ምዕራፍ 51 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
ወደ ቅፍርናሆም የመጨረሻው ጕብኝት
ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ በገሊላ ሲያልፍ፥ በዚያ ምድር ከዚያ በኋላ ድንቅ ሥራዎችን ሊሠራ ወይም በሕዝብ ፊት ሌላ ትምህርት ሊያስተምር አልፈለገም። ብዙ ሕዝብ በዙሪያው እንዲሆን አልወደደም፤ ከእነርሱ ተለይቶ ከመወሰዱ በፊት ሊነግራቸው የሚገባ ብዙ ነገር ነበረና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻውን ለመሆን ወደደ።
ባለፈው ዓመት መኖሪያው ወደ ነበረችው ወደ ቅፍርናሆም ሲሄዱ፥ ደቀ መዛሙርቱ በመንገድ ሲሄዱ እርስ በርሳቸው ሲከራከሩና ሲጣሉ አየ። እርሱ ሁሉን ነገር ያውቅ ነበርና እርስ በርሳቸው የሚሉትን በሚገባ አወቀ፤ በዚያን ጊዜ ግን ምንም አልተናገረም።
ወደ ቅፍርናሆምም መጣ፤ በዚያን ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ሳይከተለው ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ነበር። በማታም በቤት ውስጥ በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ እንዲህ አላቸው፦
«ዛሬ በመንገድ ስንሄድ የምትነጋገሩበት ነገር ምን ነበር?»
ደቀ መዛሙርቱም ጥቂት አፍረው እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ መጀመሪያም ምንም አልተናገሩም። በመጨረሻ ከእነርሱ አንዱ እንዲህ አለ፦
«በመንግሥትህ ውስጥ ከእኛ ማን ፊተኛውን ስፍራ ይይዛል ብለን እርስ በርሳችን እንጠያየቅ ነበር።»
ኢየሱስ መከራ መቀበልና መሞት እንዳለበት ለእነዚህ ሰዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ቢነግራቸውም፥ አላመኑትም ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በመንገድ ላይ እንደ ሆነ አዩ፤ እንደ እነዚያም በእርሱ እንዳመኑት ሕዝብ ሁሉ፥ ወደዚያች ከተማ በደረሰ ጊዜ መንግሥቱን ይዞ እንደሚገዛ አሰቡ፤ ስለዚህም ከደቀ መዛሙርቱ እያንዳንዱ ከዙፋኑ አጠገብ ለራሱ የሚሆን ስፍራ ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስም፥ «ፊተኛው ስፍራ!» ብሎ መለሰ። «ከእናንተ በመንግሥተ ሰማያት ፊተኛ ሊሆን የሚወድ ቢኖር፥ ያ ከሁሉ በኋላ ይሁን፥ ሌሎቹንም ሁሉ ያገልግል!»
አንድ ትንሽ ሕፃን በአጠገቡ ይጫወት ነበር፤ ሕፃናት ኢየሱስን ከቶ አይፈሩትም ነበርና፥ ከእርሱም ጋር መሆንን ይወዱ ነበር። ኢየሱስም እጁን ወደ እርሱ ዘርግቶ ሕፃኑን በእቅፉ ወሰደው፥ ወደ ራሱም አስጠጋው። ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፦
«እላችኋለሁ፥ መንፈሳችሁን ካልለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም! ከእናንተ ለራሱ ታላቅ ነገርን ሳይፈልግ እንደዚህ ሕፃን ትሑትና የዋህ የሚሆን ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ የሚሆን እርሱ ነው። ትንሽ ሕፃንም እንኳ ቢሆን ከተከታዮቼ አንዱ እንዲሆን የሚረዳ ሁሉ እኔን ይረዳል። ነገር ግን ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እኔን እንዳይከተል ወጥመድ ወይም ማሰናከያ በመንገዱ የሚያኖር ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢጣል ይሻለው ነበር! ሰዎችን ከእግዚአብሔርና ከመዳን ለሚያርቁ ወጥመዶችና እንቅፋቶች ለዓለም ወዮላት! እነዚህ ወጥመዶችና እንቅፋቶች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ ለሚያኖራቸው ሰው ወዮለት!»
«እጅህ ወይም እግርህ ከእግዚአብሔር እያራቀ ወጥመድ ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው። ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም ሞት ከምትሄድ፥ ጕንድሽ ሆነህ፥ አንድ እጅ ብቻም ኖሮህ ወደ ሕይወት ብትገባ ይሻልሃል። ዓይንህም እግዚአብሔርን እንድትተው የሚያደርግህ ቢሆን፥ አውጥተህ ጣለው። ሁለት ዓይን ኖሮህ ከምትጠፋ፥ አንድ ዓይን ብቻ ኖሮህ ብትድን ይሻልሃል።»
«እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከቶ እንዳትንቁ ወይም እንዳታቃልሉ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ዘወትር ያያሉ እላችኋለሁና።»
ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ዮሐንስ እንዲህ አለ፦
«መምህር ሆይ፥ ከተከታዮችህ ያልሆነ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ስላልሆነም ስምህን እንዳይጠራ ከለከልነው።»
ኢየሱስም፥ «አትከልክሉት፤» አለ፥ «በስሜ የኃይል ሥራ ሠርቶ ደግሞ በእኔ ላይ ክፉ መናገር የሚችል ማንም የለምና። የማይቃወመን ከእኛ ጋር ነው። ስለ ክርስቶስ ስለ ሆናችሁ አንድ ሰው ጽዋ ውኃ እንኳ ቢያጠጣችሁ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ያ ሰው ዋጋው አይጠፋበትም።»
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ የበደሏቸውን ሰዎች እንዴት እንዲይዙ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦
«ወንድምህ ቢበድል፥ ሂድና አንተና እርሱ ብቻችሁን ሳላችሁ ስለ ነገሩ ንገረው። ቢሰማህ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው። ባይሰማህ ግን፥ በማንኛውም ነገር ቢያንስ ሁለት ምስክሮች እንዲኖሩ፥ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ከአንተ ጋር ውሰድና እንደ ገና ተነጋገረው። እነዚህንም ባይሰማ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ቤተ ክርስቲያንንም ደግሞ ባይሰማ፥ ከእርሱ ጋር ምንም ግንኙነት አይኑርህ፤ ሕዝቡ ለሮማውያን ከአይሁድ ግብር የሚሰበስቡትን እንደሚቈጥሩ እንደ እንግዳ ቍጠረው።»
«ደቀ መዛሙርቴ ሆይ፥ እላችኋለሁ፥ በምድር የምትከለክሉት ሁሉ በሰማይ ባሉት ዘንድ የተከለከለ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈቅዱት ሁሉ በሰማይ ባሉት ዘንድ የተፈቀደ ይሆናል። ደግሞ ሌላ ነገር እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በጸሎት በሚለምኑት ነገር ሁሉ በምድር ቢስማሙ፥ በሰማያት ያለው አባቴ ያደርግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።»
ከዚያም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ አንድ ጥያቄ ጠየቀው። ጥያቄውም ይህ ነበር፦
«ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ይሁንን?»
