ምዕራፍ 50 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ
ዲዳ መንፈስ ያደረበት ልጅ
ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርቱ በተራራው ግርጌ ወዳለው መንደር በደረሱ ጊዜ፥ በሌሎቹ ዘጠኝ ደቀ መዛሙርት ዙሪያ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አገኙ፤ ከአይሁድም የሕግ መምህራን የሆኑ አንዳንድ ጻፎች ከእነርሱ ጋር በብርቱ ይከራከሩ ነበር። ከትናንቱ ሌሊት ክብር ጥቂቱ ገና በኢየሱስ ፊት ላይ ነበር፤ ሕዝቡም ወደ እርሱ ባዩት ጊዜ እጅግ ተደነቁ፤ በፊቱም ሰገዱለት።
ከሕዝቡም መካከል ፊቱ ታላቅ ጭንቅ እንዳለበት የሚያሳይ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ። በኢየሱስም ፊት ተንበርክኮ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦
«መምህር ሆይ፥ ዲዳ ያደረገው ክፉ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አመጣሁ። እባክህ ማረውና ፈውሰው፤ አንድ ልጄ ነውና። ብዙ ጊዜ መንፈሱ ይይዘውና ወደ መሬት ይጥለዋል። አረፋ ያስደፍቀዋል፤ ጥርሱንም ያፋጨዋል። እየከሳ ይሄዳል፤ ርዳታም ካልመጣለት ይሞታል ብዬ እፈራለሁ። አንተን አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ወደዚህ አመጣሁት። አንተ ግን አልነበርህም፤ እነዚህን ደቀ መዛሙርትህን ለመንሁ። ክፉውን መንፈስ ሊያወጡት ሞከሩ፥ ነገር ግን አልቻሉም። አሁን አንተ ስለ መጣህ እባክህ አትረዳኝምን?»
ኢየሱስም፥ «እናንተ የማታምኑና ከእግዚአብሔር ፊታችሁን የምትመልሱ ሰዎች ሆይ፥» አለ፥ «እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደ እኔ አምጣው።»
ልጁንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ ልጁ ግን ኢየሱስን ገና እንዳየው ወዲያው ክፉው መንፈስ አንፈራገጠው። በምድርም ላይ ወደቀ፤ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠና እየተናጠ አረፋ እያስደፈቀ ይንከባለል ነበር።
ኢየሱስም የልጁን አባት፥ «ይህ ከደረሰበት ምን ያህል ጊዜ ነው?» ብሎ ጠየቀው።
ሰውየውም፥ «ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤» ብሎ መለሰ፥ «ብዙ ጊዜም ሊገድለው ምንም ያህል ሲቀረው ወደ እሳትና ወደ ውኃ ጥሎታል። አንዳች ልታደርግ ብትችል ግን ሁለታችንንም ራራልንና እርዳን።»
ኢየሱስም የሰውየውን ቃል አንሥቶ፥ «‹ብትችል!›» አለ። «ለሚያምን ሁሉ ይቻላል መሆኑን አታውቅምን?»
የልጁም አባት፥ «አምናለሁ፤» ብሎ ጮኸ፤ «ጌታ ሆይ፥ አለማመኔን እርዳው!»
ኢየሱስ ሕዝቡ በፍጥነት በዙሪያው እንደሚሰበሰብ አይቶ ክፉውን መንፈስ ተናገረው።
«አንተ ደንቆሮና ዲዳ መንፈስ፥» አለ፥ «ከዚህ ልጅ ወዲያው እንድትወጣ፥ ዳግመኛም እንዳታስቸግረው አዝሃለሁ!»
ክፉውም መንፈስ በታላቅ ጩኸት ልጁን በብርቱ ሥቃይ አንፈራግጦ ተለየው። ልጁም እንደ በድን ሆኖ በምድር ላይ ተጋደመ። እንዲያውም በአጠገቡ የቆሙ ብዙዎች ባዩት ጊዜ፥ «ልጁ በእርግጥ ሞቶአል!» አሉ።
ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ ከወደቀበት ከምድር አነሣው። ልጁም ቆመ፤ ከክፉው መንፈስ ተፈትቶና መናገርም ችሎ ደኅና ሆኖ ሄደ።
ኢየሱስ በቤት ውስጥ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻውን በሆነ ጊዜ፥ «ክፉውን መንፈስ ከልጁ እኛ ልናወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?» ብለው ጠየቁት።
«ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው። እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ብቻ ቢኖራችሁ ይህን ተራራ፥ ‹ከዚህ ስፍራ ወደዚያ እለፍ› ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።»
ደግሞም፥ «እንዲህ ያለው ክፉ መንፈስ ከብዙዎቹ ይልቅ ለማውጣት ይከብዳል። በልዩ ጸሎት ብቻ ይወጣል፤» አለ።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በተራራው ግርጌ ያለውን ያንን ስፍራ ትቶ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደቡብ መራቸው። እነርሱም እርሱ አሁን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ እንደሚሄድ አዩ፤ በዚያም ዙፋኑንና መንግሥቱን እንደሚያቆም እርግጠኞች ሆኑ። ኢየሱስ ግን የሚያስቡትን አውቆ እንዲህ አላቸው፦
«ቃሌን በጥንቃቄ ስሙ። የሰው ልጅ በጠላቶቹ እጅ አልፎ ይሰጣል። ይገድሉታል፤ ከተገደለም ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ሕይወት ይነሣል።»
ደቀ መዛሙርቱ ግን እንደሚሞት ሊያምኑ ስላልፈለጉ ይህን ቃል ሊያስተውሉ አልቻሉም፤ የዚህም ንግግር ትርጉም ምን እንደ ሆነ ሊጠይቁት ፈሩ።