የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስና ኃጢአተኛዪቱ ሴት

ምዕራፍ 56 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስና ኃጢአተኛዪቱ ሴት

ከዳስ በዓል በኋላ ኢየሱስ በቢታንያ እየኖረ ሌላ በዓል፥ የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል እስኪደርስ ድረስ ሁለት ወር ያህል በኢየሩሳሌም አጠገብ ቈየ። ከዚያ ዘመን ሁለት መቶ ዓመት ያህል አስቀድሞ ቤተ መቅደሱን ጠላቶች ይዘውት ነበር፤ አገልግሎቱንም አስቁመው በሕንጻው ውስጥ ጣዖታትን አቁመው ነበር፤ ሊያረክሱትም ብዙ ነገር አድርገው ነበር። በመጨረሻም ጠላቶቹ ተባረሩ፤ አይሁድም ቤተ መቅደሱን እንደ ገና አነጹ፤ ጣዖታቱንም አጥፍተው የዘወትሩን አገልግሎት ደግመው ጀመሩ። ከዚህም በኋላ ቤተ መቅደሱ እንደ ገና የተከፈተበትን ቀን በየዓመቱ «የመታደስ በዓል» ብለው ያከብሩት ነበር። በዚህም በዓል ቤተ መቅደሱ በየሌሊቱ እጅግ ደምቆ ይበራ ነበር፤ ስለዚህም በዓሉ ደግሞ «የብርሃን በዓል» ይባል ነበር።

ኢየሱስ በዚያ በቈየባቸው ቀኖች ብዙ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄደ «የሴቶች አደባባይ» በተባለው ስፍራ ይቀመጥ ነበር፤ ይህም ስም የተሰጠው በአንድ ወገኑ ሴቶች በመሠዊያው የሚደረገውን አገልግሎት ወደ ታች እያዩ የሚሰግዱበት ሰገነት ስለ ነበረ ነው። በግንቦቹም ላይ ሰዎች ለድሆችና ለቤተ መቅደሱ መደገፊያ ገንዘባቸውን የሚጥሉባቸው የስጦታ ሣጥኖች ስለ ነበሩ «መዝገብ ቤት» ደግሞ ይባል ነበር። እጅግ ሰፊ በሆነውና ጣራ ሳይኖረው ለሰማይ ክፍት በሆነው በዚህ አደባባይ የአይሁድ መምህራን ሕጉን ለማጥናት ተማሪዎቻቸውን ይሰበስቡ ነበር፤ ብዙዎችም ቃሉን ለመስማት ወደ ኢየሱስ ይመጡ ነበር።

አንድ ቀን ጠዋት የኢየሱስ ትምህርት በአደባባዩ በተነሣ ሁካታ ተቋረጠ። የኢየሱስ ጠላቶች የነበሩ አንዳንድ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከሮማውያን ገዦች ጋር ሊያጣሉት አቀዱ። ክፉ ሥራ የሠራችን አንዲት ምስኪን ሴት እየጐተቱ መጡ፤ በኢየሱስም ፊት ለፊት አቆሙአት።

«መምህር ሆይ» አሉት፥ «ይህች ሴት በክፉ ሥራ ተይዛለች። ሙሴም በሕግ እንዲህ ያለውን ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት አዝዞአል፤ አንተስ በእርስዋ ላይ ምን ይደረግ ትላለህ?»

