ምዕራፍ 4 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
በወርቁ መሠዊያ አጠገብ የቆመው እንግዳ
በፍልስጤም ምድር አይሁድ ከሌሎች ስፍራዎች ሁሉ አብልጠው የሚወዷት አንዲት ከተማ ነበረች። እርስዋም በይሁዳ ክፍለ ሀገር የምትገኘው፥ በአገሪቱ ከሁሉ የምትበልጠው ከተማ ኢየሩሳሌም ነበረች። በፍልስጤም ብቻ ሳይሆን አይሁድ በሚኖሩበት በምድር ሁሉ ለሚገኙ አይሁድ ሁሉ እርስዋ «ቅድስቲቱ ከተማ» ነበረች። ሕዝቡ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ለማምለክ ከአገሩ ክፍሎች ሁሉ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ይመጡ ነበር፤ ብዙ ቤተሰቦችም በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ይመጡ ነበር። ታላላቅ በዓላት በሚባሉት በእነዚህ ወቅቶች ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ ለአምልኮ ወደዚያ በሚወጡ መንገደኞች ይጨናነቁ ነበር። በብዙ መቶ ማይል ርቀት በሌሎች አገሮች፥ እስከ ሮም ድረስ እንኳ የሚኖሩ አይሁድ በሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ከተማዪቱን ለመጎብኘት ይጥሩ ነበር። ስለ ኢየሩሳሌምም እንዲህ ያሉ መዝሙሮችን ይዘምሩ ነበር፦
«ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥
ቀኜ ትርሳኝ፤
ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ
ባላስብሽ፥
ኢየሩሳሌምን
ከደስታዬ ሁሉ በላይ ባላደርጋት።»
ኢየሩሳሌምን ቅድስት ከተማ ያደረጋት ቤተ መቅደስዋ ነበር። ይህም የከተማዪቱ ብዙው ክፍል ከቆመበት ከጽዮን ተራራ በሸለቆ ብቻ ተለይቶ፥ በሞሪያ ተራራ ላይ የቆመ እጅግ ያማረ ሕንፃ ነበር። አይሁድ አምላካቸው በውስጡ ያድራል ብለው ያምኑ ስለ ነበር ቤተ መቅደሱን «የእግዚአብሔር ቤት» ብለው ይጠሩት ነበር። በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ከድንጋይ የተሠራ፥ ውስጡ ክፍት የሆነና በብረት ፍርግርግ የተሸፈነ ትልቅ ሣጥን የሚመስል መሠዊያ ነበረ። በዚህ መሠዊያ ላይ ሌሊትና ቀን እሳት ይነድድ ነበር፤ የእግዚአብሔርን አምልኮ የሚመሩ ካህናትም ለእግዚአብሔር ስጦታ ሆነው የሚቃጠሉትን የበጎችንና የበሬዎችን መባ በእሳቱ ላይ ያኖሩ ነበር፤ «መሥዋዕት» ብለው የሚጠሩት መባ ሲቃጠልም ሕዝቡ በመሠዊያው ዙሪያ ቆመው ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር።
በቤተ መቅደሱ ሕንፃ ውስጥ ሁለት ክፍሎች ነበሩ። የፊተኛው ክፍል «ቅድስት» ይባል ነበር፤ በአንዱ ወገኑ በወርቅ የተለበጠ ገበታ ነበረ፤ በላዩም ለእግዚአብሔር መባ የሆኑ አሥራ ሁለት እንጀራዎች ይቀመጡ ነበር፤ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ለእያንዳንዳቸው አንድ እንጀራ ነበር። በክፍሉ በሌላው ወገን «የወርቅ መቅረዝ» የሚባል ሰባት ቅርንጫፎች ያሉት የወርቅ መብራት ማስቀመጫ ቆሞ ነበር። በክፍሉ በውስጠኛው ጫፍ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ፊት ካለው ከታላቁ መሠዊያ ያነሰ፥ ከወርቅ የተሠራ ሌላ መሠዊያ ነበረ። በዚህ የወርቅ መሠዊያ ላይ ካህኑ በየቀኑ ሁለት ጊዜ በሙዳይ ዕጣን ያቀርብ ነበር፤ ዕጣኑም መልካም መዓዛ ያላቸውን ሙጫዎች፥ ነጭ ዕጣንንና ከርቤን በመቀላቀልና በማቃጠል ይዘጋጅ ነበር፤ እነርሱም ቅድስትን የሚሞላ መዓዛው ያማረ ነጭ ደመና ይሆኑ ነበር።
