የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በተራራው ላይ የታየው ራእይ

ምዕራፍ 49 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

በተራራው ላይ የታየው ራእይ

አንድ ጊዜ ኢየሱስ በምድሪቱ በሩቅ ሰሜን ባለው በኤርሞን ተራራ ግርጌ ካሉት መንደሮች በአንዲቱ ሲቀመጥ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን፥ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም፥ ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራው ወጣ። ተራራውን የወጡት ከሰዓት በኋላ ነበር፤ ሌሊትም በገባ ጊዜ እርሱ ገና በጸሎት ላይ ነበር። ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተራራውን በመውጣታቸው ደክመው ስለ ነበር ለጥቂት ጊዜ እንቅልፍ ወሰዳቸው። በነቁም ጊዜ በጌታቸው ላይ በመጣው ለውጥ እጅግ ተደነቁ።

ሌሊት ቢሆንም፥ የኢየሱስ ፊት በቀትር እንዳለች ፀሐይ ሲበራ አዩ፤ ክብሩም እጅግ የሚያንጸባርቅ ስለ ነበር ወደ እርሱ ሊመለከቱ አልቻሉም። ልብሱም ደግሞ ነጭና የሚያብረቀርቅ ሆነ። ፊቱ ብቻ ሳይሆን እጆቹም እግሮቹም፥ ሰውነቱም ሁሉ በልብሱ ውስጥ ሆኖ በብርሃን ያበራ ነበር።

በዚያም ክብሩ ውስጥ ከኢየሱስ አጠገብ ቆመው ሁለት ሰዎችን አዩ፤ እነርሱም ከብዙ ዘመን በፊት በምድር ላይ የኖሩና አሁን በዚህ ዓለም የሌሉ ነበሩ። ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንዳወቋቸው አልተነገረንም። ምናልባት እግዚአብሔር ያንን እውቀት በድንገት በልባቸው አብርቶላቸው ይሆናል፤ ወይም የሁለቱን ሰዎች ንግግር ሲሰሙ ከቃላቸው ማን መሆናቸውን አውቀው ይሆናል። አንዱ እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣውና በናባው ተራራ ላይ የሞተው ታላቁ ነቢይ ሙሴ ነበር፤ ሁለተኛውም ክፉውን ንጉሥ አክዓብን በድፍረት የተናገረውና በእሳት ሰረገላ ወደ ሰማይ የተወሰደው ነቢዩ ኤልያስ ነበር። ሁለቱም ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ከምድር ያለፉ ነበሩ።

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሲመለከቱና ሲያዳምጡ፥ እነዚህ የጥንት ዘመን ሁለት ነቢያት የሚናገሩትን ሰሙ። ከኢየሱስ ጋር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ሞቱ ይነጋገሩ ነበር። እንግዲህ እነዚህ ያለፈው ዘመን ሁለት ታላላቅ ሰዎች ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሊነግራቸው የሞከረውንና እነርሱም ለማመን የዘገዩበትን ነገር፥ እርሱ በቅርብ እንደሚሞት፥ አስቀድመው ያውቁ ነበር!

ጴጥሮስ ሁልጊዜ ለመናገር የሚቸኩል ነበር፤ አሁንም የገዛ ቃሉ ምን ማለት እንደ ሆነ በደንብ ሳያስተውል ተናገረ።

«መምህር ሆይ፥» አለ፥ «እዚህ መቀመጥ ለእኛ መልካም ነው። ብትፈቅድ፥ በዚህ ሦስት ዳሶች እሠራለሁ፤ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድም ለኤልያስ።»

ሁለቱ ነቢያት፥ ሙሴና ኤልያስ፥ በምድር ላይ ለመኖር የተመለሱ መሰለው፤ ዳሶችም ቢሠሩላቸው በዚያ ተራራ ላይ የሚኖሩ መሰለው።

ጴጥሮስ ገና ሲናገር ብሩህና የከበረ ደመና ሁሉንም ጋረዳቸው፤ ኢየሱስንም ሁለቱንም ነቢያት ሦስቱንም ደቀ መዛሙርት ሸፈነ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደመናው በዙሪያቸው እንዳለ ባዩ ጊዜ ፍርሃት ሞላባቸው። ከደመናውም የእግዚአብሔር ድምፅ እንዲህ ሲል በሰሙ ጊዜ የባሰ ፍርሃት ያዛቸው፦

«ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስሙት!»

ይህንም ቃል በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አውቀው በታላቅ ድንጋጤ በግንባራቸው ወደቁ። ኢየሱስም ቀርቦ በቀስታ ዳሰሳቸውና እንዲህ አለ፦

«ተነሡ፥ አትፍሩም።»

ከዚያም ቀና ብለው ተመለከቱ። ብሩሁ ደመና አልፎ ነበር፤ ሁለቱ ነቢያት ከዚያ በኋላ አልታዩም፤ ኢየሱስም ብቻውን በአጠገባቸው ቆሞ ነበር፤ ከክብሩም ጥቂቱ ገና በፊቱ ላይ ነበር።

ከተራራውም ሲወርዱ ኢየሱስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርቱን፥ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም፥ እንዲህ አላቸው፦

«የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ በዚህ ሌሊት ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ።»

ስለዚህ ይህን ድንቅ ራእይ ለሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሊነግሩ እጅግ ቢመኙም፥ ጌታቸውን ታዘዙ፤ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ገና ሳለ ስለ እርሱ አንድ ቃል እንኳ አልተናገሩም።

ኢየሱስንም፥ «የሕግ መምህራን መሲሕ ንጉሡ ከመገለጡ በፊት ነቢዩ ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል የሚሉት ለምንድን ነው?» አሉት።

ኢየሱስም መለሰ፦ «ኤልያስ በእርግጥ ይመጣል፤ ለንጉሡም መምጣት መንገዱን ያዘጋጃል። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ አሁን መጥቶአል፥ ሕዝቡ ግን አላወቁትም። ሊሰሙት አልወደዱም፤ የወደዱትንም አደረጉበት። በእርሱ እንደ ሆነ እንዲሁ በሰው ልጅ ላይ ይሆናል። እርሱም ደግሞ በሰዎች እጅ መከራ ይቀበላል።»

በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ፤ እርሱ እንደ ኤልያስ በምድረ በዳ የኖረ፥ ቁርበትም የለበሰ፥ የምድረ በዳም ምግብ የበላ ነበር፤ እንደ ኤልያስም የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ሰጥቶ ለኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት መንገድ ያዘጋጀ ነበር።


ቀዳሚ ቀጣይ