የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
አልዓዛር ከመቃብሩ ተጠራ

ምዕራፍ 60 · 6 ደቂቃ ንባብ · 7 ደቂቃ ማዳመጥ

አልዓዛር ከመቃብሩ ተጠራ

ኢየሱስ ገና በቤተ ራባ ሳለና በቅርቡ በፔሪያ በኩል ጕዞውን ሊጀምር ሲጠብቅ፥ ለጊዜው ዕቅዱን እንዲለውጥ ያደረገው ወሬ ደረሰው።

እንደምታስታውሱት፥ በኢየሩሳሌም አጠገብ ባለችው በቢታንያ የሚወዳቸው ወዳጆቹ ማርታና ማርያም አልዓዛርም ይኖሩ ነበር። ሁለቱ እኅቶች በቤተ ራባ ወዳለው ወደ ኢየሱስ እንዲህ የሚል መልእክት ላኩ፦

«ጌታ ሆይ፥ ወዳጅህ አልዓዛር በጽኑ ታሞአል።»

መጥቶ አልዓዛርን እንዲፈውስ ኢየሱስን አልለመኑትም፤ ነገር ግን ከቤተ ራባ እስከ ቢታንያ ስድሳ ማይል መጓዝ ቢያስፈልገውም ምናልባት ይመጣ ይሆናል ብለው ተስፋ አደረጉ። ኢየሱስ ግን ወዲያውኑ ወደ ታመመው ሰው አልሄደም። እንዲህም አለ፦

«ይህ ሕመም በሞቱ የሚፈጸም አይደለም፤ ፍጻሜው ለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ልጅ ክብርን መስጠት ነው።»

ኢየሱስ ማርታንና ማርያምን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። ቢሆንም አልዓዛር በጽኑ መታመሙን በሰማ ጊዜ በቤተ ራባ ሁለት ቀን ጨምሮ ተቀመጠ። ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን «እንደ ገና ወደ ይሁዳ እንሂድ» አላቸው።

በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተደነቁ። እንዲህም አሉት፦ «መምህር ሆይ፥ ገና ከጥቂት ጊዜ በፊት የይሁዳ ሰዎች ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር እኮ። እንደ ገና ወደዚያ መሄድህ አያሰጋም ወይ?»

ኢየሱስም «ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን?» ብሎ መለሰ። «ሰው በቀን ቢመላለስ የፀሐይን ብርሃን ስለሚያገኝ አይሰናከልም፤ በሌሊት ቢመላለስ ግን ብርሃን ስለሌለው ይሰናከላል።»

ቀጥሎም «ወዳጃችን አልዓዛር አንቀላፍቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ» አለ።

ደቀ መዛሙርቱም «መምህር ሆይ፥ አንቀላፍቶ ከሆነ ይድናል» አሉት።

ኢየሱስ በእንቅልፍ ስለ ማረፍ የሚናገር መሰላቸው፤ ይህም ንዳዱ እየለቀቀው መሆኑን የሚያሳይ ነበር፤ ኢየሱስ ግን አልዓዛር በሞት እንቅልፍ እንዳለ ማለቱ ነበር። ስለዚህ በግልጥ ቃል እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦

«አልዓዛር ሞተ፤ በዚያም ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን በእኔ ይበልጥ ማመንን ትማራላችሁና። አሁንም ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ።»

በዚህ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ አንዱ፥ «መንታ» የሚል ትርጕም ባለው ቃል «ዲዲሞስ» ተብሎ ደግሞ የሚጠራው ቶማስ፥ ለባልንጀሮቹ ደቀ መዛሙርት እንዲህ አላቸው፦

«እኛም ደግሞ እንሂድ፤ እርሱም ቢሞት ከእርሱ ጋር እንሞታለን።»

ስለዚህ ከቤተ ራባ ተነሥተው ከኢየሩሳሌም ሁለት ማይል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቢታንያ እንደ ገና ሄዱ፤ ይህም ስድሳ ማይል ያህል የሆነ ጕዞ ነበር። ኢየሱስ ወደ ቢታንያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር በመቃብር አራት ቀን ሆኖት አገኘ። በቤቱ ውስጥ ከማርታና ከማርያም ጋር በወንድማቸው ሞት ከእኅቶቹ ጋር አብረው እያለቀሱ ሐዘናቸውን ሊካፈሉ የመጡ ብዙ ወዳጆቻቸው ነበሩ።

አንድ ሰው ወደ ክፍሉ ገብቶ ኢየሱስ እየመጣ እንደ ሆነና ወደ መንደሩም እንደ ቀረበ ለማርታ ነገራት። እርስዋም በጸጥታ ተነሥታ ኢየሱስን ልትቀበል ቸኩላ ወጣች፤ ማርያም ግን በክፍሉ ውስጥ ተቀምጣ ቀረች። ማርታ ኢየሱስን ባየች ጊዜ በሐዘን እንዲህ አለችው፦

«ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ቢሆን ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ።»

ኢየሱስም «ወንድምሽ እንደ ገና ወደ ሕይወት ይነሣል» አላት።

ማርታም «ሙታን ሁሉ በሚነሡበት በመጨረሻው ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ» አለች።

ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ «ሙታንን ወደ ሕይወት የማስነሣ እኔ ራሴ ነኝ። በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ እንደ ገና በሕይወት ይኖራል፤ በእኔ እያመነ በሕይወት የሚኖር ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ይህን ታምኛለሽን?»