ከቅድስት ባሻገር «ቅድስተ ቅዱሳን» የሚባል ሌላ ክፍል ነበረ። ከሊቀ ካህናቱ በቀር ማንም ወደዚህ ክፍል አይገባም ነበር፤ እርሱም ቢሆን በዓመት አንድ ቀን ብቻ ይገባ ነበር፤ ይህ የውስጠኛው ክፍል ለእግዚአብሔር ማደሪያ የተለየ ነበርና፤ አይሁድም በዚህ ክፍል የእግዚአብሔር ብርሃን ማንም ሊቋቋመው በማይችል ብርታት ያበራል ብለው ያምኑ ነበር። ንጉሡ ሰሎሞን በሠራው በመጀመሪያው ቤተ መቅደስ የቃል ኪዳኑ ታቦት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ይቀመጥ ነበር። ይህም በወርቅ የተለበጠ ሣጥን ሲሆን አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸው ሁለቱ የድንጋይ ጽላቶች በውስጡ ነበሩ። ነገር ግን የቃል ኪዳኑ ታቦት ጠፍቶ ነበር፤ እኛ በምንናገርበት ዘመንም በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከአንድ የዕብነ በረድ ድንጋይ በቀር ምንም አልነበረም።
አንድ ቀን ዘካርያስ የሚባል አንድ ሽማግሌ ካህን በቅድስት ውስጥ በወርቁ መሠዊያ ላይ ዕጣን ያጥን ነበር። ጥና ብለው የሚጠሩትን ሙዳይ በነጭ ዕጣንና በከርቤ ሞልቶ፥ በቤተ መቅደሱ ፊት ካለው ከታላቁ መሠዊያ የእሳት ፍም አድርጎበት ነበር። ነጭ ደመናውን ወደ አየር የሚያወጣውን የዕጣን ጥናውን ይዞ ወደ ቅድስት ገብቶ በመሠዊያው ላይ ሊያኖረው ሲል፥ በወርቁ መሠዊያ በስተ ቀኝ አንድ ሰው ቆሞ በድንገት አይቶ ደነገጠ።
ዘካርያስ ከእርሱ በቀር ማንም በዚያ የመገኘት መብት እንደሌለው ያውቅ ስለ ነበር በክፍሉ ውስጥ ሰው በማየቱ ተደነቀ። ነገር ግን በመሠዊያው አጠገብ የቆመውን ይህን እንግዳ ሲመለከት ይበልጥ ተደነቀ፥ ፍርሃትም ሞላበት። እንግዳው ጎልማሳ ይመስል ነበር፤ ፊቱና አካሉ ልብሱም እንደ ፀሐይ ያበሩና ያንጸባርቁ ነበር፤ ሽማግሌው ካህን ቀና ብሎ ሊያየው እስኪያቅተው ድረስ እጅግ የከበረ ነበር።
ዘካርያስ ይህ የከበረ አካል ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ መሆኑን ወዲያው አወቀ። በፍርሃት ተንቀጠቀጠ፤ ጕልበቱ ተብረከረከ፤ መሬት ላይ ከመውደቅም ጥቂት ቀረው። መልአኩም በለስላሳና በደግ ድምፅ እንዲህ አለው፦
«ዘካርያስ ሆይ፥ አትደንግጥ። የምትፈራው ምንም ነገር የለም። የምሥራች ይዤልህ መጥቻለሁ። አንተና ደጊቱ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ለብዙ ዓመታት ወደ ሰማይ ስታቀርቡት የነበረውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰምቶአል። ወንድ ልጅ ይሆንልሃል፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ልጅህ ሰው በሆነ ጊዜ ለብዙ ሰዎች ደስታና ተድላ ያመጣል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፤ ሕዝቡንም ለረጅም ዘመን ሲጠብቁት ለነበረው ንጉሥ መምጣት ማዘጋጀት ሥራው ይሆናል። ልጅህ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ ከቶ እንዳይጠጣ ተጠንቀቅ፤ እግዚአብሔርን ብቻ ሊያገለግልና የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝቡ ሊናገር፥ ንጉሣቸውና መድኃኒታቸው መቅረቡን ሊነግራቸው ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናልና።»
ካህኑ በመደነቅና በፍርሃት እጅግ ተሞልቶ ስለ ነበር የሰማውን ለማመን ተቸገረ።
«እነዚህ ድንቅ ቃላት እንዴት እውነት ሊሆኑ ይችላሉ?» አለ። «እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም ደግሞ አርጅታለች። አሁን ልጆች ለመውለድ እጅግ አርጅተናል። ይህን ሁሉ እንዴት አምናለሁ?»
