ምዕራፍ 5 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
መልአኩ ናዝሬትን ጎበኘ
ለሚቀጥለው ታሪካችን ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ሰባ ማይል ያህል ርቃ ወደምትገኘው በገሊላ ወዳለችው ወደ ናዝሬት መንደር እንሄዳለን። ቀደም ብለን እንዳየነው ገሊላ በዮርዳኖስ ወንዝና በታላቁ ባሕር መካከል የምትገኝ የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ነበረች። የገሊላ የታችኛው ክፍል «የኤስድራሎን ሜዳ» ወይም «የኢይዝራኤል ሜዳ» የሚባል ሰፊ ሜዳ ነው፤ በዚያም በቀድሞ ዘመናት ብዙ ጦርነቶች ተደርገዋል። የገሊላ የላይኛው ክፍል በሁሉ ስፍራ ተራሮችና ሸለቆዎች ነው፤ መንደሮቹም በተራሮቹ ራስ ላይ ተቀምጠዋል፥ ወይም በጎናቸው ላይ ተጣብቀዋል፥ አንዳንድ ጊዜም በሸለቆዎቹ ውስጥ ተሸሽገዋል። ሜዳው በሚያልቅበትና ተራሮቹ በሚጀምሩበት ስፍራ ረጅም የገደላማ ኮረብቶች ሰንሰለት እናገኛለን። ወደዚህ ሰንሰለት ራስ ብንወጣ በአንድ ወገን ሜዳው ተዘርግቶ፥ በሩቅም የሜዲትራኒያን ባሕር ይታየናል፤ በሌላው ወገን ማለትም በኮረብቶቹ ሰሜናዊ ተዳፋት ላይ ወደ ናዝሬት ከተማ እንደርሳለን። የኢየሱስ እናት ልጅዋ ከመወለዱ በፊት በልጅነትዋ በዚያ ኖረች፤ ኢየሱስም አብዛኛውን ዕድሜውን በዚያ ኖረ።
በዚያች ምድር ብዙዎቹ የጥንት ከተሞች ቢጠፉም ናዝሬት ዛሬም አለች፤ አሁን ትልቅ ከተማ ሆናለች፤ እኛ በምንተርክበት ዘመን ግን መንደር ብቻ ነበረች። ዙሪያዋን ሁሉ ኮረብቶች ናቸው። ሰው በከተማዪቱ ውስጥ ቆሞ የሚታዩትን አሥራ አምስት ኮረብቶችንና ተራሮችን ሊቈጥር ይችላል።
ጠባብ መንገዶችዋ ባለ አንድ ፎቅ ነጫጭ ቤቶች መካከል ኮረብቶቹን ይወጣሉ፤ ብዙዎቹ ቤቶች በጣሪያቸው ላይ ትንሽ ጕልላት አላቸው። እኛ በምንተርክበት ዘመን በእያንዳንዱ ጣሪያ ዙሪያ በማዕዘኖቹ ምሰሶ ያለው መከታ ነበረ፤ ይህም በጣሪያው ላይ ያለ ሰው እንዳይወድቅ ነው፤ ጠፍጣፋው ጣሪያ ለመጠያየቂያና ለማረፊያ ያገለግል ነበርና፤ የቤቱ ውስጥ መስኮት ስለሌለው ጨለማ ነበር፤ በግድግዳው ላይ አንዲት ትንሽ ቀዳዳ ብቻ ነበረችው። ከእነዚህ ቤቶች አንዱም ወደ መንገድ የሚከፈት በር አልነበረውም። በመንገዱ ዳር ረጅም ቅጥር ነበረ፤ በውስጡም ወደ ክፍት ግቢ የሚያስገባ ደጅ ነበረ፤ ቤቱም በግቢው በአንድ ጫፍ ይቆም ነበር።
በመንደሩ ሴቶች ሁሉ ውኃ የሚቀዱበት አንድ ምንጭ ነበረ። በቤቶቹ ውስጥ የውኃ ጕድጓድ ወይም መሳቢያ ወይም ቧንቧ አልነበረም፤ በምንጩ ዙሪያም በማለዳ ባዶ እንስራ ይዘው የሚመጡና በውኃ ሞልተው በራሳቸው ላይ አመጣጥነው ወደ ቤት የሚወስዱ ብዙ ሴቶች ይታዩ ነበር። ውኃ መቅዳት የሴት ሥራ ተደርጎ ይታይ ስለ ነበር ወንድ የውኃ እንስራ ተሸክሞ የሚታይበት ጊዜ እምብዛም አልነበረም።
