የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በምኵራብና በግብዣ

ምዕራፍ 62 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

በምኵራብና በግብዣ

ኢየሱስ በፔሪያ ሳለ በሰንበት ቀናት ወደ ምኵራቦች እየገባ ያስተምር ነበር፤ በየስፍራውም ምኵራቡ እርሱን ለመስማት በሚጓጉ ሰዎች ይሞላ ነበር። በአንድ ሰንበት ቀን ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ ጐብጣ ቀና ልትል ፈጽሞ የማትችል አንዲት ሴት በምኵራቡ ውስጥ አየ። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ወደ እርሱ እንድትመጣ ጠራት።

«አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል» አላት።

እጁንም ጫነባት፤ በዚያው ቅጽበትም ኃይል ወደ እርስዋ መጣ። እርስዋም ቀና ብላ ቆመች፤ ስለ መፈወስዋም በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን አመሰገነች። የምኵራቡ አለቃ ግን ኢየሱስ ይህን በሰንበት ስላደረገ እጅግ ተቈጣ። ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦

«በሳምንት ውስጥ ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ ልትፈወሱ ከፈለጋችሁ ከእነዚህ በአንዱ ኑ እንጂ በተቀደሰው ሰንበት አትምጡ።»

ጌታ ኢየሱስም «እናንተ እግዚአብሔርን የምታገለግሉ መስላችሁ የምትታዩ ልባችሁ ግን ሐሰተኛ የሆነ ሰዎች ሆይ!» አለ። «ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሬውን ወይም አህያውን ከግርግም ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአባታችን የአብርሃም ልጅ የሆነች፥ ክፉው እነሆ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አስሮ የያዛት ሴት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባትምን?»

ይህንም ሲናገር የሚቃወሙት ሁሉ በራሳቸው እጅግ አፈሩ፤ ሕዝቡ ግን ባደረገው ድንቅ ሥራ ሁሉ ደስ አላቸው። ኢየሱስ ሁልጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እያቀና በከተሞችና በመንደሮች ሲያልፍ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች የሰጣቸውን ብዙ ምሳሌዎችና ትምህርቶች፥ ለምሳሌ «ጠባቡ በር»፥ «የሰናፍጭ ቅንጣት»፥ «በሊጥ ውስጥ ያለ እርሾ» እና ሌሎችንም ደግሞ አስተማረ።

በዚያ ጊዜ ያስተምርበት የነበረው የፔሪያ አገር የሄሮድስ ግዛት ነበረ። የኢየሱስ ጠላቶች የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦

«ንጉሥ ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ አገር ብትወጣ ይሻልሃል።»

ይህንም ያሉት ከእነርሱ አገር ተነሥቶ እንዲወጣ ለማድረግ እንጂ የኢየሱስን ሕይወት ለማዳን አልነበረም። ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦

«ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ እንዲህ በሉአት፦ ‹እነሆ፥ ዛሬና ነገ ክፉ መናፍስትን አወጣለሁ በሽታዎችንም እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ሥራዬን እፈጽማለሁ።› ነገር ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ ወዲያም በመንገዴ ልሄድ ያስፈልገኛል። ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድዪ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ የላካቸውን የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን በዙሪያዬ ልሰበስብ ስንት ጊዜ ወደድሁ! እናንተ ግን አልመጣችሁም! በእውነት ቤታችሁ እንዲጠፋ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁ፥ ‹በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው› የምትሉበት ቀን እስኪመጣ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።»

በአንድ ስፍራ ከአለቆች አንዱ የነበረ አንድ ፈሪሳዊ ምሳ ሊበላ ወደ ቤቱ ጋበዘው። በማዕዱም ሌሎች ፈሪሳውያንና ለኢየሱስ ወዳጆች ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም የሚያደርገውን ሁሉ አጥብቀው ይጠባበቁት ነበር። በቤቱም ውስጥ ሰውነቱ በውኃ ሕማም ያበጠ አንድ ሰው አየ፤ ኢየሱስም የሕግ መምህራንንና ፈሪሳውያንን እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦

«በሰንበት በሽተኛን መፈወስ በሕግ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?»

እነርሱ ግን አንዳች ሳይመልሱ ዝም አሉ። ኢየሱስም እጁን በሰውዬው ላይ ጭኖ ፈወሰውና አሰናበተው። ከዚያም በኋላ እንዲህ አለ፦

«ከእናንተ አህያው ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ውስጥ ቢወድቅበት የሥራ ቀን ሳይጠብቅ ወዲያው የማያወጣው ማን ነው?»