እርስዋም «አዎን ጌታ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም ሊመጣ ተስፋ የተሰጠበት ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምናለሁ» አለች።

ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ኢየሱስን ገና ከመንደሩ ውጭ ትታው እንደ ገና ወደ ቤት ሄደች። እኅትዋንም ማርያምን በሹክሹክታ እንዲህ አለቻት፦

«መምህሩ መጥቶአል፤ ይጠራሽማል።»

ማርያምም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ኢየሱስ ወዳለበት ስፍራ ሄደች። ከእርስዋ ጋር የነበሩት ወዳጆችም ከቤት ስትወጣ ባዩአት ጊዜ በዚያ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መሰላቸውና ከእርስዋ ጋር ሊያለቅሱ ተከተሉአት። በዚያች አገር ወዳጃቸው የሞተባቸው ሰዎች ቀን በቀን በመቃብሩ ተገናኝተው በዚያ ስለ እርሱ ማልቀስ ልማድ ነበረ፤ አሁንም ልማድ ነው።

ማርያም ግን ወደ ወንድምዋ መቃብር አልሄደችም። ማርታ ወደ ተገናኘችው ስፍራ ገና ወደ ነበረው ወደ ኢየሱስ ሄደች፤ ከእግሩም በታች ወድቃ እኅትዋ አስቀድማ እንደ ተናገረችው እንዲህ አለች፦

«መምህር ሆይ! አንተ በዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር!»

ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ፥ ከእርስዋም ጋር የመጡት ወዳጆች ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ ታወከ፤ እጅግም አዘነ።

«ወዴት አኖራችሁት?» ብሎ ጠየቀ።

እነርሱም «መምህር ሆይ፥ መጥተህ እይ» ብለው መለሱለት።

ኢየሱስም ለሁለቱ እኅቶች ከማዘኑ የተነሣ ያለቅስ ጀመር።

አይሁድም እርስ በርሳቸው «እንዴት ይወደው እንደ ነበር እዩ!» ተባባሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን እንዲህ አሉ፦

«ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ሰው ይህ ሰው እንዳይሞት ሊያደርግ አይችልም ነበርን?»

ኢየሱስም ደግሞ በጸጥታ እያቃሰተ ወደ መቃብሩ መጣ። በዚያች አገር እንዳሉ እንደ ብዙ መቃብሮች፥ ይህም በዓለታማው ኮረብታ ጐን ያለ ዋሻ ነበረ፤ በአፉም ላይ ትልቅ ድንጋይ ተገጥሞበት ነበር።

ኢየሱስም «ድንጋዩን አንሡ» ብሎ አዘዘ።

ማርታም «መምህር ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን እንደ ሆነው አስብ፤ አሁን ከሥጋው ብርቱ ሽታ ሊኖር ይችላል» አለችው።

ኢየሱስም «በእኔ ብቻ ብታምኚ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?» አላት።

ድንጋዩንም ከዋሻው ደጃፍ አነሡት፤ ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፦

«አባት ሆይ፥ ጸሎቴን ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቅ ነበር፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዙሪያዬ ስለ ቆሙት ሰዎች ይህን ተናገርሁ።»

ከዚያም ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦

«አልዓዛር ሆይ! ና ውጣ!»

ሞቶ የነበረውም ሰው ከመቃብሩ ወጣ። እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ ተጠቅልለው ስለ ነበሩ መራመድ እንኳ አልቻለም ነበር፤ ፊቱም ደግሞ በላዩ በታሰረ ጨርቅ ተሸፍኖ ነበር።

ኢየሱስም «ፍቱትና ይሂድ ተዉት!» አለ።

ጨርቁንም ከፊቱ አነሡለት፤ መግነዙንም ከሰውነቱ ፈቱለት፤ አልዓዛርም በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሕይወት ሆኖ ደኅና ሆኖ ቆመ! ማርታና ማርያም እጆቻቸውን በዙሪያው ሲጠመጥሙና የሕይወት ደም እንደ ገና በደም ሥሮቹ ውስጥ እየፈሰሰ ሥጋው ሞቆ ሲሰማቸው እንዴት ደስ አላቸው!

