ምዕራፍ 47 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
እንደ ገና በገሊላ ባሕር ላይ
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከዐሥሩ ከተሞች አገር በቀጥታ የገሊላን ባሕር ተሻግረው በደቡብ ምዕራብ ዳርቻው ማጋዳን ወይም መግደላ ወደ ተባለች ከተማ መጡ። ኢየሱስ በገሊላ ሲዞር አብረውት ከሚሄዱት ሴቶች አንዲቱ መግደላዊት ማርያም፥ ማለት የመግደላዋ ማርያም፥ ከዚህች ከተማ ነበረች። ኢየሱስ ወደዚህ ስፍራ የመጣው ለማረፍና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጸጥታ ለመነጋገር ነበር፤ ነገር ግን ከታንኳው እንደ ወረደ አንዳንድ ፈሪሳውያንና በእርሱ የማያምኑ ሌሎች ሰዎች ተገናኙትና እንዲህ አሉት፦
«መምህር ሆይ፥ ነቢይ ወይም እግዚአብሔር የላከው መሆንህን የሚያሳይ ከሰማይ ምልክት አሳየን።»
ኢየሱስ ተአምር ወይም ድንቅ ሥራ እንዲያደርግ የፈለጉት በእርሱ እንዲያምኑ ሳይሆን ምን ማድረግ እንደሚችል ለማየት ብቻ ነበር። ፈሪሳውያን ራሳቸውን እንደ መሪዎች ይቈጥሩ ነበርና በየስፍራው ኢየሱስን ይቃወሙ፥ ያልተማረውንም ሕዝብ በእርሱ ላይ ያነሣሡ ነበር።
ኢየሱስ ለመታየት ብቻ ፈውስን ወይም ድንቅ ሥራን ከቶ እንዳላደረገ አስቀድመን አይተናል። የተቸገሩትንና በመከራ ያሉትን ይረዳ ነበር፤ ተአምርን ለማየት ያለውን ከንቱ ምኞት ግን ብቻ ሊያረካ አልወደደም። ሌሎችን እንደ መለሰ ለእነዚህም ፈሪሳውያን እንዲህ ብሎ መለሰ፦
«ከሰማይ ምልክት እሰጣችኋለሁ። በመሸ ጊዜ ፀሐይ ስትጠልቅ ‹ሰማዩ እንደ እሳት ቀልቶአልና ብራ ይሆናል› ትላላችሁ። ማለዳ ግን ሰማዩ ቀይ ቢሆን ‹ሰማዩ እንደ እሳት ቀልቶ ደምኖአልና ዛሬ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል› ትላላችሁ። በሰማይ ያሉትን ምልክቶች ማንበብ ትማራላችሁ፤ የዘመኑን ምልክቶች ግን ማንበብ አታውቁም። ብትመለከቱ ኖሮ ከእግዚአብሔር የመጣሁ መሆኔን ወይም አለመሆኔን ማየት በቻላችሁ ነበር። ዘወትር ምልክትን የሚሻ ክፉና የማይታዘዝ ሕዝብ ነው። ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ለዚህ ሕዝብ ምልክት አይሰጠውም።»
ዮናስ ለእነርሱ እንዴት ምልክት ወይም መታሰቢያ እንደሚሆን እንኳ አልነገራቸውም። ምናልባት ከጥቂት ወራት በኋላ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደ ተገደለና እንደ ተቀበረ፥ ዮናስም በታላቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀን ተቀብሮ ከኖረ በኋላ በሕይወት እንደ ወጣ እርሱም ከሦስት ቀን በኋላ ተነሥቶ ወደ ሕይወት እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ፥ ያን ጊዜ ዮናስ ለኢየሱስ እንዴት ምልክት እንደ ሆነ ያስተውሉ ይሆናል።
ኢየሱስ ይህ ስፍራ ጸጥታ የሚገኝበትና ደቀ መዛሙርቱን የሚያስተምርበት ጊዜ የሚያገኝበት እንዳልሆነ ወዲያው አየ፤ ስለዚህ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና ወደ ታንኳው ገብቶ በባሕሩ ወደ ላይ ሄደ። በችኰላ ስለ ተነሡ ደቀ መዛሙርቱ በምድር ሳሉ እንጀራ ለመግዛት አላሰቡም፤ በታንኳውም ውስጥ ለኢየሱስና ለዐሥራ ሁለቱ ሰዎች አንድ እንጀራ ብቻ ነበራቸው።
