የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ለገሊላ የተደረገ ስንብት

ምዕራፍ 52 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ለገሊላ የተደረገ ስንብት

ኢየሱስ ገና በቅፍርናሆም ሳለ የዓመቱ የመከር ወራት ደረሰ፤ ከእርሱም ጋር የአይሁድ የድንኳን በዓል ወይም የዳስ በዓል የሚከበርበት ጊዜ ቀረበ። በመጽሐፍ ቅዱስ «ዳስ» የሚለው ቃል ሁልጊዜ «ድንኳን» ማለት ነው። ይህ በዓል «የድንኳን በዓል» የተባለው በየዓመቱ ሊያከብሩት ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡ ሰዎች ከለመለመ ቅርንጫፍ በተሠሩ ትንንሽ ድንኳኖች ወይም ጎጆዎች ውስጥ አንድ ሳምንት ስለሚኖሩ ነው፤ ይህንም የሚያደርጉት ከብዙ ዘመን በፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ ከቦታ ወደ ቦታ እየተጓዙ በድንኳን የኖሩባቸውን አርባ ዓመታት ለማሰብ ነው።

የዮሴፍና የማርያም ልጆች የሆኑት የኢየሱስ ታናናሽ ወንድሞች ኢየሱስ በቅፍርናሆም እንዳለ ሰሙ፤ ሊያዩትም መጡ። እነዚህ የኢየሱስ ወንድሞች ኋላ ከተከታዮቹ መካከል ቢገኙም፥ በዚያን ጊዜ ግን ንጉሣቸውና መድኃኒታቸው እንደ ሆነ ገና አላመኑበትም ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን እንዲህ አሉት፦

«ደቀ መዛሙርትህ የምትሠራውን በዚያ እንዲያዩ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ለምን አትሄድም? ሊታወቅ የሚወድድ ማንም ከሕዝብ ተለይቶ አይኖርም። እነዚህን ታላላቅ ሥራዎች ልትሠራ የምትችል ከሆንህ ራስህን ለዓለም ግለጥ።»

ኢየሱስም «ጊዜዬ ገና አልደረሰም» አለ፤ «ጊዜያችሁ ግን ሁልጊዜ የተዘጋጀ ነው። ዓለም እናንተን አይቃወማችሁም፤ እኔን ግን ይቃወመኛል፤ በክፉ ሥራው ላይ እናገራለሁና። እናንተ ወደ በዓሉ ውጡ፤ እኔ ጊዜዬ ገና ስላልደረሰ አሁን ወደዚህ በዓል አልወጣም።»

ኢየሱስ ወንድሞቹ እንኳ ቢሆኑ በእርሱ የማያምኑ ሰዎችን በበዓሉ ላይ ጓደኞቹ ሊያደርጋቸው አልፈለገም። ስለዚህ ወንድሞቹ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ እርሱ በገሊላ ጥቂት ጊዜ ቈየ። ከቅፍርናሆም ከተማ ከመሄዱ በፊት ለሕዝቧና በአጠገቧ ላሉት ከተሞች ሰዎች የመጨረሻ ጥሪና ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ከቅፍርናሆም ጥቂት ማይል ብቻ በምትርቀው በኮራዚ ለሚኖሩ፥ አምስት ማይል ርቃ በሐይቁ ራስ ላይ በምትገኘው በቤተ ሳይዳም ለሚኖሩ ተናገረ። ለእነዚህ ከተሞች እንዲህ አለ፦

«ወዮልሽ ኮራዚ! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ከብዙ ጊዜ በፊት ማቅ ለብሰው በራሳቸውም ላይ አመድ ነስንሰው እያለቀሱ ከኃጢአት ወደ እግዚአብሔር በተመለሱ ነበር! እላችኋለሁ፥ እግዚአብሔር አገሮችን ሊፈርድ በሚመጣበት ጊዜ ከጢሮስና ከሲዶና ይልቅ በኮራዚና በቤተ ሳይዳ ላይ ይከብዳል። አንቺም ቅፍርናሆም ሆይ፥ እስከ ሰማይ ከፍ ትያለሽን? አይደለም፤ ወደ ሞት ትወርጃለሽ። በአንቺ የተደረገው ታላቅ ሥራ በሰዶም ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ያች ከተማ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ቅፍርናሆም ሆይ፥ በእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል!»

በዚያው ጊዜ ኢየሱስ ደግሞ እነዚህን ቃሎች ተናገረ፦

«አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከተማሩ ሰዎች ሰውረህ በመንፈሳቸው እንደ ሕፃናት ለሆኑት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን፥ አባት ሆይ፥ አንተ የመረጥኸው መንገድ ይህ ስለ ሆነ አመሰግንሃለሁ።»

«ሥልጣን ሁሉ ከአብ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን ፈጽሞ የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን ፈጽሞ የሚያውቅ የለም።»

«እናንተ ደካሞች በመከራችሁም ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። እኔ የምሸከመውን ቀንበር በላያችሁ ተሸከሙ፥ እንዴት እንደምትኖሩም ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።»

ኢየሱስ በእነዚህ ቃሎች ቅፍርናሆምንና ገሊላን ለመጨረሻ ጊዜ ተወ።


ቀዳሚ ቀጣይ