ምዕራፍ 63 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ዋጋውን አስቀድሞ ስለ መቍጠር
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በፔሪያ በየከተማው እየሰበከ ሳለ የዳዊት ልጅና የእስራኤል ንጉሥ እንደ ሆነ በእርሱ እናምናለን የሚሉ ከቀድሞው ሁሉ የሚበልጡ ብዙ ሕዝብ ይከተሉት ነበር። ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ እንደ ሆነ አዩ፤ ወደዚያች ከተማ በደረሰ ጊዜ የንጉሥ ዳዊት የነበረውን ዙፋን እንደሚይዝ፥ የዚያችም አገር ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የአይሁድን ሕዝብ እየመራ አገሮችን ሁሉ እንደሚያሸንፍ የሚል ወሬ በመካከላቸው ተሰራጨ። ኢየሱስን ከሚከተሉት ሕዝብ እጅግ ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱ መሆን ምን ማለት እንደ ሆነ ፈጽሞ አላሰቡም ነበር። ታላላቅ ነገሮችን፥ ማለት ሀብትንና ክብርን ሥልጣንንም ይጠብቁ ነበር፤ ነገር ግን ኢየሱስ ሊቀበለው ያለውን መከራና ተከታዮቹም በቅርቡ በሚመጡት ቀናት የሚደርስባቸውን ስቃይ ምንም አያውቁም ነበር።
ኢየሱስ እንደ እነዚህ ያሉ ግድ የለሽና የማያስቡ ተከታዮች እንዲኖሩት አልወደደም። ጨካኝና የሚያስፈራ የሚመስል ቃል ተናገራቸው፤ ነገር ግን በእርሱ ከሚያምኑት መካከል ሊሆኑ ቢፈልጉ ምን እንደሚገጥማቸው እንዲያስቡ ለማድረግ ነበር። በዙሪያውም ወደሚጐርፉት ሕዝብ ዘወር ብሎ እንዲህ ብሎ ጮኸላቸው፦
«ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ማንም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በእግሬ ፈለግ የማይሄድ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም!»
ኢየሱስ የተናገረ የሚመስለውን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ቃል በቃል ማለቱ አልነበረም። ወንዶችና ሴቶች ልጆች አባቶቻቸውንና እናቶቻቸውን በእውነት እንዲጠሉ፥ ወላጆችም የገዛ ልጆቻቸውን እንዲጠሉ አልፈለገም፤ ነገር ግን ማንም ‹አባቴና እናቴ ኢየሱስን እንድከተል አይፈቅዱልኝም፤ ስለዚህ ደቀ መዝሙሩ ልሆን አልችልም› እንዳይል ማለቱ ነበር። ደግሞም ወላጆች ‹የምጠብቃቸው ልጆች አሉኝ፤ ስለዚህ በኢየሱስ አምኜ ደቀ መዝሙሩ ልሆን አይገባኝም› እንዲሉ አልፈለገም። ሳያስቡ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች፥ ማንም ቢቃወመው ወይም በአገልግሎቱ ምንም መከራ ቢደርስባቸው፥ ስለ ክርስቶስ ብለው ሁሉን ሊያጡና እርሱን ሊያገለግሉ ፈቃደኞች እንደ ሆኑ ራሳቸውን እንዲጠይቁ ፈለገ።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ፥ አስቀድሞ ተቀምጦ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማይቈጥርና ለመፈጸም የሚበቃ ገንዘብ እንዳለው የማያይ ማን ነው? መሠረቱን ብቻ ጥሎ ሥራውን ሳይጨርስ ቢተወው፥ እኩሌታው የተሠራውን ግንብ የሚያዩ ሁሉ ‹ይህ ሰው መሥራት ጀመረ፤ ሊፈጽመው ግን አልቻለም!› እያሉ ይሥቁበታል።»
«ወይስ ከሌላ ንጉሥ ጋር ሊዋጋ የሚሄድ ንጉሥ፥ በሃያ ሺህ ወታደሮች ሊመጣበት ያለውን ንጉሥ በዐሥር ሺህ ወታደሮች ሊገጥመው ይችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማይመክር ማን ነው? ጠላቱን ሊገጥም ባይደፍር፥ ሠራዊቱ ገና ሩቅ ሳለ የዕርቅን ነገር እንዲጠይቅ መልእክተኛ ይልካል። እንዲሁም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ማንም ቢሆን ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።»
ኢየሱስ ማለቱ ይህ ነበር፦ «ከተከታዮቼ መካከል ልትሆኑ ብትፈልጉ እስከ መጨረሻው ትጸኑ እንደ ሆነ አስቡ። ደግሞም ደቀ መዛሙርቴ ለመሆን ልታሸንፉት የሚገባችሁን ጥላቻና ተቃውሞ ለመጋፈጥ ትደፍሩ እንደ ሆነ አስቡ።» እንደዚህ ያሉትንም ቃሎች መናገሩን ቀጠለ፦
«እውነተኛ ደቀ መዝሙሬ ሁሉ እንደ ጨው ነው፤ ጨውም የራሱ ጣዕም እስካለው ድረስ መልካም ነው። ጨው ግን ጣዕሙን አጥቶ አልጫ ቢሆን እንደ ገና መልካም ጨው የሚሆንበት መንገድ አለን? ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ሰዎች ግን የማይጠቅም ነው ብለው ወደ ውጭ ይጥሉታል። በራሱ ውስጥ የሕይወቴን ጨው የሚያጣ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል። እንግዲህ እነዚህ ቃሎቼ በአንድ ጆሮአችሁ ገብተው በሌላው አይውጡ። ስሙ፥ የተናገርሁትንም አስቡ!»