በናዝሬት ከነበሩት ከእነዚያ ትናንሽ ነጫጭ ቤቶች በአንዱ ማርያም የምትባል አንዲት ወጣት አይሁዳዊት ልጃገረድ ትኖር ነበር። መልክዋ እንዴት እንደ ነበረ አናውቅም፤ ብዙ ሠዓሊዎች ሥዕልዋን ቢሠሩም ሁሉም የሣሉዋት እነርሱ እንደ ገመቱዋት እንጂ እንደ ነበረችው አይደለም። ስለ ማርያም በእርግጥ የምናውቀውን ሁሉ የምናነበው ከአራቱ ወንጌሎች በሁለቱ፥ በማቴዎስና በሉቃስ ነው፤ ከእነዚህም አንዱ ስለ ልጅነትዋ ወይም ስለ ቤተሰብዋ ምንም አይነግረንም። የአባትዋ ስም ኢያቄም፥ የእናትዋም ሐና እንደ ነበረ ይነገራል፤ ነገር ግን ይህ በአንዱም ወንጌል አይገኝም፤ እውነት መሆኑንም አናውቅም።
ነገር ግን ልበ ንጹሕና ተወዳጅ ልጃገረድ እንደ ነበረች፥ የእስራኤልን አምላክ በፍጹም ልብዋ እንዳገለገለችና ቅዱስ ሕይወት እንደ ኖረች እናውቃለን። ቃሉ በቀላሉ ወደ አፍዋ ይመጣ ስለ ነበር መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ እንደምታውቅ እርግጠኞች ነን፤ እርስዋም ብዙ የምታስብ ጥቂት የምትናገር ልጃገረድ ነበረች። በእነዚያ ዓመታት ከመንደሩ ሌሎች ልጃገረዶች ጋር ወደ ምንጩ ውኃ ልትቀዳ ስትሄድ፥ ወይም በምኵራብ በሴቶች መቀመጫ ተቀምጣ የመጽሐፍ ቅዱስን ንባብ በአሳብ ስትሰማና በለጋ ድምፅዋ ከሌሎቹ ጋር የዳዊትን መዝሙራት ስትዘምር ብዙ ጊዜ ትታይ ነበር።
በዚያች አገር ልጃገረዶች ገና በልጅነታቸው ለጋብቻ ይታጫሉ፤ ማርያምም በዚህ ጊዜ አናጢ ለሆነ፥ ወይም በወንጌሎች እንደሚጠራው በእንጨት ለሚሠራ፥ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ታጭታ ነበር። የዮሴፍና የማርያም ሁለቱ ቤተሰቦች ባለ ጠጎች አልነበሩም። የሠራተኛው ወገን ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን እንደ ብዙዎች እጅግ ድሆች አልነበሩም። በበቂ ሁኔታ መተዳደር የሚችሉ ተራ፥ ታማኝ ሠራተኞች ነበሩ።
ዮሴፍና ማርያም ከተራው ሕዝብ ቢሆኑም በአገሩ ሁሉ ካለው ከከበረው ዘር የተወለዱ ነበሩ። ሁለቱም ከእስራኤል ነገሥታት ከሁሉ ታላቅ ከሆነውና ብዙ ያማሩ መዝሙራትን ከዘመረው ከንጉሡ ከዳዊት ዘር የተገኙ ነበሩ። ባለ አንድ ክፍል በሆኑ ትናንሽ ቤቶች ይኖሩ ነበር፤ እጆቻቸውም በሥራ ደርቀው ነበር፤ ነገር ግን የቤተሰባቸው መሥራች ዳዊት እስከ ኖረበት ቤተ መንግሥት ድረስ የትውልድ ሐረጋቸውን መቍጠር ይችሉ ነበር።
አንድ ቀን ማርያም ብቻዋን ነበረች። በራስዋ ትንሽ ቤት ውስጥ፥ ወይም ብዙ ጊዜ ለጸሎት በምትወጣበት በጣሪያው ላይ፥ ወይም ምናልባት በመንደሩ አጠገብ ባለው ኮረብታ ላይ ከአንድ ዛፍ ሥር ሊሆን ይችላል። ዘካርያስ ከጥቂት ወራት በፊት በቤተ መቅደስ ውስጥ በክብር የሚያበራ ሰማያዊ አካል እንዳየ፥ እንዲሁ አሁን ማርያም ያንኑ መልአክ ገብርኤልን በድንገት ሲያበራላት አየች። እርሱም በጣፋጭ ድምፅ እንዲህ አለ፦
«ማርያም ሆይ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን! ጌታ ከአንቺ ጋር ነውና ታላቅ ሞገስና ፍቅር አግኝተሻል!»
