ምዕራፍ 48 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ታላቁ ምስክርነት
ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ከገሊላ ባሕር አጠገብ ካለችው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሰሜን፥ እስከ እስራኤል ምድር ዳርቻ፥ እስከ አርሞንዔም ተራራ ግርጌ መራቸው። በዚህ ስፍራ የዮርዳኖስ ወንዝ ከሚፈልቅባቸው ታላላቅ ምንጮች በአንዱ አጠገብ የፊልጶስ ቂሣርያ ከተማ ነበረች፤ ይህም ስም የተሰጣት በገሊላ ይገዛ የነበረው የሄሮድስ አንቲጳስ ወንድም ሄሮድስ ፊልጶስ በሚገዛው ምድር ውስጥ ስለ ነበረች ነው። ኢየሱስ በዙሪያው ሕዝብ እንዲሰበሰብ ሳይሆን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻውን ለመሆን ስለ ፈለገ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ከተማ አልገባም፤ በከተማዪቱ አጠገብ ካሉት መንደሮች ወደ አንዲቱ ሄደ እንጂ።
ደቀ መዛሙርቱ ስለ ኢየሱስ፥ ማን እንደ ሆነ፥ ሊሠራው ስላለው ሥራና በቅርቡ ስለሚደርስበት መከራ አብልጠው የሚያውቁበት ጊዜ አሁን ደርሶ ነበር። የማስተማሩም መንገድ ነገሩን በቀጥታ መንገር ሳይሆን፥ እውነትን ራሳቸው ፈልገው እንዲያገኙት በጥያቄ እየመራ መውሰድ ነበር። አንድ ቀን ብቻውን ወደ አባቱ ከጸለየ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦
«እስቲ ንገሩኝ፥ ሰዎች እኔን ማን ነው ይሉኛል?»
ደቀ መዛሙርቱም «አንዳንዶች ከሙታን የተነሣ መጥምቁ ዮሐንስ ነህ ይላሉ፤ ሌሎች ወደ ምድር እንደ ገና የመጣ ነቢዩ ኤልያስ ነህ ይላሉ፤ ሌሎችም ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስ ወይም ከጥንት ነቢያት አንዱ ነህ ይላሉ» ብለው መለሱ።
ኢየሱስም «እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?» ብሎ ጠየቀ።
ስምዖን ጴጥሮስም ወዲያው መለሰ፤ ከዐሥራ ሁለቱ መካከል ሁልጊዜ ለመናገር የሚቸኵለው እርሱ ነበርና፦
«አንተ መሲሕ፥ ክርስቶስ፥ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ!»
አይሁድ በየስፍራው በላያቸው የሚነግሥ፥ ከሮም ሥልጣን ነፃ የሚያወጣቸውና ድል አድራጊ ታላቅ ሕዝብ የሚያደርጋቸው ንጉሥ ይጠብቁ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ። ይህንን ንጉሥ በራሳቸው ቋንቋ «መሲሕ» ብለው ይጠሩት ነበር፤ ትርጓሜውም «የተቀባው» ማለት ነው፤ በእስራኤል አዲስ ንጉሥ የሚመረጠው በራሱ ላይ ዘይት በመፍሰስ ነበርና። «መሲሕ» የሚለው ቃል በየስፍራው በሚነገረው በግሪክ ቋንቋ «ክርስቶስ» ነበር፤ እርሱም «የተቀባው» ማለት ነው። ጴጥሮስ «አንተ መሲሕ፥ ክርስቶስ ነህ» የሚለውን ቃል ሲናገር ኢየሱስ ሕዝቡ ሁሉ ይጠብቁት የነበረው የእስራኤል ንጉሥ መሆኑን ማለቱ ነበር።
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ብፁዕ ነህ፤ ይህን የገለጠልህ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሰው አይደለምና። አዎን፥ እኔም እልሃለሁ፥ ‹ስምህ ጴጥሮስ—ዓለት—ነው፤ በዚህም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የሲኦልም ኃይላት ሁሉ አያሸንፉአትም።› ደግሞም ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ፥ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ። በምድር የምትከለክለው ሁሉ በሰማይ የተከለከለ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈቅደው ሁሉ በሰማይ የተፈቀደ ይሆናል።»
ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን መሲሕ-ክርስቶስ፥ ንጉሥ፥ ብሎ በዚህ ቃል በመመስከር የመጀመሪያው ስለ ሆነ በጌታ ተከታዮች መካከል የተለየ ክብር ተሰጠው። ከአንድ ዓመት በላይ አስቀድሞ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ስምዖንን ለመጀመሪያ ጊዜ ባገኘው ጊዜ «ዓለት» ማለት የሆነውን ጴጥሮስ የሚለውን አዲስ ስም እንደ ሰጠው ታስታውሳላችሁ።
ከዚያም ኢየሱስ ጴጥሮስ የተናገረውን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ንጉሥ፥ መሆኑን ለሕዝቡ ለማንም እንዳይናገሩ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፤ ይህን በግልጥ የሚገልጡበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበርና። አሁን ግን ንጉሥ እንደሚሆንና በእስራኤል ላይ እንደሚገዛ ስላወቁ፥ ለማስተዋል እጅግ የከበዳቸውን ሌሎች ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ይነግራቸው ጀመር።
ኢየሱስም «በቅርቡ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ በዚያም ከሕዝቡ አለቆች፥ ከካህናት አለቆችና ከሕግ መምህራን ብዙ መከራ እቀበል ዘንድ ይገባኛል። እገደላለሁ፥ እቀበራለሁም፤ በሦስተኛውም ቀን እነሣለሁ» አለ።
ደቀ መዛሙርቱ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ የሚነግሥ ከሆነ እነዚህን መከራዎች መቀበሉና መሞቱ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ሊያስተውሉ አልቻሉም። ጴጥሮስም ብቻውን ሊያነጋግረው ወደሚችልበት ስፍራ ኢየሱስን ገለል አድርጎ ወሰደው።
ጴጥሮስም «መምህር ሆይ፥ እንዲህ ያለውን ነገር መናገር የለብህም። እግዚአብሔር ይህ ነገር እንዲደርስብህ አይፈቅድም። በኢየሩሳሌም ልትገደል አትሄድም፤ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሄደው በዳዊት ዙፋን ተቀምጠህ በምድሪቱ ላይ ልትነግሥ ነው!» አለ።
ኢየሱስ ግን ጀርባውን ለጴጥሮስ ሰጥቶ ደቀ መዛሙርቱን እየተመለከተ እንዲህ አለ፦
«አንተ ሰይጣን፥ ከእኔ ራቅ! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከማድረግ ልታስተኝ ትፈልጋለህ! ነገሮችን እንደ ሰው እንጂ እግዚአብሔር እንደሚያያቸው አታይምና!»
ኢየሱስ በጴጥሮስ ልብ ውስጥ ያለው የመንግሥት ሐሳብ ሰይጣን በታላቁ ፈተና በተራራው ላይ ያሳየው ዓይነት እንደ ሆነ አየ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር መንግሥት ሳይሆን ሰዎች ይጠብቁት የነበረው ዓይነት፥ እንደ ዓለም መንግሥታት ያለ መንግሥት ነው።
ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱንና በዙሪያቸው የነበሩትን ሕዝብ ጠርቶ እንዲህ አለ፦
«ማንም ሊከተለኝና ደቀ መዝሙሬ ሊሆን ቢወድ የራሱን ፈቃድ ይተው፥ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ብሎ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ፥ በማትረፉም ነፍሱን ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ሰው ነፍሱን የሚያህል ምን ዋጋ ሊሰጥ ይችላል? የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ከመላእክቱ ጋር ይመጣልና፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሊነግሥ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች አሉ።»