጌታዬ የመጋቢነት ስፍራዬን ከእኔ የሚወስድብኝ ከሆነ ምን ላድርግ? እንደ ገበሬ መሬት ለመቈፈር ኃይል የለኝም፤ በጎዳና መለመንም ያሳፍረኛል። አሃ፥ የመጋቢነት ሹመቴ በተወሰደብኝ ጊዜ ሰዎች አብሬያቸው እንድኖር ወደ ቤታቸው እንዲቀበሉኝ ምን እንደማደርግ ዐውቃለሁ።›»

«መጋቢውም ለጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሰዎች አንድ በአንድ ወደ እርሱ ጠራ።»

«የመጀመሪያውንም ‹ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?› ብሎ ጠየቀው።»

«ሰውየውም ‹መቶ በርሜል ዘይት› ብሎ መለሰ።»

«መጋቢውም ‹ይኸው፥ ደብዳቤህን ውሰድ፤ በመቶ በርሜል ፋንታ ኀምሳ በርሜል ብለህ ጻፍ› አለው።»

አያችሁ፥ ይህ ለሰውየው ኀምሳ በርሜል ዘይት እንደ ስጦታ መስጠት ነበር፤ ነገር ግን ከመጋቢው ከራሱ አልነበረም፤ ይልቁንም ዕዳ ላለበት ሰው ለመስጠት ከጌታው መስረቅ ነበር።

«ቀጥሎም ሌላውን ሰው ‹አንተስ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?› አለው።»

«ሰውየውም ‹መቶ ጫን ስንዴ› ብሎ መለሰ።»

«መጋቢውም ‹ይኸው ደብዳቤህ፤ ሰማንያ ብለህ ጻፍ› አለው።»

«ለጌታው ዕዳ ያለባቸውን ሁሉ እንዲሁ አደረገ፤ ለእያንዳንዳቸው ከዕዳቸው ከፊሉን ተወላቸው፤ ይኸውም በሚያስፈልገው ጊዜ እንዲወዳጁትና እንዲረዱት ነው።»

«ጌታውም ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ መጋቢውን አመሰገነው፤ ያመሰገነውም ትክክል ስላደረገ ሳይሆን አስቀድሞ አርቆ ስላሰበና ለሚመጣው ጊዜ ስለ ተዘጋጀ ነው።»

ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «የዚህ ዓለም ሰዎች አርቀው በማሰብና ለሚመጡት ቀኖች በማቀድ የእግዚአብሔር ብርሃን ካላቸው ይልቅ ብዙ ጊዜ ጥበበኞች ናቸው። እኔም እላችኋለሁ፤ የዚህን ዓለም ገንዘብ በምድር ሳይሆን በሰማይ ወዳጆችን ታፈሩበት ዘንድ ተጠቀሙበት፤ ይኸውም ምድርን በምትለቁበት ጊዜ ፈጽሞ ወደማያልፉ ወደ ሰማያዊ መኖሪያዎች እንዲቀበሏችሁ ነው። በትንሽ አደራ የታመነ በትልቅ አደራም የታመነ ነው፤ ታማኝ ያልሆነና በትንሽ ነገር ለማታለል የሚሞክር ደግሞ በትልቅ ነገርም ዐመፀኛ ይሆናል፥ ለማታለልም ይሞክራል። እንግዲህ በዚህ ዓለም ገንዘብ የማትታመኑ ከሆናችሁ የእግዚአብሔርን ባለጠግነት ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላው ሰው ገንዘብ የማትታመኑ ከሆናችሁስ ለዘላለም የራሳችሁ የሆነን ነገር እንዴት ልታገኙ ትጠብቃላችሁ?»

«ማንም አገልጋይ በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይችልም፤ ወይም አንዱን ጌታ ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ከአንዱ ጌታ ጋር ይቆማል ሁለተኛውንም ይንቃል። እግዚአብሔርን እያገለገላችሁ በዚያው ጊዜ ለገንዘብ መኖር አትችሉም።»

ይህ ሁሉ የተነገረው ገንዘብን የሚወዱና ስግብግቦች የነበሩት ፈሪሳውያን እየሰሙ ነው። እነርሱም በልባቸው ንቀትና መዘባበት ይዘው አደመጡ።

ኢየሱስም በልባቸው ያለውን ዐውቆ ለእነዚህ ፈሪሳውያን እንዲህ አላቸው፦

«ሰዎች ደጎች እንደ ሆናችሁ እንዲያምኑ የምታደርጉ እናንተ ናችሁ፤ እግዚአብሔር ግን በልባችሁ ያለውን ያያል፥ ያውቃልም። በሰው ዘንድ ከፍ ያለው በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነው።»


ቀዳሚ ቀጣይ