ምዕራፍ 55 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ በዳስ በዓል
ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ የዳስ በዓል እኩሌታው አልፎ ነበር። በአገሩ ሁሉ ስለ እርሱ ይወራ ስለ ነበር ብዙዎች ይፈልጉት ነበር። በበዓሉም ሕዝቡ «የት ነው ያለው? ወደ በዓሉ መጥቶአልን?» ይሉ ነበር።
አንዳንዶቹ «ደግ ሰው ነው» አሉ። ሌሎቹ ግን «አይደለም፤ ሕዝቡን ከሙሴ ሕግ እያሳተ ነውና ደግ ሰው ሊሆን አይችልም» አሉ። ነገር ግን ካህናቱና ጻፎች ማለት የሕግ መምህራን ልባቸውን በኢየሱስ ላይ ያነሣሡባቸውን አለቆችንና የኢየሩሳሌምን ሰዎች ስለ ፈሩ ስለ እርሱ በግልጥ የተናገረ ማንም አልነበረም።
ኢየሱስ በቢታንያ በማርታ ቤት ካለው ማረፊያው በጸጥታ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ፤ በበዓሉም ጊዜ በዚያ የተሰበሰቡትን ሕዝብ ማስተማር ጀመረ፤ በማታም ወደ ቢታንያ ይወጣ ነበር። የሰሙት ሁሉ በቃሉ ተደነቁ፤ በዙሪያውም የሚሰበሰበው ሕዝብ ዕለት ዕለት እየበዛ ሄደ። ሰዎችም እርስ በርሳቸው «ይህ ሰው ይህን ሁሉ እውቀት ከየት አገኘ? በጻፎች ትምህርት ቤት ከቶ አልተማረም» ተባባሉ።
ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ «ትምህርቴ ከላከኝ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሊያደርግ የሚወድ ማንም ቢኖር፥ በእግዚአብሔር ስም እንደምናገር ወይስ ከራሴ እንደምናገር ያውቃል። ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን? ነገር ግን ከእናንተ ሕጉን በቅንነት ለመጠበቅ የሚሞክር አንድ ስንኳ የለም። ሕጉን ለመጠበቅ ብትሞክሩስ ኖሮ ልትገድሉኝ ባልፈለጋችሁ ነበር!»
ሕዝቡም ኢየሱስን «አብደሃል! ማን ሊገድልህ ይፈልጋል?» ብለው መለሱለት።
ኢየሱስ ግን የአለቆቹና በኢየሩሳሌም የነበሩት የብዙዎቹ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና እውነትን እንደ ተናገረ አወቀ። ሕዝቡንም እንዲህ አላቸው፦
«ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤ ከዚያም ወደ ላከኝ እሄዳለሁ። ትፈልጉኛላችሁ፥ አታገኙኝምም፤ እኔ ወደምሄድበትም እናንተ ልትመጡ አትችሉም።»
አይሁድም እንዲህ አሉ፦ «ይህ ሰው እንዳናገኘው ወዴት ሊሄድ ነው? በባዕድ አገር ወደሚኖሩት ወገኖቻችን ሄዶ ባዕዳንን ሊያስተምር ነውን? እንዲህ ያለው ቃል ምን ማለቱ ነው?»
ኢየሱስም ይህን ያለው፥ እነርሱ ከገደሉት በኋላ ከመቃብር ተነሥቶ ዳግመኛ ሕያው ሆኖ፥ እነርሱ ከቶ ሊመጡበት ወደማይችሉት ስፍራ፥ በሰማይ ወዳለው ቤቱ እንደሚመለስ ማለቱ ነበር።
የዳስ በዓል የመጨረሻውና ታላቁ ቀን ደረሰ። በዚያም ቀን እግዚአብሔር በምድረ በዳ ለእስራኤላውያን ከዓለት ውኃ እንደ ሰጣቸው እያሰቡ፥ በታላቅ ደስታ ውኃን ወደ ቤተ መቅደስ አምጥተው አፈሰሱት።
ውኃውም በሚፈስበት መካከል ኢየሱስ ሁሉ እንዲሰሙት በታላቅ ድምፅ ጮኸ፦
«ማንም የተጠማ ቢኖር» አለ፥ «ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ! በእኔ የሚያምን የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል!»
ከሕዝቡም አንዳንዶቹ ይህን በሰሙ ጊዜ «ይህ በእውነት የሚመጣው ነቢይ ነው!» አሉ።
ሌሎችም «ይህ ክርስቶስ፥ የእስራኤል ንጉሥ ነው!» አሉ።
ነገር ግን «አይደለም፤ ይህ ሰው ከገሊላ ይመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ክርስቶስ ከንጉሥ ዳዊት ዘር፥ ከዳዊትም ከተማ ከቤተ ልሔም ይመጣል ይላልና ይህ ንጉሡ ክርስቶስ ሊሆን አይችልም» የሚሉ ነበሩ።
እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ከገሊላ ወደ እነርሱ እንደ መጣ ያውቁ ነበር፤ በቤተ ልሔም እንደ ተወለደና ከዳዊት ንጉሣዊ ዘር እንደ ሆነ ግን አላወቁም። ስለ ኢየሱስም ተለያዩ፤ አንዳንዶቹ ተስፋ የተሰጣቸው ንጉሣቸው እንደ ሆነ አሰቡ፤ ሌሎቹ ግን የሐሰት መምህር ነው ብለው ሊይዙት ፈለጉ። አለቆቹም ሊይዙት ሎሌዎችን ላኩ፤ ነገር ግን እንደ ምን እንደ ሆነ ባይታወቅም አንድ ሰው ስንኳ እጁን ሊጭንበት አልደፈረም።
ሎሌዎቹም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ታላላቆቹ ሰዎች በተመለሱ ጊዜ «ይህን ሰው ስለ ምን ይዛችሁ አላመጣችሁትም?» ተብለው ተጠየቁ።
ሎሌዎቹም «እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም!» ብለው መለሱ።
አለቆቹም «ምን! ይህ ሰው እናንተንም ደግሞ አሳታችሁን?» አሉ። «ከታላላቆቹ ሰዎች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ሕጉን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ግን ምንም አይቈጠርም!»
ከአንድ ዓመት በፊት ከኢየሱስ ጋር ለመነጋገር በሌሊት የመጣው ከአለቆቹ አንዱ ኒቆዲሞስ እንዲህ አላቸው፦
«ሕጋችን አንድን ሰው አስቀድሞ የሚለውን ሳይሰማ ያደረገውንም ሳያውቅ በደለኛ አድርጎ እንዲቈጠር በእርግጥ አይፈቅድም!»
እነርሱም መልሰው «እንደዚህ ሰው ተከታዮች ሁሉ አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን?» አሉት። «ፈልግ፥ ከገሊላም ነቢይ ከቶ እንዳይነሣ ታገኛለህ።»
በማታም ሕዝቡ ሁሉ ወደየቤታቸው ሄዱ፤ ኢየሱስም ደብረ ዘይትን ተሻግሮ በቢታንያ ወዳሉት ወዳጆቹ ሄደ።