የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የጠፋውና የተገኘው ልጅ ምሳሌ

ምዕራፍ 65 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

የጠፋውና የተገኘው ልጅ ምሳሌ

የኢየሱስ ጠላቶች የነበሩት ፈሪሳውያንና ጻፎች ስለ እርሱ «ክፉ ሰዎችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ይበላል!» እንዳሉ ታስታውሳላችሁ። ኢየሱስም ለዚህ መልስ ሲሰጥ ከኃጢአቱ ተመልሶ የሰማዩን አባቱን የሚፈልገውን ኃጢአተኛ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚቀበለው የሚያሳይ ምሳሌ ወይም ታሪክ ነገራቸው። ይህ ከኢየሱስ ምሳሌዎች ሁሉ እጅግ ውብ ከሆኑት አንዱ ነው። «አባካኙ ልጅ» ይባላል። «አባካኝ» ማለት ገንዘቡን በግድየለሽነት እየበተነ የሚያጠፋ ሰው ማለት ነው፤ ይህም ታሪክ አባቱ የሰጠውን ገንዘብ ሁሉ ስላጠፋ አንድ ጐበዝ ነው። ምሳሌውም ይህ ነው፦

ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ሁለት ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበረ። ታላቁ ልጅ በቤት ተቀምጦ አባቱን በእርሻው ሥራ ይረዳው ነበር፤ ታናሹ ልጅ ግን ዕረፍት የሌለው ነበረና ወደ ሌላ ስፍራ መሄድ ፈለገ። ጐበዙም አባቱን እንዲህ አለው፦»

«‹አባቴ ሆይ፥ አንተ ከሞትህ በኋላ ከሀብትህ የሚደርሰኝን ድርሻ አሁን ስጠኝ።›»

«አባቱም ያለውን ሁሉ፥ መሬቱን፥ የወይን ቦታዎቹን፥ የወይራ ዛፎቹን፥ የበለስ ዛፎቹን፥ ቤቶቹን፥ የበጎቹንና የፍየሎቹን መንጋዎች፥ ገንዘቡንም በሦስት እኩል ክፍል አካፈለ። ከእነዚህም ሁለቱን ክፍሎች ለታላቁ ልጅ አስቀመጠ፤ ሦስተኛውን ክፍል ግን ለታናሹ ልጅ ሰጠው፤ በዚያ አገር ታላቁ ልጅ የቤተሰቡ ራስ እንደ መሆኑ ከታናሹ ልጅ እጥፍ እንዲቀበል ሥርዓት ነበርና።»

«ከጥቂት ቀናትም በኋላ ጐበዙ የሀብቱን ድርሻ ሸጦ በጥሬ ገንዘብ ለወጠው፤ ከዚያም እንደ ፈቃዱ ሊኖር ወደሚችልበት ወደ ሩቅ አገር ሄደ። በዚያም ከማይረቡ ወንዶችና ሴቶች ጋር እየበላና የወይን ጠጅ እየጠጣ የስንፍናና የመረን ሕይወት መኖር ጀመረ። ገንዘቡን ሁሉ አጥፍቶ በታላቅ ችግር ላይ ለመውደቅ ብዙ ወራት አልፈጀበትም። በተድላው ጊዜ አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ አሁን በችግሩ ሊረዱት አንዳቸውም አልተዘጋጁም። በዚያም ጊዜ በዚያ አገር ምግብ እጅግ ስለ ጠፋና ለሕዝቡ ሁሉ የሚበቃ እንጀራ ስላልነበረ ችግሩ ይበልጥ ከበደ።»

«ይህ ጐበዝ ሁሉ ነገር ጐደለው። ልብሱ ተቀዳዶ ቡትቶ ሆነ፤ ጫማውም አለቀ፤ ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ የሚበላው ምንም ስላላገኘ በረሃብ ይሞት ነበር። ከዚያ ቀደም ምንም ሥራ ሠርቶ አያውቅም ነበር፤ አሁን ግን ረሃብ ገፋፍቶት አንድ ጕርሻ እንጀራ የሚያስገኝለትን ሥራ እየፈለገ በየስፍራው ዞረ። በመጨረሻም ሊቀጥረው የፈቀደ አንድ ሰው አገኘ። ይህም ሰው እሪያዎቹን እንዲጠብቅና እንዲመግብ ወደ እርሻው ላከው። ይህ ሥራ እንደ ውርደት ይቈጠር ነበር፤ አይሁዳዊ ሁሉ የእሪያ ሥጋ አይበላም፥ እነዚያንም ርኩሳን እንስሶች በምንም መንገድ አይነካም ነበርና። ምስኪኑ ጐበዝ ግን በረሃብ ከመሞት ይህን ሥራ እንኳ ለመሥራት ተገደደ። በእርሻውም ውስጥ እጅግ ከመራቡ የተነሣ እሪያዎቹ ከሚበሉት የባቄላ አሰር አንሥቶ ሊበላ ተዘጋጅቶ ነበር፤ በዚያም አገር ማንም ግድ አልነበረውም፤ የሚበላውንም ነገር እንኳ የሚሰጠው አልነበረም።»