ማርታንና ማርያምን ሊጠይቁ የመጡት አይሁድ ይህን ድንቅ ሥራ፥ በመቃብሩ አራት ቀን የቆየውን ሰው ወደ ሕይወት መመለሱን ባዩ ጊዜ ከእነርሱ ብዙዎቹ በኢየሱስ አመኑ። እነዚህም ታሪኩን ለሌሎች ነገሩ፤ የአማኞቹም ቍጥር እየበዛና እየበዛ ሄደ።

የአልዓዛርን ከሞት መነሣት ካዩ ወይም ከሰሙ ሰዎች አንዳንዶቹ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው የሆነውን ነገር ለኢየሱስ ጠላቶች ለፈሪሳውያን ነገሩ። እነዚህም ሰዎች ለካህናት አለቆች ነገሩ፤ ካህናቱና ፈሪሳውያኑም ስለ እነዚህ ነገሮች እንዲነጋገሩና በኢየሱስ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት እንዲወስኑ ታላቁን ሸንጎ ሰበሰቡ።

ይህ ታላቅ ሸንጎ ከሮማዊው አገረ ገዥ ቀጥሎ በአይሁድ ላይ የሚገዛ የታላላቅ ሰዎች ጉባኤ ወይም ማኅበር ነበረ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ካህናት፥ አንዳንዶቹም ጻፎች ወይም የሕግ መምህራን የሆኑ ሰባ ሁለት ሰዎች ነበሩበት። ለእነርሱ አገልግሎት ተለይቶ በተሰጠ በቤተ መቅደስ ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ይሰበሰቡ ነበር፤ ሕግን ተላልፈዋል ተብለው የተከሰሱትንም ሁሉ የሚዳኝ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ነበሩ።

ይህ ሸንጎ በተሰበሰበ ጊዜ ኢየሱስ ያደረገውንና ከቀድሞው ሁሉ በበለጠ ቍጥር በኢየሱስ ማመን የጀመሩትን ሰዎች ሰምተው እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ «ይህ ኢየሱስ ቀድሞ ካደረጋቸው ሥራዎቹ ሁሉ ይልቅ የሚደንቅ ሌላ ሥራ ስላደረገ አሁን ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወው ሕዝቡ ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ ንጉሣቸውም ሊያደርጉት ይፈልጋሉ። ከዚያም ሮማውያን መጥተው ቤተ መቅደሳችንን ያፈርሳሉ፤ ከእንግዲህም እንደ ሕዝብ እንድንኖር አይፈቅዱልንም።»

በሸንጎው ውስጥ ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ግን ቀያፋ የተባለው ሊቀ ካህናት ነበረ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦

«እናንተ ፈጽማችሁ ተሳስታችኋል። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የመጣ ነቢይ ቢሆንም ባይሆንም፥ ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ቢሞት እንደሚሻል አታስተውሉም። ኢየሱስ እንዲገደል፥ የእስራኤልም ሕዝብ ከሞት እንዲድን ሁላችንም እንስማማ።»

ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እርሱ ሲናገራቸው ከሚያውቀው በላይ ትርጕም ነበራቸው። እርሱ ሊቀ ካህናት በመሆኑ ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ እንደሚሞት ትንቢት ይናገር ነበር፤ ኢየሱስ በቅርቡ የሚያደርገው ይህንኑ ነበርና። ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ሊሞት ነበር፤ ስለ አይሁድ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለም ሕዝብ ሁሉ። ኢየሱስ በሞቱ በየአገሩ ሁሉ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ ወደ አንድ አካል ሊሰበስብ ነበር።

በዚያ የሸንጎ ስብሰባ አለቆቹ ኢየሱስ መገደል አለበት ብለው ወሰኑ። ሁሉም በዚህ አልተስማሙም፤ ምክንያቱም ከብዙ ጊዜ በፊት ከኢየሱስ ጋር ሊነጋገር በሌሊት የመጣው ኒቆዲሞስ፥ ዮሴፍ የተባለውም ባለጠጋ የሸንጎ አባል—ስለ እርሱ ኋላ እንሰማለን—ሌሎችም ጥቂቶች ለኢየሱስ ወዳጆች ነበሩ። ነገር ግን ጠላቶቹ እጅግ ብዙዎችና ጨካኞች ስለ ነበሩ እነዚህ ጥቂት የኢየሱስ ወዳጆች ለእርሱ ለመናገር አልደፈሩም። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲገደል ድምፅ ተሰጠ።

ኢየሱስም ሁሉን የሚያውቅ ስለ ሆነ ዕቅዳቸውን አወቀ፤ ጊዜው በደረሰ ጊዜ እንደሚሞትም ያውቅ ነበር። ነገር ግን ከዮርዳኖስ ማዶ በፔሪያ ወንጌሉን ለመስበክ ቃል ገብቶ ስለ ነበረ ያ ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ስለዚህ በምድረ በዳ አጠገብ ኤፍሬም ወደምትባል ከተማ ሄደ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለጥቂት ሳምንታት ተቀመጠ።

ታላቁ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ነበረ፤ ብዙ ሰዎችም ለበዓሉ ራሳቸውን ሊያነጹ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር። ኢየሱስን ይፈልጉ ነበር፤ በቤተ መቅደሱም አደባባዮች ሲመላለሱ እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ነበር፦

«ምን ይመስላችኋል? ኢየሱስ ወደ በዓሉ የሚመጣ ይመስላችኋልን?»

የካህናት አለቆችና የፈሪሳውያን አለቆች ግን ኢየሱስ ያለበትን ስፍራ ያወቀ ሰው ቢኖር ሰዎች ልከው እንዲያስይዙት እንዲነግራቸው ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።


ቀዳሚ ቀጣይ