በባሕሩ ላይ እየቀዘፉ ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦
«ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ።»
እነርሱም ብዙ እንጀራ ይዘው ስላልመጡ የሚናገራቸው መስሎአቸው እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አለ፦
«እንጀራ ስለ ጐደለባችሁ እርስ በርሳችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? በእኔ ያላችሁ እምነት እንዴት ትንሽ ነው! አምስት ሺህ ሰዎችን የመገብሁባቸውን አምስቱን እንጀራ፥ ከዚያም በኋላ ያነሣችሁትን ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ቍርስራሽ አታስታውሱምን? ለአራቱ ሺህ ስለ ተከፈለው ስለ ሰባቱ እንጀራ፥ ስላነሣችሁትም ሰባት መሶብ ሙሉ ረሳችሁን? ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉም? አይደለም፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ።»
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከፈሪሳውያን እርሾ ሲያስጠነቅቅ ትዕቢታቸውን፥ የሃይማኖት ግብዝነታቸውንና ሥርዓትን በመጠበቅ ያላቸውን ጥንቃቄ፥ እግዚአብሔርን ግን በልብ ሳያገለግሉ መቅረታቸውን ማለቱ ነበር። በሄሮድስ እርሾ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ምንም ሳያስቡ ለዓለም፥ ለኃጢአት ተድላም የመኖርን መንፈስ ማለቱ ነበር።
ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ሰዎቹም ኢየሱስን እንዳዩ አንድ ዕውር ወደ እርሱ አምጥተው ኢየሱስ ዓይኑን ሲያበራለት ለማየት ተስፋ አድርገው እንዲዳስሰው ለመኑት። ኢየሱስ ግን ሰውየው ሲፈወስ እንዲመለከቱ አልፈቀደላቸውም። ከሕዝቡ ለይቶ ከከተማው ውጭ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ ወሰደው። በዚያም በሰውየው ዓይኖች ላይ እንትፍ ብሎ እጆቹን ጫነበትና እንዲህ ብሎ ጠየቀው፦
«አንዳች ታያለህን?»
ሰውየውም አሻቅቦ «አዎን፥ ጥቂት አያለሁ፤ ነገር ግን አጥርቼ አይደለም። ሰዎች ሲመላለሱ አያለሁ፤ ነገር ግን እንደ ዛፍ ይመስላሉ» አለ።
ከዚያም ኢየሱስ እጆቹን በሰውየው ዓይኖች ላይ ጫነ። እርሱም ዙሪያውን ተመለከተ፤ አሁንም ሁሉን አጥርቶ ማየት ቻለ።
ኢየሱስም «አሁን በቀጥታ ወደ ቤትህ ሂድ፤ ሰዎች አይተውህ ዓይንህ እንዴት እንደ በራልህ እንዳይጠይቁህ ወደ ከተማው አትግባ» አለው።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በቤተ ሳይዳ አልቈዩም፤ ደቀ መዛሙርቱ ምንም የማያውቋቸውን ታላላቅ እውነቶች፥ ደግሞም ለማመንና ለማስተዋል የሚከብዷቸውን እውነቶች የሚያስተምርበት ጸጥ ያለና ገለልተኛ ስፍራ ማግኘት እንዳለበት ተሰምቶት ነበርና። ስለዚህ ከቤተ ሳይዳ ተነሥቶ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ያለውን መንገድ ተከትሎ በሩቅ ሰሜን ወዳለው ወደ አርሞንዔም ተራራ ግርጌ ሄደ።