መልአኩም ዘካርያስ ቃሉን እንደ ተጠራጠረ ባየ ጊዜ ደስ አላለውም፤ እንዲህም አለ፦
«እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህና ይህችን የምሥራች እንዳመጣልህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬአለሁ። አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላላመንህ ቃሌ እስኪፈጸምና ልጅህ እስኪወለድ ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።»
ከዚያም መልአኩ እንደ መጣ በድንገት ከዓይን ተሰወረ፤ ዘካርያስም ብቻውን ቀረ።
በዚህ ጊዜ ሁሉ መባው ሲቀርብ እግዚአብሔርን እያመለከ ብዙ ሕዝብ በቤተ መቅደሱ ውጭ ቆሞ ነበር። ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይህን ያህል መዘግየቱ አስደነቃቸው፤ በወጣም ጊዜ መናገር እንዳልቻለ ባዩ ጊዜ ይበልጥ ተደነቁ። መልአክ እንዳየ ሊያሳያቸው እየሞከረ በምልክት ጠቀሳቸው፤ ነገር ግን መልአኩ የነገረውን አልነገራቸውም፤ ያ ቃል ለእርሱ ብቻ እንጂ ለሌሎች የታሰበ አልነበረምና።
እያንዳንዱ ካህን በቤተ መቅደስ አንድ ሳምንት ቆይቶ ወደ ቤቱ ይሄድ ነበር፤ ስለዚህ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዘካርያስ ኢየሩሳሌምን ትቶ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። ቤቱም የእስራኤላውያን የቀድሞ አባቶች አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ ከተቀበሩባት ከጥንቲቱ ከተማ ከኬብሮን ብዙ የራቀ አልነበረም።
ባልዋ በምልክትና በጽሕፈት ስለ መልአኩ፥ የጌታንም ቃል ለሕዝቡ የሚያደርስ ልጅ እናት እንደምትሆን ስለ ሰጠው ተስፋ በነገራት ጊዜ ኤልሳቤጥ እንዴት ደስ አላት! እግዚአብሔር የሚናገራቸውና ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች «ነቢያት» ይባሉ ነበር። ባለፉት ዘመናት እንደ ሳሙኤል፥ እንደ ኤልያስና እንደ ኢሳይያስ ያሉ ብዙ ታላላቅ ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ለእስራኤላውያን ተናግረው ነበር። ነገር ግን በምድሪቱ የነቢይ ድምፅ ከተሰማ ከአራት መቶ ዓመት በላይ አልፎ ነበር። ተስፋ የተሰጣቸው ልጃቸው ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሕዝቡ እንደ ገና ሊናገር ነበር። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ እንደ ነቢይ የሚናገረውን ድምፁን እስኪሰሙ ድረስ በሕይወት ላይቆዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ተስፋ ነበራቸው፤ በዚያም ተስፋ ልጃቸው እስኪመጣና ለታላቁ ሥራው እስኪያድግ እየጠበቁ ደስ ብሏቸው ይኖሩ ነበር።