ምዕራፍ 53 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
በሰማርያ በኩል ማለፍ
ለዳስ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡት አብዛኞቹ ሰዎች ቅፍርናሆምን ከለቀቁ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጕዞውን ጀመረ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ያዩት ሁሉ፥ ደቀ መዛሙርቱም እንኳ፥ አሁንስ በእርግጥ ዙፋኑን ሊይዝና የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሕዝቡን ሊገዛ መሄዱ ነው ብለው አሰቡ።
ሊነሡ ሲሉ ከሕግ መምህራን አንዱ የሆነ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ እንዲህ አለ፦
«መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ።» ኢየሱስን በመከተሉ በመንግሥቱ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ የሚያገኝ መስሎት ነበር። ኢየሱስ ግን ይህ ሰው የሚከተለው ለጥቅም ብቻ እንደ ሆነ አየ። እንዲህም አለው፦
«እኔን በመከተል ምንም አታተርፍም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ፥ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ የለውም።»
ኢየሱስ ሌላውን ሰው «ተከተለኝ!» አለው። ሰውየውም «አስቀድሜ ሄጄ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ» ብሎ መለሰ።
ኢየሱስም ለዚህ ሰው «ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ፤ አንተ ግን ሂድና የእግዚአብሔርን መንግሥት ወሬ በየስፍራው አውራ» አለው።
ኢየሱስ ይህን ሲል፥ እንደ ሙታን መቅበር ያሉ ጉዳዮችን ሕይወት የሚሰጠውን እውነት የማያውቁ ሌሎች ሰዎች እንኳ ሊፈጽሙት ይችላሉ ማለቱ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ይህ ሰው ወዲያውኑ ሄዶ ወንጌሉን እንዲሰብክ ፈለገ።
ሌላም ሰው ኢየሱስን «እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ሄጄ በቤቴ ያሉትን ወዳጆቼን ‹ደኅና ሁኑ› እንድል ፍቀድልኝ» አለው።
ኢየሱስም «እጁን በማረሻ ላይ ከጫነ በኋላ ወደ ኋላ የሚመለከት ሁሉ ለእግዚአብሔር መንግሥት አይጠቅምም» ብሎ መለሰ።
ኢየሱስ ለሥራው ሁሉን ትተው እንዲከተሉትና እንዲያገለግሉት ልባቸው ያልተከፈለ ሰዎችን ፈለገ።
ኢየሱስ በዚህ ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርገው ጕዞ ሰዎች ዘወትር በሚሄዱበት በዮርዳኖስ ሸለቆ መንገድ አልወረደም። በዚህ ጊዜ በሰማርያ በኩል ለማለፍ ቈረጠ፤ ምናልባት ብዙ ሕዝብ አብሮት እንዲሄድ ስላልፈለገ ይሆናል፤ ከአይሁድም በሰማርያ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ።
ወደ አንዲት የሳምራውያን መንደር በቀረበ ጊዜ ማረፊያ እንዲፈልጉለት ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹን ወደዚያ ላከ። የሳምራውያን ሕዝብ ግን ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱ አይሁድ መሆናቸውን ስላዩ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ መንደራቸው እንዲገቡ አልፈቀዱም። ሳምራውያንና አይሁድ እርስ በርሳቸው ይጠላሉ፤ አንዳቸው ለሌላው ደግነት አያሳዩም ነበር።
ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ያዕቆብና ዮሐንስ መምህራቸውን በከለከሉት በእነዚህ ሰዎች እጅግ ተቈጡ። እንዲህም አሉት፦
«ጌታ ሆይ፥ ነቢዩ ኤልያስ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ አውርደን ያችን ክፉ መንደር እናቃጥልን?»
ኢየሱስ ግን «መንፈሳችሁ ትክክል አይደለም። እኔ የመጣሁት የሰዎችን ሕይወት ላድን እንጂ ላጠፋ አይደለም። ወደ ሌላ መንደር እንሂድ» አላቸው።
ገና በገሊላና በሰማርያ ድንበር ላይ ሳለ ወደ አንዲት መንደር ሲገባ አስከፊው የለምጽ በሽታ የያዛቸው ዐሥር ሰዎች አገኙት። ለምጻሞች ወደ ሰዎች መቅረብ አይፈቀድላቸውም ነበርና በሩቅ ቆሙ፤ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ እንዲህ አሉ፦
«ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን!»
ኢየሱስም «ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ» ብሎ መለሰ።
በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንደ ለምጽ ያለ በሽታ ያለበትና በቆዳው ላይ ሽፍታ የወጣበት ሰው የሚሄድበት አንድ ክፍል ነበረ። በዚያ ክፍል ለተወሰነ ጊዜ ይቈያል፤ በሽታውም ለምጽ እንዳልሆነ ከታወቀ የተወሰኑ መሥዋዕቶችንና መታጠብን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቤቱ ሄዶ ከሰዎች ጋር እንዲኖር ይፈቀድለት ነበር። እነዚህ ሰዎች ወደ ቤተ መቅደሳቸው ተነሡ፤ አይሁድ የሆኑት በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ፥ ሳምራውያን የሆኑትም በሴኬም ከተማ አጠገብ በገሪዛን ተራራ ላይ ወዳለው ቤተ መቅደሳቸው ሄዱ። ሲሄዱም፥ በመሄዳቸውም በኢየሱስ ያላቸውን እምነት ሲያሳዩ፥ ድንገት ለምጻቸው እንደ ለቀቀና ፈጽመው እንደ ዳኑ አገኙ።
ከእነዚህ ዐሥር ሰዎች ዘጠኙ ከተፈወሱ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መንገዳቸውን ቀጠሉ። ከእነርሱ አንዱ ግን ከእንግዲህ ለምጻም እንዳልሆነ ባወቀ ጊዜ ቆመ፤ በታላቅ ድምፅም እግዚአብሔርን አከበረ፤ ወደ ኢየሱስ እግርም ሮጦ በፊቱ በግንባሩ ወደቀ፤ ስለ መዳኑም አመሰገነው። ይህ ሰው ሳምራዊ ነበረ።
ኢየሱስም «ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? እግዚአብሔርን ሊያመሰግን የተመለሰ አንድ ብቻ ነውን? እርሱም ደግሞ ከልዩ ወገን የሆነው?» አለ።
ኢየሱስም ይህን አመስጋኝ ሳምራዊ «ተነሣና መንገድህን ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል» አለው።