ምዕራፍ 57 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
በሰሊሆም መጠመቂያ አጠገብ የነበረው ዕውር
በአንድ ሰንበት ጠዋት፥ ይህም እሑድ ሳይሆን ቅዳሜ፥ የአይሁድ የዕረፍትና ወደ ምኵራብ የመሄጃ ቀን ነበር፤ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቤተ መቅደስ ወዳለው አገልግሎት ሲሄዱ አንድ ዕውር ሰው አጠገብ አለፉ። ይህን ሰው ከዚህ ቀደም አይተውት ነበር፤ ዕድሜውንም ሁሉ ዕውር እንደ ነበረ ያውቁ ነበር። አባቱንና እናቱን እጅግ እያሳዘነ ዓይን ሳይኖረው ወደ ዓለም መጥቶ ነበር፤ ሰዎችም ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ በሚሰጡት ጥቂት ሳንቲም ይኖር ነበር።
አይሁድ በሽታ ሁሉ በአንዳች ኃጢአት ምክንያት ይመጣል ብለው ያምኑ ነበር፤ ሰው ቢታመም ክፉ ሥራ ሠርቶ ስለ እርሱ ስለሚቀጣ ነው፤ ሕፃንም ዕውር ወይም ዲዳ ወይም አንካሳ ሆኖ ቢወለድ፥ አባቱ ወይም እናቱ የእግዚአብሔርን ሕግ ስለ በደሉ መሆን አለበት ይሉ ነበር። የሕግ መምህራን ከነበሩት ጻፎች አንዳንዶቹ ደግሞ እያንዳንዲቱ ነፍስ በምድር ላይ ብዙ ጊዜ ትኖራለች ይሉ ነበር፤ ሰው ሲሞት ነፍሱ በዚያው ቅጽበት ወደ ተወለደ ሌላ ሰውነት ትገባለች፤ አዲስ የተወለደውም ሕፃን ዕውር ወይም በሽተኛ ቢሆን ከዚህ በፊት በነበረው በሌላ ሕይወት በደል ስለ ሠራ ነው ይሉ ነበር። ክርስቶስ ሰዎችን ካስተማረ ወዲህ ከእነዚህ ነገሮች አንዱም ዛሬ የሚታመን የለም፤ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ግን ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል ያምኑባቸው ነበር።
ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ዕውር አጠገብ ሲያልፉ ከእነርሱ አንዱ ኢየሱስን እንዲህ አለው፦
«መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ያደረገው የማን ኃጢአት ነው? የወላጆቹ በደል ነውን? ወይስ የራሱ በደል ነው?»
ኢየሱስም «ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በእርሱ ወይም በአባቱ ወይም በእናቱ በደል አይደለም» ብሎ መለሰ። «የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው። ቀን ሳለ የእግዚአብሔርን ሥራ ልንሠራ ይገባናል፤ ከእንግዲህ ልንሠራ የማንችልባት ሌሊት በቶሎ ትመጣለች። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ ለሰዎችም ብርሃንን እሰጣለሁ።»
ይህንም ብሎ በመሬት ላይ እንትፍ አለ፤ ምራቁንም ከአፈር ጋር ለውሶ ጭቃ አደረገው፤ በሰውዬውም ዓይኖች ላይ ቀባው። ዕውሩንም እንዲህ አለው፦
«አሁን ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ውረድና ታጠብ።»
የሰሊሆም መጠመቂያ ከከተማይቱ በደቡብ ምሥራቅ፥ የቄድሮን ወንዝ ሸለቆና የሄኖም ሸለቆ በሚገናኙበት ስፍራ የነበረ ታላቅ ኵሬ ወይም የውኃ ማጠራቀሚያ ነበር። ወደዚያ ስፍራ ለመሄድ ዕውሩ ሰው በፊቱ ላይ ሁለት ትልልቅ የጭቃ ቅቦች እንዳሉበት ለአምልኮ የሚሄዱትን ሕዝብ ሁሉ እያለፈ የኢየሩሳሌምን ከተማ አቋርጦ መሄድ ነበረበት። ወደ ሰሊሆም መጠመቂያም ወረደ፤ በደረጃዎቹም ወደ ውኃው ወርዶ ጭቃውን ከፊቱ ታጠበ። ወዲያውም ነጭ የነበሩትና የማያዩት ዓይኖቹ በአዲስ ብርሃን አበሩ። ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በሕይወቱም ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት ቻለ!
