ምዕራፍ 64 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
የጠፉትን መፈለግ
ፈሪሳውያን የአይሁድን ሕግ ሥርዓቶች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ነበር፤ በሕዝብ ፊት በአደባባይ ብዙ ጊዜ ስለሚጸልዩና ዘወትር ወደ ጸሎት ቤት ስለሚሄዱም እጅግ ሃይማኖተኞች እንደ ሆኑ ይቈጠሩ ነበር። ኢየሱስ ግን ሃይማኖታቸው እውነተኛ ሳይሆን የይምሰል ብቻ እንደ ሆነ አየ፤ ስለ ኃጢአታቸው ከመገሠጽ በቀር ከእነርሱ ጋር ምንም ግንኙነት አልፈለገም። በየጸሎት ቤቱ የሕግ መምህራን የነበሩት ጻፎችም ኢየሱስ ልዩ ክብር እንዲሰጣቸው ይጠብቁ ነበር። ኢየሱስ ግን ምንም ትኩረት እንዳልሰጣቸውና አይሁድ ሁሉ ከሚንቋቸውና ከሚጠሏቸው ቀራጮች ጋር ወዳጅ እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ፈሪሳውያንም ጻፎችም እጅግ ተቈጡ። ኢየሱስ ወደ ጸሎት ቤት የማይሄዱትንና የአይሁድን ሥርዓት ለመጠበቅ የማይሞክሩትን የተናቁ ሰዎች እንኳ ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ፈቀደላቸው።
ፈሪሳውያንና ጻፎችም ኢየሱስን በታላቅ ንቀት «ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ይበላል!» አሉ።
ኢየሱስም ቃላቸውን ሰምቶ «የጠፋው በግ» በተባለው ምሳሌ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦
«ከእናንተ መቶ በጎች ያሉት ሰው ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በጎች በሜዳ ባለው በረት ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው አይሄድምን? ባገኘውም ጊዜ በታላቅ ደስታ በትከሻው ተሸክሞ ወደ ቤቱ ያመጣዋል። ወደ ቤቱም በደረሰ ጊዜ ጎረቤቶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ ‹የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ኑ፥ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ› ይላቸዋል።»
«እንዲሁ እላችኋለሁ፤ አስቀድመው ደጎች ከሆኑና ከኃጢአት መመለስ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ሃይማኖተኞች ይልቅ ከኃጢአቱ ተመልሶ ወደ እግዚአብሔር በሚመጣ በአንድ የተናቀ ኃጢአተኛ በሰማይ የሚሆነው ደስታ ይበልጣል።»
አንዲት ሴት ይህን ምሳሌ በግጥም ጽፈዋለች፤ ግጥሙም በዜማ ተቀናብሮ ብዙ ጊዜ ተዘምሯል። ግጥሞቿ እነዚህ ናቸው፦
ዘጠና ዘጠኙ
ዘጠና ዘጠኙ በደኅና ተኝተው ነበር
በበረቱ መጠለያ ውስጥ፥
አንዱ ግን በኮረብቶች ላይ ርቆ ነበር፥
ከወርቁ ደጆች እጅግ ርቆ—
በዱሩና በራቁቱ ተራሮች ላይ ርቆ፥
ከርኅሩኁ እረኛ ጥበቃ ርቆ።
«ጌታ ሆይ፥ ዘጠና ዘጠኙ በዚህ አሉልህ፤
እነርሱ አይበቁህምን?»
እረኛው ግን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «ይህ የእኔ ነው፥
ከእኔ ርቆ የባዘነ፤
መንገዱም ሻካራና ዳገታም ቢሆን
በጌን ልፈልግ ወደ ምድረ በዳ እሄዳለሁ።»
ከተቤዡት ግን አንዱ ስንኳ አላወቀም
የተሻገራቸው ውኆች ምን ያህል ጥልቅ እንደ ነበሩ፤
ጌታ ያለፈባት ሌሊትም ምን ያህል ጨለማ እንደ ነበረች
የጠፋውን በጉን ሳያገኝ በፊት።
በምድረ በዳው ውስጥ የበጉን ጩኸት ሰማ፥
ታሞ፥ ረዳት አጥቶ፥ ሊሞትም ተቃርቦ።
«ጌታ ሆይ፥ በመንገዱ ሁሉ ያሉት እነዚህ የደም ጠብታዎች ከወዴት ናቸው፥
የተራራውን ዱካ የሚያሳዩት?»
«የፈሰሱት ለባዘነው ለአንዱ ነው፥
እረኛው መልሶ ሳያመጣው በፊት።»
«ጌታ ሆይ፥ እጆችህ እንዲህ የተቀደዱትና የቈሰሉት ከምን የተነሣ ነው?»
«ዛሬ ሌሊት በብዙ እሾህ ተወግተዋል።»
ነገር ግን በነጐድጓድ በተሰነጠቁት ተራሮች ሁሉ፥
ከዓለታማውም ገደል ወደ ላይ፥
እስከ ሰማይ ደጅ ድረስ አንድ ጩኸት ተነሣ፦
«ደስ ይበላችሁ! በጌን አገኘሁ!»
መላእክትም በዙፋኑ ዙሪያ እንዲህ ብለው አስተጋቡ፦
«ደስ ይበላችሁ! ጌታ የራሱን መልሶ ያመጣልና!»
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ሲ. ክሌፌን።
ኢየሱስም «የጠፋው ድሪም» የሚባለውን ሌላ ምሳሌ ለሕዝቡ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦
«ወይም ዐሥር የብር ድሪሞች ያሏት ሴት ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋባት ምን ታደርጋለች? መብራቷን አብርታ ቤቷን ትጠርጋለች፤ እስክታገኘውም ድረስ ገንዘቧን አጥብቃ ትፈልጋለች። ባገኘችውም ጊዜ ወጥታ ሴት ወዳጆቿንና ጎረቤቶቿን ጠርታ ‹የጠፋብኝን ድሪም አግኝቼዋለሁና ኑ፥ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ› ትላቸዋለች።»
«እንዲሁ እላችኋለሁ፤ ወደ እግዚአብሔር በሚመለስ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ዘንድ ደስታ ይሆናል።»
አንድ ሰው—ሴቲቱ የጠፋውን ድሪሟን ስትፈልግ መብራት ማብራት ለምን አስፈለጋት? ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። በዚያ አገር የተራ ሰዎች ቤቶች ወይ መስኮት የላቸውም፥ ወይም ለቤቱ ሁሉ አንድ መስኮት ብቻ አላቸው፤ እርሱም በግድግዳው ላይ ያለ ቀዳዳ ብቻ ነው። ክፍሎቹ በቀትር እንኳ ጨለማ ናቸው፤ ስለዚህ ወለሉን፥ በተለይም ማዕዘኖቹን፥ በሚገባ ለማየት መብራት ተለኵሶ ወደ ወለሉ ተጠግቶ መያዝ አለበት።