ምዕራፍ 59 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የሰባዎቹ መላክ
ኢየሱስ በመቅደስ መታደስ በዓል ጊዜ ከኢየሩሳሌም ከወጣ በኋላ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ወንዙንም ተከትሎ ወደ ላይ ወጥቶ ከገሊላ ባሕር በታች ዐሥራ ሁለት ወይም ዐሥራ ሦስት ማይል ያህል ርቆ ወዳለው ስፍራ ደረሰ። ይህም በዮሐንስ የተጠመቀበት፥ ከጥምቀቱም በኋላ ብዙም ሳይቆይ የመጀመሪያዎቹን ተከታዮቹን ያገኘበት ስፍራ ነበር። ይህ ስፍራ በሁለት ስሞች ይጠራ ነበር፤ አንደኛው «ቤተ ራባ» ሲሆን ትርጕሙ «የመሻገሪያው ከተማ» ማለት ነው፤ ይኸውም ሰው ወንዙን በእግሩ ሊሻገር የሚችልበት ስፍራ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ማርታና ማርያም ይኖሩባት ከነበረችው በኢየሩሳሌም አጠገብ ካለችው ከሌላይቱ ቢታንያ ለመለየት «በዮርዳኖስ ማዶ ያለችው ቢታንያ» ይባል ነበር።
ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በቤተ ራባ ከኢየሱስ ጋር ነበሩ፤ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳም ከእርሱ ጋር የመጡ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። ደግሞም ኢየሱስ በዚህ ስፍራ እንዳለ የሚገልጠው ወሬ በገሊላ በተሰማ ጊዜ ብዙ ሌሎች ሰዎች ሊገናኙት ቸኩለው መጡ፤ ስለዚህም ብዙም ሳይቆይ እጅግ ብዙ ተከታዮቹ በዙሪያው ተሰበሰቡ። ኢየሱስ አሁን ፔሪያ ተብሎ ከሚታወቀው ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ካለው ምድር ዳርቻ አጠገብ ነበረ። ይህ ቃል «ማዶ» ማለት ነው፤ ምድሪቱም ይህን ስም ያገኘችው ከይሁዳ አንጻር «በዮርዳኖስ ማዶ» ስለ ነበረች ነው።
ኢየሱስ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ ቢሰብክም ይህችን ምድር ከቶ ጎብኝቶ አያውቅም ነበር፤ በደቡብ በይሁዳ፥ በሰሜን በገሊላ፥ በሰሜን ምሥራቅ በዲካፖሊስ ሰብኮ ነበር፤ ሕዝቡ አይሁድ ሳይሆኑ ሳምራውያን በነበሩባት በሰማርያም እንኳ ሰብኮ ነበር። አሁንም በሌሎቹ የምድሪቱ ክፍሎች ሁሉ እንደ ሰበከ በፔሪያም እየሰበከ ሊያልፍ ቈረጠ። በፔሪያ ግን ጊዜው አጭር መሆን ነበረበት፤ ምክንያቱም እስከ ፋሲካ በዓል ድረስ የቀሩት ሦስት ወሮች ብቻ ነበሩ፤ በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም መገኘት ነበረበት። የፔሪያ ሰዎች ለመምጣቱ እንዲዘጋጁ፥ የሚቻለውንም ያህል ብዙ ሰዎች እርሱን ለመስማት እንዲሰበሰቡ፥ በዚያች ምድር የሚጎበኛቸውን ስፍራዎች መረጠ። ከዚያም ከተከታዮቹ መካከል ሰባ ሰዎችን ጠርቶ ለሕዝቡ እንዲሰብኩና ኢየሱስ በቅርቡ ወደ እነርሱ እንደሚመጣ እንዲነግሩአቸው ሁለት ሁለት አድርጎ ወደ እነዚያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳሉት መንደሮች ላካቸው።
ኢየሱስ ለእነዚህ ሰባ ሰባኪዎች ከጥቂት ወሮች በፊት ዐሥራ ሁለቱን በገሊላ እንዲሰብኩ በላካቸው ጊዜ የሰጣቸውን ያንኑ ትእዛዝ ሰጣቸው። እንዲህም አለ፦