ወደ አባቱ ቤት ሲሄድ ያዩት ሁሉ ምን ያህል እንደ ተለወጠ አስተዋሉ። ሁሉም ቀድሞ ለምኖ ወደሚቀመጥበት ስፍራ እየዳበሰ የሚሄድ ዕውር አድርገው ያውቁት ነበር። ሰዎቹም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦
«ይህ በመንገድ ይለምን የነበረው ያ ዕውር አይደለምን?»
አንዳንዶቹ «አዎን፥ ይህ ያው ሰው ነው» አሉ።
ሌሎቹ ግን «አይደለም፤ ይህ ያ ሰው ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን ጥቂት የሚመስለው ሌላ ሰው ነው» አሉ።
እርሱም «ያው ሰው እኔ ነኝ» አለ።
«እንግዲያስ እንዴት ማየት ቻልህ?» ብለው ጠየቁት።
እርሱም «ኢየሱስ የሚሉት ሰው» ብሎ መለሰ፥ «ጭቃ አድርጎ ዓይኖቼን ቀባና ‹ወደ ሰሊሆም ሄደህ ዓይኖችህን ታጠብ› አለኝ። ሄጄም ታጠብሁ፤ ማየትም ቻልሁ።»
«ያ የፈወሰህ ሰው ወዴት ነው?» ብለው ጠየቁት።
እርሱም «አላውቅም» ብሎ መለሰ።
ዕውር የነበረውንም ሰው የሕዝቡ መሪዎች ወደ ነበሩት ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። ፈሪሳውያን ሁልጊዜ የኢየሱስ ጠላቶች እንደ ነበሩ አይተናል። ስለዚህ ፈሪሳውያን እንዴት ማየት እንደ ቻለ ደግሞ እንዲነግራቸው ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦
«ኢየሱስ የተባለው ሰው በዓይኖቼ ላይ ጭቃ ቀባ፤ ታጠብሁም፤ አሁንም አያለሁ።»
ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ «ይህ ኢየሱስ የተባለው ሰው ሰንበትን አይጠብቅምና ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም» አሉ።
ጻፎች በሰንበት ቀን ጭቃ መለወስ ሥራ ነው፤ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ መውሰዱም ሸክም መሸከም ነው፤ ሕይወቱን ለማዳን የግድ ካልሆነ በቀር በሰንበት ለታመመ ሰው ማናቸውንም ሕክምና መስጠት ሰንበትን መሻር ነው የሚል ደንብ አውጥተው ነበር። ስለዚህ በእነርሱ ዓይን ኢየሱስ ዕውሩን በመፈወሱ የሰንበትን ደንቦች ከአንድ በሚበልጥ መንገድ ሽሮአል።
ሌሎች ግን «ክፉ ሰው እንዲህ ያሉትን ድንቅ ሥራዎች እንዴት ሊያደርግ ይችላል? ይህ የፈውስ ሥራ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ምልክት አይደለምን?» አሉ።
ስለዚህ ስለ ኢየሱስ ባላቸው አሳብ በመካከላቸው ሁለት ወገን ሆኑ። ዕውሩንም ደግመው ጠየቁት፦
«ዓይኖችህን ስለ ከፈተልህ ስለዚህ ሰው አንተ ምን ትላለህ?»
ሰውዬውም «ከእግዚአብሔር የመጣ ነቢይ ነው እላለሁ» ብሎ መለሰ።
ነገር ግን ከአይሁድ ብዙዎቹ አባቱንና እናቱን እስኪያስጠሩ ድረስ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንደ ተወለደና ማየት እንደ ቻለ አላመኑም።
«ይህ ልጃችሁ ነውን?» ብለው ጠየቁ፤ «ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጅ ይህ ነውን? እንግዲህ አሁን እንዴት ያያል?»