«ይህ ጐበዝ ተቀዳዶ፥ በረሃብ ደክሞ፥ ሊሞትም ተቃርቦ በሜዳው ውስጥ በሚያጕረመርሙ እሪያዎች መካከል ተቀመጠ። ድንገትም በአንድ ወቅት በብዙ ነገር ተደስቶ፥ አገልጋዮች እያገለገሉት በምቾት ይኖርበት የነበረው የአባቱ ቤት ትዝ አለው። አሁን ምን ያህል ሞኝ፥ ለደጉ አባቱ ምን ያህል ውለታ ቢስ፥ ምን ያህልም ክፉ እንደ ነበረ አየ። በሕልም ሲኖር የነበረ፥ አሁን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነቅቶ ወደ ልቡ የተመለሰ መሰለው። በልቡም እንዲህ አለ፦»

«‹እንዴ፥ በአባቴ እርሻ ያሉት ምንደኞች እንኳ ከሚበሉት የሚተርፍ ምግብ አላቸው፤ እኔ ግን እዚህ በረሃብ ልሞት ነው! ተነሥቼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፦ «አባቴ ሆይ፥ በሰማይ ባለው በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በደልሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ በደመወዝ እንደሚሠሩ አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።»›»

«ምስኪኑ ጐበዝ እርሻውንና እሪያዎቹን ትቶ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ። በዚያም አባቱ የባዘነውን ልጁን እየጠበቀና እየተመለከተ በደጁ ተቀምጦ ነበር። ልጁም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየው፤ ባዶ እግሩንና ቡትቶ ለብሶ ሳለ እንኳ ዐወቀው። መልኩ የደረሰበትን ፍጹም መከራ ያሳይ ነበርና ለልጁ ራራለት፤ ወደ እርሱም ሮጦ አንገቱን አቅፎ በክንዶቹ ያዘውና ሳመው።»

«ጐበዙም ‹አባቴ ሆይ፥ በሰማይ ባለው በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በደልሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም—› አለ። አባቱ ግን ከዚያ በላይ ሊሰማው አልጠበቀም። አገልጋዮቹንም ጠርቶ እንዲህ አለ፦»

«‹ፈጥናችሁ አዲስ ልብስ፥ በቤቱ ካለው ሁሉ የሚበልጠውን አምጥታችሁ አልብሱት፤ በእጁ የሚደረግ ቀለበትና ለእግሩ ጫማ አምጡ፤ ሄዳችሁም ከጋጣው የሰባውን ፊሪዳ መርጣችሁ ለግብዣ እረዱት! ሁላችንም እንብላ፤ በአንድነትም ደስ ይበለን። ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፥ ሕያውም ሆነ፤ ጠፍቶም ነበር፥ ተገኘም!›»

«ደስም ይላቸው ጀመር። ታላቁ ልጅ ግን በእርሻ ነበረ፤ ወደ ቤቱም ሲቀርብ የዘፈንና የጭፈራ ድምፅ ሰማ። የዚህ ሁሉ ደስታ ምክንያት ምን እንደ ሆነ ተደንቆ ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ እርሱ ጠርቶ ይህ ሁሉ ምን እንደ ሆነ ጠየቀው።»

«አገልጋዩም ‹ወንድምህ ወደ ቤት መጥቷል፤ አባትህም በደኅና ስላገኘው ከጥጆቹ ሁሉ የሰባውን አርዶ ግብዣ አድርጓል› ብሎ መለሰለት።»

«ይህም ታላቁን ልጅ እጅግ አስቈጣው። ወደ እራቱ ሊገባ አልፈለገም፤ ከውጭም ቆመ። አባቱም ወጥቶ እንዲገባና ወንድሙን እንዲቀበል ለመነው።»

«እርሱ ግን እንቢ ብሎ እንዲህ አለ፦ ‹ይኸው ስንት ዓመት እንደማገለግልህ አስብ! አንድ ጊዜ ስንኳ ትእዛዝህን አላፈረስሁም፤ አንተ ግን ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ ከፍየሎች መንጋ አንዲት ትንሽ ጠቦት ስንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም። ነገር ግን ገንዘብህን ከርኩሳን ሰዎች ጋር ያባከነው ይህ ልጅህ ወደ ቤት እንደ መጣ የሰባውን ፊሪዳ አርደህ ታላቅ ግብዣ አደረግህለት።›»

«አባቱም እንዲህ አለው፦ ‹ልጄ ሆይ፥ አንተና እኔ ሁልጊዜ አብረን ነን፤ የእኔም የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበርና ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበርና ተገኝቷል፤ ስለዚህ ደስ ከማለትና ከመደሰት ልንቆጠብ አንችልም ነበር።›»

በታሪኩ ውስጥ በተነገረው በዚህ ታላቅ ወንድም የፈሪሳውያንና የጻፎች መንፈስ እንደ ነበረ ታያላችሁ፤ እነርሱ ኃጢአተኞች የነበሩት ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ተጸጽተው ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ኢየሱስ ሊቀበላቸው ፈቃደኛ በመሆኑ ተከፉ።


ቀዳሚ ቀጣይ