ድምፁ ለስላሳ ነበር፤ ነገር ግን የዚህ የሚያበራ አካል መታየት ወጣቲቱን ልጃገረድ አስደነገጣት። ምን እንደምታስብ፥ ይህ የከበረ አካል ለምን ወደ እርስዋ እንደ መጣ አላወቀችም። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ መልአኩ ንግግሩን ቀጥሎ እንዲህ አለ፦
«ማርያም ሆይ፥ እግዚአብሔር ለልዩ ሞገሱ ከሴቶች ሁሉ መርጦሻልና አትፍሪ። ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እርሱ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል አምላክ ልጅም ይባላል። እግዚአብሔር የአባቱን የዳዊትን ዙፋንና መንግሥት ይሰጠዋል። በእስራኤል ሕዝብ ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።»
መልአኩ ዝም አለ፤ ማርያምም እየተንቀጠቀጠችና እየፈራች የምትናገረውን ቃል አገኘች፦
«ይህ ሁሉ ለእኔ እንዴት ይሆናል? ትርጕሙ ምን እንደ ሆነ አላስተውልም!»
መልአኩም ለተጨነቀችውና ለፈራችው ልጃገረድ እንደ ገና እንዲህ አላት፦
«የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የእግዚአብሔርም ኃይል በአንቺ ላይ ይሆናል፤ ስለዚህ የሚሰጥሽ ቅዱሱ ሕፃን ‹የእግዚአብሔር ልጅ› ይባላል። ደግሞም ልንገርሽ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ በእርጅናዋ በቅርቡ ወንድ ልጅ ትወልዳለች። ይህ ለአንቺ እንግዳ ሊመስልሽ ይችላል፤ ነገር ግን ኃይል የሌለው የእግዚአብሔር ቃል የለም። የእግዚአብሔር ተስፋ ሁሉ በእርግጥ ይፈጸማል።»
ማርያምም እንዲህ አለች፦
«እነሆኝ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ በእርሱም እታመናለሁ። እንደ ቃልህ ይሁንልኝ። ያለ ፍርሃት በጌታ ፈቃድ አርፋለሁ።»
ከዚያም እንደ መጣ በድንገት መልአኩ ከዓይን ተሰወረ፤ ማርያምም ብቻዋን ቀረች። ባየችውና በሰማችው ነገር እጅግ ተደነቀች። በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት የነቢያት ቃል አሁን እንደሚፈጸም፥ ለረጅም ጊዜ ተስፋ የተሰጠበት የእስራኤል ንጉሥ በቅርቡ እንደሚወለድና እርስዋም እናቱ እንደምትሆን የምሥራች የደረሳት ወጣት አይሁዳዊት ልጃገረድ ሁሉ በመልእክቱ ትደነቃለች፥ ምናልባትም ትደነግጣለች።
አንዳንድ ልጃገረዶች ስለዚህ ነገር ያወሩ ነበር፤ እንዲህ ባለ ተስፋም ይኰሩ ይሆናል። የማርያም ጠባይ ግን ጸጥ ያለ ነበር፤ ጥልቅ አሳብዋን ለመናገር አትቸኩልም ነበር። በቤትዋ ወይም በመንደርዋ ስለነዚህ ነገሮች የምታወራው ማንም እንደሌለ በሆነ መንገድ ተሰማት። በልብዋ በዝምታ ሰወረቻቸው፤ ነገር ግን ቀንና ሌሊት ታስብባቸው ነበር።