ኢየሱስም፥ «ሰባት ጊዜ?» አለ። «አይደለም፤ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እላለሁ! ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹ ያለባቸውን ዕዳ እንዲከፍሉት የወደደ ንጉሥን ትመስላለች። ሒሳባቸውን መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ፥ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚበደር አንድ ባሪያ ወደ እርሱ ቀረበ። ያንን ዕዳውን ሊከፍል ምንም አልቻለም፤ ጌታውም እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ ተሽጦ ለዕዳው እንዲከፈል አዘዘ። ባሪያውም በፊቱ በግንባሩ ወድቆ፥ ‹ጌታዬ ሆይ፥ ብቻ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ› አለው። ጌታውም ያን ያህል ታላቅ ዕዳ ከቶ ሊከፍል እንደማይችል አወቀ፤ ስለዚህ ራራለትም፤ የነበረበትን ዕዳ ሁሉ ተወለትና በነጻ አሰናበተው።»
«ያ ባሪያ ግን ሲሄድ፥ ጥቂት ዕዳ፥ ዐሥራ አምስት ዶላር ያህል ብቻ የሚበደረውን ከባልንጀሮቹ ባሪያዎች አንዱን አገኘ። ይዞም አንገቱን አንቆ፥ ‹ያለብህን ክፈለኝ!› አለው። ሰውየውም በምድር ላይ ወድቆ ምሕረትን ለመነው፤ ‹ታገሠኝ፥ ጥቂት ጊዜ ጠብቀኝ፥ ያለብኝንም ሁሉ እከፍልሃለሁ› ብሎ ጮኸ። እርሱ ግን ሊምረው አልወደደም፤ ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አስገባው።»
«ሌሎቹ ባሪያዎችም ያ ባሪያ ይህን ሰው ወደ ወኅኒ ሲያስገባው ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ያደረገውንም ለንጉሡ ነገሩት። በዚህም ነገር ንጉሡ እጅግ ተቈጣ። ያንን ጨካኝ ባሪያ አስጠርቶ፥ ‹አንተ ክፉ ባሪያ! ምሕረትን በለመንኸኝ ጊዜ ታላቁን ዕዳህን ሁሉ ተውሁልህ፤ አሰናበትሁህም! እኔ ለአንተ ያደረግሁትን ቸርነት አንተ ደግሞ ለባልንጀራህ ባሪያ ልታደርግለት አይገባህም ነበርን?› አለው። ጌታውም እጅግ ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ በጨለማ እስር ቤት እንዲጠበቅ ለጠባቂው አሳልፎ ሰጠው። እንዲሁም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን በፍጹም ልባችሁ ይቅር ባትሉ፥ የሰማዩ አባቴ እንዲሁ ያደርግባችኋል።»
ኢየሱስ በዚህ ጊዜ በቅፍርናሆም ሳለ፥ ከአይሁድ የቤተ መቅደሱን ግብር የሚሰበስበው ሹም ወደ ጴጥሮስ መጥቶ እንዲህ አለው፦
«መምህራችሁ የቤተ መቅደሱን ግብር አይከፍልምን?»
ጴጥሮስም፥ «አዎን፥ ይከፍላል፤» ብሎ መለሰ።
ጴጥሮስ ግን ወደ ቤት በገባ ጊዜ፥ እርሱ ገና አንድ ቃል ሳይናገር ኢየሱስ አስቀድሞ እንዲህ አለው፦
«ስምዖን ሆይ፥ ንገረኝ፥ የዚህ ዓለም ነገሥታት ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸው ወይስ ከእንግዶች?»
ጴጥሮስም፥ «ከእንግዶች፤» ብሎ መለሰ።
«እንግዲያስ የገዛ ወገናቸው ከግብር ነጻ ናቸው፥ አይደሉምን? እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ከሚከፈለው ግብር ነጻ ልንሆን ይገባናል። ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ ወደ ባሕር ሂድ፥ መንጠቆም ጣል፥ መጀመሪያ ተይዞ የሚወጣውንም ዓሣ ያዝ፤ አፉንም ስትከፍት በውስጡ የብር ገንዘብ ታገኛለህ። እርሱን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ለግብር ሰብሳቢዎቹ ስጣቸው።»