ምዕራፍ 61 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ በፔሪያ ሲሰብክ
ኢየሱስ በኤፍሬም መንደር ብዙ ጊዜ አልቆየም። ከተራሮቹ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረደ፤ ወንዙንም ተሻግሮ ሰባው መልእክተኞቹ መምጣቱን አስቀድመው ወዳወሩባቸው ስፍራዎች እየሄደ በፔሪያ አገር ይሰብክ ጀመረ።
በየስፍራውም ሕዝቡ ሊያዩትና ቃሉን ሊሰሙ በታላቅ ብዛት እየተሰበሰቡ ይጋፉ ነበር። በሕዝቡ መካከል ሀብታሞችና ድሆች፥ አለቆችና ተራ ሰዎች፥ ጠላቶቹ የነበሩት ፈሪሳውያንና በኃጢአት የተሞላ ሕይወት ይኖሩ የነበሩት ቀራጮች ተገናኙ። ሕዝቡ ብዙ የሰሙለትን፥ ነገር ግን ከዚያ በፊት አይተውት የማያውቁትን ያን ከገሊላ የመጣውን መምህርና ነቢይ ለመስማት ታላቅ ምኞት ነበራቸው። ብዙዎችም በዙፋኑ ተቀምጦ አገሮችን ሁሉ ሊገዛ በመጨረሻ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ያለው ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው ክርስቶስ እርሱ ነው ብለው ስላመኑ ሊያዩት ሄዱ። ኢየሱስን ለማየትና ለመስማት የተሰበሰበው ሕዝብ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ በዙሪያው ያሉት ሺዎች እርስ በርሳቸው ይረጋገጡ ነበር ይባላል።
በአንድ ስፍራ ለብዙ ሕዝብ ሲናገር ከሕዝቡ መካከል አንድ ድምፅ ተሰማ።
አንድ ሰው «መምህር ሆይ፥ የቤተሰባችንን ርስት ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው» ብሎ ጮኸ።
ይህ ሰው ኢየሱስ የእስራኤል ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን በሕዝቡ መካከል በሚነሣ ክርክር ሁሉ የሚፈርድ መስሎት ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ ብሎ መለሰለት፦
«አንተ ሰው፥ በጉዳያችሁ ላይ ፈራጅና አካፋይ እንድሆን ማን ሾመኝ?»
ቀጥሎም «ከገንዘብ ፍቅር ተጠበቁ፤ ሰው ምንም ያህል ሀብታም ቢሆን እውነተኛ ሕይወቱ ባለው ገንዘብ ላይ የተመሠረተ አይደለምና» አለ።
«ድሀው ሀብታም» የሚለውንም ምሳሌ ወይም ታሪክ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦
«እርሻው እጅግ ብዙ ፍሬ የሰጠው አንድ ሀብታም ሰው ነበረ። እርሱም በልቡ ‹ምን ላድርግ? በምድሬ ላይ ያደገውን እህልና ፍሬ የማከማችበት ስፍራ የለኝም። ይህን አደርጋለሁ፤ የቀድሞ ጎተራዎቼን አፍርሼ በእነርሱ ፋንታ የሚበልጡ እሠራለሁ። በዚያም ከአትክልቴ የሚገኘውን ፍሬና ከእርሻዬ የሚገኘውን እህል ሁሉ አከማቻለሁ። ከዚያም ነፍሴን «አሁን ለብዙ ዓመታት የሚበቃ ብዙ መልካም ነገር ተከማችቶልሻል፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ» እላታለሁ› ብሎ ያስብ ጀመር። እግዚአብሔር ግን ‹አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህ ከአንተ ትወሰዳለች፤ ያከማቸኸው ሁሉ ለማን ይሆናል?› አለው። የእግዚአብሔርን ባለጠግነት በማግኘት ፋንታ ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች ሁሉ እንዲሁ ነው።»
ኢየሱስም ቀደም ሲል በታላቁ «የተራራው ስብከት» ያስተማራቸውን አንዳንድ ነገሮች ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገና ነገራቸው፤ እርሱ ከእነርሱ ከተወሰደ በኋላ እነርሱ በተራቸው ለሌሎች ይነግሩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ በልባቸው እስኪያጠኑት ድረስ ያንኑ ትምህርት ደጋግሞ ያስተምር ነበርና። በዚህ ጊዜም እንዲህ አለ፦
«ስለዚህ እላችኋለሁ፥ በዚህ ምድር ስለ ሕይወታችሁ የምትበሉትን ወይም የምትለብሱትን በማሰብ አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፥ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። በአየር ላይ የሚበሩትን ቍራዎች ተመልከቱ! አይዘሩም አያጭዱምም፤ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ በእግዚአብሔር ፊት ከወፎች እንዴት እጅግ ትበልጣላችሁ? ብትጨነቁስ በዕድሜያችሁ ላይ አንዲት ደቂቃ ልትጨምሩ ትችላላችሁን? ይህን እንኳ ካልቻላችሁ ስለ ሌላው ነገር ሁሉ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ?»