ለዚህም ጥያቄ አንድ ቃል እንኳ ሊመልሱለት አልቻሉም። ወደ ግብዣው የተጠሩት ሰዎች በማዕዱ ራስ አጠገብ ያሉትን የከበሩ ስፍራዎች ለራሳቸው እንደ መረጡ አስተዋለ፤ ስለዚህም ይህን ምክር ሰጣቸው።

«ወደ ሰርግ ግብዣ በተጠራህ ጊዜ በከበረው ስፍራ አትቀመጥ። ምናልባት ከአንተ በማዕረግ የሚበልጥ ሰው ተጠርቶ ይሆናል፤ ግብዣውንም ያዘጋጀው ሰው መጥቶ ‹ለዚህ ሰው ስፍራ ልቀቅለት!› ይልሃል። ያን ጊዜም አፍረህ ተነሥተህ በማዕዱ መጨረሻ በታችኛው ስፍራ ትቀመጣለህ። ይልቅስ ወደ ግብዣው በመጣህ ጊዜ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ግብዣውን ያዘጋጀው ሰውም ባየህ ጊዜ ‹ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ› ይልሃል፤ በዚያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት እንግዶች ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።»

ኢየሱስም የጋበዘውን አለቃ ደግሞ እንዲህ አለው፦ «ምሳ ወይም እራት ባዘጋጀህ ጊዜ ወዳጆችህን ወይም ወንድሞችህን ወይም ዘመዶችህን ወይም ባለጠጎች ጎረቤቶችህን አትጥራ፤ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ይጠሩሃልና፥ እንዲህም ብድራትህን ትቀበላለህ። ይልቅስ ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችን፥ ጉንድሾችን፥ ክንዳቸውን ያጡትንና ዕውሮችን ጥራ። እግዚአብሔርም ይባርክሃል፤ እነዚህ ሰዎች ብድራትህን ሊመልሱልህ አይችሉምና፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ከመቃብራቸው ለዘላለም ሕይወት በሚያስነሣበት ጊዜ ዋጋህን ትቀበላለህ።»

በማዕዱ ከተቀመጡት አንዱ ይህን የኢየሱስን ቃል ሰምቶ «በእግዚአብሔር መንግሥት በዚያ ግብዣ የሚቀመጥ ብፁዕ ነው!» ብሎ ተናገረ።

ኢየሱስም «እራቱና ምክንያቶቹ» የሚለውን ምሳሌ በመስጠት መለሰለት። እንዲህም አለ፦

«በአንድ ወቅት ታላቅ እራት ያዘጋጀ አንድ ሰው ነበረ፤ ወደዚያም ብዙ ወዳጆቹን ጠርቶ ነበር። በእራቱም ሰዓት የተጠሩትን እንግዶች ‹አሁን ሁሉ ተዘጋጅቶአልና ፈጥናችሁ ኑ!› እንዲላቸው ባሪያውን ላከ። ሁሉም ግን በአንድ ልብ ሆነው ግብዣውን ይመልሱ ጀመር። የመጀመሪያው ሰው ለባሪያው እንዲህ አለው፦»

«‹መሬት ገዝቻለሁ፤ ሄጄም ላየው ያስፈልገኛል። እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ።›»

«ሁለተኛውም ‹አምስት ጥማድ በሬዎች ገዝቻለሁ፤ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ። እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ› አለ።»

«ሌላውም ‹አሁን ሚስት አግብቻለሁና ልመጣ አልችልም› አለ።»

«ባሪያውም ወደ ቤት ተመልሶ ይህን መልስ ሁሉ ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ እጅግ ተቈጣ። ባሪያውንም እንዲህ አለው፦»

«‹ፈጥነህ ወደ ከተማው አደባባዮችና መንገዶች ውጣ፤ ድሆችንና ጉንድሾችን ዕውሮችንና አንካሶችንም ወደዚህ አስገባ።›»

«ባሪያውም ብዙም ሳይቆይ ወደ ጌታው ተመልሶ ‹ጌታዬ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፤ ነገር ግን ገና ስፍራ አለ› አለ።»

«ባለቤቱም ‹ቤቴ እንዲሞላ ወደ ገጠሩ ወደ መንገዶችና ወደ ቅጥሮች ውጣ፤ ሰዎችንም ግድ ብለህ አስገባ፤ እላችኋለሁና፥ ከእነዚያ ከተጠሩት ሰዎች አንዱ እንኳ እራቴን አይቀምስም› አለ።»


ቀዳሚ ቀጣይ