«የገንዘብ ኮሮጆ ወይም የምግብ ከረጢት ወይም ትርፍ ነጠላ ጫማ አትያዙ። በመንገድ ላይ ለሚገናኛችሁ ሰው ሰላምታ ለመስጠት አትቁሙ። ወደ ማናቸውም ቤት በምትገቡበት ጊዜ አስቀድማችሁ ‹ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን!› በሉ። በዚያም የሰላም መንፈስ ያለበት ሰው ቢኖር ሰላማችሁ በእርሱ ላይ ያርፋል፤ ያለዚያ ግን ወደ እናንተ ይመለሳል። በዚያች ከተማ እስካላችሁ ድረስ በዚያው ቤት ተቀመጡ፤ ሠራተኛም ደመወዙ ይገባዋልና ያቀረቡላችሁን ብሉ ጠጡም። ከቤት ወደ ቤት አትዘዋወሩ። ወደምትጎበኙት ማናቸውም ከተማ ሕዝቡ ቢቀበሏችሁ የሚሰጣችሁን ብሉ፤ ድውዮችን ፈውሱ፤ በየስፍራውም ላሉት ሰዎች ‹የእግዚአብሔር መንግሥት በጣም በቅርብ ይመጣል› ማለትን አትርሱ።»
«ወደምትጎበኙት ማናቸውም ከተማ ግን ሕዝቡ ባይቀበሏችሁና መልእክታችሁን ባይሰሙ፥ ወደዚያ ስፍራ አደባባዮች ወጥታችሁ በታላቅ ድምፅ ‹በእግራችን ላይ የተጣበቀውን የከተማችሁን ትቢያ እንኳ ምልክት ይሆንባችሁ ዘንድ እናራግፋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በቅርቡ ወደ እናንተ እንደሚመጣ ይህን እወቁ› ብላችሁ ጩኹ። እላችኋለሁ፥ እግዚአብሔር በሰዎች ላይ በሚፈርድበት ቀን ከዚያች ከተማ ቅጣት ይልቅ የሰዶም ቅጣት ይቀልላል!»
ሰባዎቹ ሰዎች ሁለት ሁለት እየሆኑ ከቤተ ራባ ወጡ፤ እነርሱም ሠላሳ አምስት ጥንዶች ነበሩ። ኢየሱስ ወደ ላካቸው፥ እርሱ ራሱ ኋላ ሊጎበኛቸው ወዳሰባቸው በፔሪያ አገር ወዳሉት ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ሄዱ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት በቅርቡ እንደሚገለጥ የሚናገረውን የኢየሱስን መልእክት ለሕዝቡ ሰጡ፤ በዚህም በየስፍራው ያሉ ሰዎች የኢየሱስን መምጣት እንዲናፍቁ አነቃቁአቸው። ሠላሳ አምስት ጥንድ ሰዎች ብዙ ስፍራዎችን በአጭር ጊዜ ሊጎበኙ ስለሚችሉ ተልእኮአቸው በጥቂት ሳምንታት ተፈጸመ፤ ወደ ቤተ ራባም በተመለሱ ጊዜ ኢየሱስን ገና በዚያው አገኙት።
የትኞቹን ስፍራዎች እንደ ጎበኙ፥ በስሙና እርሱ በሰጣቸው ኃይል ብዙ ፈውስ እንዳደረጉ ለኢየሱስ ነገሩት። በታላቅ ደስታም ለኢየሱስ እንዲህ አሉት፦
«መምህር ሆይ፥ ክፉ መናፍስት እንኳ በስምህ ስንጠቀም ይታዘዙልናል!»
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ «አዎን፥ የክፉ መናፍስት አለቃ ሰይጣን ከሰማይ እንደሚያብረቀርቅ መብረቅ ሲወድቅ አየሁት። አስታውሱ፤ እባቦችንና ጊንጦችን ልትረግጡ፥ የጠላትንም ኃይል ሁሉ ከእግራችሁ በታች ልትጨፈልቁ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፤ የሚጎዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን ክፉ መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ ብቻ ደስ አይበላችሁ፤ ይልቁንስ ስማችሁ እንደ እግዚአብሔር ልጆች በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።»
ኢየሱስ በቤተ ራባ በነበረ ጊዜ ብዙ ሰዎች ሊያዩትና ቃሉን ሊሰሙ ወደ እርሱ መጡ። ይህ ስፍራ መጥምቁ ዮሐንስ ከሦስት ዓመት በፊት ከሰበከባቸው ስፍራዎች አንዱ ስለ ነበረ፥ ኢየሱስን ከዮሐንስ ጋር አወዳደሩት፤ ከእነርሱም ብዙዎቹ እንዲህ አሉ፦
«መጥምቁ ዮሐንስ እግዚአብሔር እንደ ላከው የሚያሳይ ምልክት ሆኖ ምንም ድንቅ ሥራ አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው ተናገረ፤ ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረውም ሁሉ እውነት ነበረ።»
ኢየሱስም በቤተ ራባ በነበረ ጊዜ ብዙ ሰዎች በእርሱ አመኑ፤ ተከታዮቹም ሆኑ።