የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
መልካሙ እረኛ

ምዕራፍ 58 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

መልካሙ እረኛ

ከቤተ መቅደሱ ሕንፃዎች በምሥራቅ በኩል ጣሪያ ያለው፥ በሁለቱም ጐኑ የምሰሶዎች ረድፍ የተሠራለት ረጅም መመላለሻ ወይም ቅስት ያለው መተላለፊያ ነበረ። ይህም «የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ» ይባል ነበር። በምሥራቅ በኩል ወደ ቄድሮን ወንዝ ሸለቆ፥ ከሸለቆውም ማዶ ወደ ደብረ ዘይት ይመለከት ነበር። በምዕራብ በኩል ደግሞ ታላቁን የአሕዛብ አደባባይ ፊት ለፊት ያይ ነበር። ይህ መመላለሻ ርዝመቱ በግምት አንድ ሺህ ጫማ ያህል ነበር።

የመቅደስ መታደስ በዓል በሆነ ጊዜ ክረምት ነበረ፤ ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚህ መመላለሻ ይመላለስ ነበር። በዚያን ጊዜ አይሁድ በዙሪያው ተሰብስበው እንዲህ ብለው ጠየቁት፦

«እስከ መቼ ልባችንን በጥርጣሬ ታቈየዋለህ? በእርግጥ አንተ ክርስቶስ፥ የጥንት ነቢያት አስቀድመው የተናገሩለት የእስራኤል ንጉሥ ከሆንህ በግልጥ ንገረን።»

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑኝም። በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ እርሱ ይመሰክርልኛል፤ እናንተ ግን ከመንጋዬ ስላልሆናችሁ አትሰሙም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም አይጠፉም፤ ማንም ቢሆን ከእጄ ፈጽሞ አይነጥቃቸውም። እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፤ ከአባቴም እጅ ማንም ምንም ሊነጥቅ አይችልም።»

ከዚያም በኋላ ኢየሱስ የ«መልካሙ እረኛ»ን ምሳሌ ወይም ታሪክ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦

«እውነት እላችኋለሁ፥ በበሩ ወደ በጎች በረት የማይገባ፥ ነገር ግን በሌላ በኩል የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው። በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። በረኛውም በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱን በጎች እያንዳንዳቸውን ስለሚያውቃቸው በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ ከበረቱም ወደ ውጭ ይመራቸዋል። በጎቹን ሁሉ ወደ ውጭ ካወጣ በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ ሰው ሲናገራቸው ግን የእንግዳውን ድምፅ ስለማያውቁ አይከተሉትም፤ ይልቁንም ከእርሱ ይሸሻሉ።»

ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን ማለቱ እንደ ሆነ ትርጕሙን አላስተዋሉም። ስለዚህ ገለጠላቸው።

እንዲህም አለ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት በስሜ ሳይሆን የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባልም ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው የሚመጣው ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ነው። እኔ ግን ሕይወት እንዲሆንላቸው፥ እንዲበዛላቸውም መጣሁ።»

«እኔ በር ብቻ ሳልሆን መልካም እረኛም ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል። እረኛ ያልሆነና በጎቹ የእርሱ ያልሆኑ ምንደኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል። ከዚያም ተኵላው ይነጥቃቸዋል፤ መንጋውንም ይበትናል። ምንደኛው ይህን የሚያደርገው ምንደኛ ብቻ ስለ ሆነና ስለ በጎቹ ግድ ስለሌለው ነው።»

«መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ አብ እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቅ፥ እንዲሁ በጎቼን አውቃለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።»

«ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች ደግሞ አሉኝ፤ እነርሱንም ደግሞ ላመጣቸው ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ እንዲሁም አንድ መንጋ፥ አንድ እረኛም ይሆናሉ።»

«ነፍሴን ደግሞ እንዳነሣት ስለማኖራት ስለዚህ አባቴ ይወደኛል። ማንም ከእኔ አልወሰዳትም፤ እኔ ግን በፈቃዴ አኖራታለሁ። ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ። ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። እኔና አባቴ አንድ ነን።»

ይህን ቃል ሲናገር አይሁድ ድንገት ሊወግሩት ብለው እንደ ገና ድንጋይ ያነሡ ጀመር። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦

«ከእግዚአብሔር ዘንድ ብዙ መልካም ሥራ አድርጌላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ሥራዎች ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?»

አይሁድም «ስለ ስድብ ቃል እንጂ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ አንተ ሰው ብቻ ስትሆን ራስህን አምላክ የሚያደርጉ እነዚያን አስፈሪ ቃላት ስለ ተናገርህ ነው!» ብለው መለሱለት።

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ «‹እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ› ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን ሕጉ ‹አማልክት› ካላቸው፥ የእግዚአብሔርም መጽሐፍ እውነትን ይናገር ዘንድ ግድ ከሆነ፥ እግዚአብሔር የቀደሰውና መልእክተኛው አድርጎ ወደ ዓለም የላከው ስለ ራሱ ‹የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ› ቢል ስለ ምን እንዲህ ያለ አስፈሪ ነገር ይሆናል? የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን እኔን ባታምኑ እንኳ ሥራዬ የሚያሳየውን እመኑ። ያን ጊዜ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቃላችሁ፤ ታስተውሉማላችሁ።»

እንደ ገናም ሊይዙት ፈለጉ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አምልጦ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ሄደ።


ቀዳሚ ቀጣይ