ኢየሱስ ግን ምንም ቢናገር በእርሱ ላይ ችግር ለማምጣት ተስፋ አድርገው ይህን ጥያቄ እንዳመጡለት በሚገባ ያውቅ ነበር። «ነጻ ሆና ትሂድ» ቢል፥ ኢየሱስ ሕግን የሚሽርና ስለ ወንጀል ግድ የሌለው ነው ብለው ያወሩበት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ «ትቀጣ» ቢል፥ ለሮማውያን ገዦች «ይህ ሰው እንደ ፈራጅ ሆኖ ይፈርዳል፤ የእስራኤልም ንጉሥ ነኝ ይላል» ሊሉ ይችሉ ነበር፤ ይህም ሮማውያን እንዲገድሉት ሊያደርጋቸው ይችል ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ምንም ቢል የሚከሱበትን ምክንያት ያገኙ ነበር።

ኢየሱስ ግን ቃላቸውን ያልሰማ መሰለ። ጐንበስ ብሎ በጣቱ በመሬት ላይ ይጽፍ ጀመር። ነገር ግን ያንኑ ጥያቄ ደጋግመው ሲጠይቁት፥ በመጨረሻ ቀና ብሎ ጠላቶቹን ፊት ለፊት ተመለከታቸውና እንዲህ አለ፦

«ከእናንተ መካከል ከቶ በደል ያልሠራ እርሱ አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት።»

ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ መጻፉን ቀጠለ። እነርሱም ጥቂት ጊዜ ዝም ብለው ቆሙ፤ ከዚያም ከሽማግሌዎቹ ጀምሮ እስከ ጐበዞቹ ድረስ በጸጥታ ይወጡ ጀመር። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ኢየሱስ ቀና ብሎ ሴቲቱ ብቻዋን በፊቱ ቆማ አያት። ተነሥቶም እንዲህ አላት፦

«አንቺ ሴት፥ እነዚያ ሰዎች ወዴት አሉ? በደለኛ ነሽ የሚልሽ የለምን?»

እርስዋም «ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ» ብላ መለሰችለት።

ኢየሱስም «እኔም በደለኛ ነሽ አልልሽም። ሂጂ፥ ደግመሽም ኃጢአት አትሥሪ» አላት።

ከዚያም ኢየሱስ ጠላቶቹ ሴቲቱን በማምጣታቸው የተቋረጠውን ትምህርቱን ቀጠለ። እንዲህም አለ፦

«እኔ የዓለም ሁሉ ብርሃን ነኝ። የሚከተለኝና ቃሌን የሚጠብቅ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም።»

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡ ሌላም ብዙ ነገር ተናገረ፤ ከሰሙትም አንዳንዶቹ ከእግዚአብሔር የመጣ መምህር እንደ ሆነ ያምኑ ጀመር። ላመኑትም እንዲህ አላቸው፦

«በቃሌ ጸንታችሁ ብትኖሩ በእውነት ተከታዮቼ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፥ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።»

ሕዝቡም «‹አርነት ትወጣላችሁ› በሚለው ቃል ምን ማለትህ ነው?» አሉ። «እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ከቶም ባሪያዎች አልሆንም። እንዴት አርነት እንወጣለን?»

ኢየሱስም «እውነት እውነት እላችኋለሁ» ብሎ መለሰ፥ «ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ ባሪያ ነው። ባሪያም ሁልጊዜ በቤት አይኖርም፤ ልጅ ግን ቤቱ ስለ ሆነና በዚያም ለመኖር መብት ስላለው ይኖራል። እንግዲህ የሰማያዊው አባት ልጅ ከኃጢአት አርነት ቢያወጣችሁ በእውነት አርነት ትወጣላችሁ።»

ኢየሱስ መናገሩን በቀጠለ ጊዜ የሚሰሙት ሰዎች እጅግ ተቈጡ። በመጨረሻም እንዲህ አለ፦

«ታላቁ አባታችሁ አብርሃም እኔ ወደ ምድር የምመጣበትን ቀን ለማየት ናፈቀ፤ ሲመጣም አየ፥ ደስም አለው።»

አይሁድም «እንዴት? ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ፥ አብርሃም አይቶኛል ትላለህን?» አሉ።

ኢየሱስም «እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ!» ብሎ መለሰ።

በዚህ ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ከእነርሱ ተሰውሮ ከቤተ መቅደስ ወጣ።


ቀዳሚ ቀጣይ