ወላጆቹም «ይህ ልጃችን ነው» ብለው መለሱ፥ «ዕውር ሆኖም ተወለደ፤ ይህን በእርግጥ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ አናውቅም፤ ዓይኖቹንም ማን እንደ ከፈተለት አናውቅም። እርሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው፤ ስለ ራሱ ይናገራል።»
ወላጆቹ እንዲህ ያሉት አይሁድን ስለ ፈሩ ነበር፤ አለቆቹ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ማንም ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት ተስማምተው ነበርና። ስለዚህ ነው «ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት» ያሉት። ፈሪሳውያንም ዕውር የነበረውን ሰው ደግመው አስጠርተው እንዲህ አሉት፦
«ስለ ማየትህ ክብርን ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጥ፤ ይህ ኢየሱስ ክፉ ሰው እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን።»
«ክፉ ሰው መሆኑን እኔ ምንም አላውቅም፤ አንድ ነገር ግን አውቃለሁ፤ ዕውር ነበርሁ፥ አሁን ግን አያለሁ።»
«ምን አደረገህ?» ብለው ጠየቁት። «ዓይኖችህን እንዴት ከፈተ?»
እርሱም «አስቀድሜ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ» ብሎ መለሰ፥ «የምትሰሙም አትመስሉም። ደግሞ ልትሰሙት ስለ ምን ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን?»
በዚያን ጊዜ እጅግ ተቈጥተው እንዲህ አሉት፦ «አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ትሆን ይሆናል፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ ሕጉንም እንጠብቃለን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም!»
ሰውዬውም መልሶ እንዲህ አለ፦ «እንግዲህ ይህ እጅግ ድንቅ ነገር ነው! ከወዴት እንደ ሆነ አታውቁም፤ እርሱ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔር ክፉ ሰዎችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ነገር ግን ማንም እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ያንን ሰው ይሰማዋል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዓይን የከፈተ እንዳለ ማንም ከቶ አልሰማም። ይህ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።»
እነርሱም «አንተ ልታስተምረን ትሞክራለህን?» ብለው መለሱለት። «አንተ በኃጢአት የተወለድህ?»
ከዚያም ከምኵራብ አወጡት፤ በጉባኤዎች እንዳይቀመጥ ወደ ቤተ መቅደስም እንዳይገባ ከለከሉት፤ ከዚያም በኋላ ከእነርሱ አንድ ስንኳ ሊያነጋግረው አልፈለገም። ኢየሱስም ከምኵራብ እንዳወጡት ሰማ፤ ፈልጎም ባገኘው ጊዜ እንዲህ ብሎ ጠየቀው፦
«አንተ በሰው ልጅ ታምናለህን?»
ሰውዬውም «በእርሱ አምን ዘንድ ማን እንደ ሆነ ንገረኝ» አለ።
ኢየሱስም «አይተኸዋል» ብሎ መለሰ፥ «አሁን ከአንተ ጋር የሚናገረውም እርሱ ነው።»
ሰውዬውም «ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ» አለ፤ በፊቱም ተደፋ።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «እንደዚህ ሰው የማያዩና ዕውሮች መሆናቸውን የሚያውቁ እንዲያዩ፥ የሚያዩ የሚመስላቸው ግን ዕውሮች ሆነው እንዲቀሩ፥ ሰዎችን በዚህ ልፈትን ወደዚህ ዓለም መጣሁ።»
ይህን የሰሙት አንዳንድ ፈሪሳውያን ከእግዚአብሔር የተላከውን በኢየሱስ ማየት ስላልቻሉ ይህ ተግሣጽ ለእነርሱ እንደ ሆነ አወቁ። እንዲህም አሉ፦
«እንግዲያስ እኛ ደግሞ ዕውሮች ነን!»
ኢየሱስም «በእውነት ዕውሮች ብትሆኑ የምትጠየቁበት ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር» አለ፤ «አሁን ግን ‹እናያለን› ትላላችሁ፤ ስለዚህ ኃጢአታችሁ በላያችሁ ይኖራል።»
አይሁድም ስለ ኢየሱስ ቃል ደግመው ተለያዩ። አንዳንዶቹ «አብዶአል! ለምን ትሰሙታላችሁ?» አሉ።
ሌሎች ግን «ይህ የእብድ ሰው ቃል አይደለም። ያበደ ሰው የዕውርን ዓይን ሊከፍት ይችላልን?» አሉ።