«አበቦችን እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ። አይፈትሉም አይሸምኑምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እንግዲህ ዛሬ የሚያብበውን ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እግዚአብሔር እንዲህ አሳምሮ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እግዚአብሔርን በጥቂቱ የምትታመኑ ሰዎች ሆይ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም?»
«ስለዚህ ስለ ምግብና ስለ መጠጥ ስለ ልብስም አትጨነቁ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ የዓለም አሕዛብ የሚፈልጉት ይህን ነውና፤ እናንተም እንደ እነርሱ ልትሆኑ አትውደዱ። ደግሞም የሰማዩ አባታችሁ እነዚህ የተለመዱ ነገሮች እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ብቻ ፈልጉ፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህን ነገሮች እንድታገኙ ያደርጋል። አንተ ታናሽ መንጋ፥ በመንግሥቱ ስፍራ ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ።»
በዚህ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የሮማው አገረ ገዥ ጲላጦስ አንዳንድ የገሊላ ሰዎችን በመሠዊያው አጠገብ ሲሰግዱ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ገደላቸውና ደማቸው ከመሥዋዕታቸው ደም ጋር እንደ ፈሰሰ ወሬ ለኢየሱስ አመጡለት። ይህ የአገረ ገዥው ድርጊት ሕዝቡን ሁሉ እጅግ አስደንግጦ ነበር።
ኢየሱስም «እነዚያ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው በገሊላ ከሚኖሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሏችኋልን?» አለ። «እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ከኃጢአታችሁ ተመልሳችሁ እግዚአብሔርን ባትፈልጉ ሁላችሁ ደግሞ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።»
«ደግሞም ከኢየሩሳሌም ውጭ ጥቂት ራቅ ብሎ በሰሊሆም የነበሩትን፥ ግንቡ ወድቆባቸው ሁሉንም የገደላቸውን እነዚያን ዐሥራ ስምንት ሰዎች አስቡ፤ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ክፉዎች የነበሩ ይመስሏችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ወደ እግዚአብሔር ባትመለሱ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ።»
ከዚያም ኢየሱስ «ፍሬ የማታፈራው በለስ» የሚለውን ምሳሌ ለሕዝቡ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦
«አንድ ሰው በአትክልቱ ውስጥ የበቀለች በለስ ነበረችው፤ በለስ በሚበስልበትም ወራት ፍሬ ሊፈልግባት መጣ፤ ነገር ግን አንዲት በለስ እንኳ አላገኘባትም። አትክልተኛውንም ‹እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም። ቍረጣት! ስለ ምን ስፍራ ይዛ መሬቱን ታጐሳቍላለች?› አለው። አትክልተኛው ግን ‹ጌታዬ ሆይ፥ እባክህ አንድ ዓመት ደግሞ ተዋት። ዙሪያዋን ኰትኵቼ መሬቱን አዳብራለሁ፤ በሚመጣውም ዓመት ምናልባት ታፈራ ይሆናል። ባታፈራ ግን ትቈረጣለች› ብሎ መለሰለት።»