የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በዐሥሩ ከተሞች አገር

ምዕራፍ 46 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

በዐሥሩ ከተሞች አገር

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻውን ለመሆን ከፈለገ የጢሮስንና የሲዶናን አገር መተው እንዳለበት ወዲያው ተረዳ፤ የሴቲቱን ልጅ ከክፉ መንፈስ ከፈወሳት በኋላ ሕዝቡ ሌላ የኃይል ሥራ ለማግኘት ወደ እርሱ ይመጡ ነበርና። ስለዚህ ወደ ሩቅ ስፍራ ለመሄድ ቈረጠ፤ ደቀ መዛሙርቱንም ይዞ ከጢሮስ በሰሜን ወዳለችው ወደ ሲዶና ሄደ፤ ከዚያም በገሊላ በኩል ሳይሆን ገሊላን ዞሮ ከገሊላ ባሕር በሰሜን ወዳለው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ደረሰ። ዮርዳኖስንም ተሻግሮ በገሊላ ባሕር ምሥራቅ በኩል ዲካፖሊስ ወደ ተባለው አገር መጣ፤ ይህም ስም በዚያ ክፍል ካሉት ከዐሥር ታላላቅ ከተሞች የተነሣ «የዐሥሩ ከተሞች አገር» ማለት ነው። በዚህ ጕዞ ላይ ሳሉ ያዩአቸው ሰዎች ጥቂቶች ነበሩ፤ አብረውም ሲሄዱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እየተነጋገረ ብዙ ነገር አስተማራቸው።

ኢየሱስ የደረሰበት ስፍራ ከጥቂት ወራት በፊት ከአንድ ምስኪን ሰው ብዙ ሠራዊት የሚያህሉ ክፉ መናፍስትን አውጥቶ ወደ እሪያዎቹ መንጋ ከላካቸው ከተማ ብዙ የራቀ አልነበረም። በዚያን ጊዜ፥ ታስታውሳላችሁ፥ ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ መጥተው ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት፤ ኃይሉን አይተው ነበር፥ ቸርነቱን ግን ፈጽሞ አላወቁም ነበርና። ከዚያ ተአምር በኋላ ግን የተፈወሰው ሰው በዚህ በዐሥሩ ከተሞች አገር ሁሉ እየዞረ ኢየሱስ ያደረገለትን መልካም ሥራ፥ እርሱንም በማባረራቸው ምን ያህል እንደ ጐደለባቸው በየስፍራው ለሰዎች ይነግር ነበር።

ኢየሱስ ወደዚህ አገር ለሁለተኛ ጊዜ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ ተዘጋጅተው መምጣቱን በጕጕት ይጠብቁ ነበር። በታላቅ ደስታ በኢየሱስ ዙሪያ ተሰበሰቡ፤ ሊያዩትም ከቅርብም ከሩቅም መጡ። ብቻውን ለመሆን ተስፋ አድርጎ ወደ ተራራ ወጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ። ሕዝቡ ግን አንካሶችንና በልዩ ልዩ በሽታ የታመሙትን ይዘው እጅግ ብዙ ሆነው ወደ እርሱ መጡ። እነዚህንም ሕመምተኞች በእግሩ አጠገብ አስቀምጠው እንዲፈውሳቸው ለመኑት። ሁሉንም ፈወሳቸው። ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጕንድሾች ሲድኑ፥ አንካሶች ሲመላለሱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ሁሉም ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።

በዚህ ጊዜ እጅግ ደንቆሮ የሆነና ሰዎች ቃሉን ሊያስተውሉ እስኪያቅታቸው ድረስ የሚንተባተብ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ። እጁንም በዚህ ሰው ላይ ጭኖ እንዲፈውሰው ለመኑት። ኢየሱስ ግን ብዙ ሕዝብ እየተመለከተ በግልጥ ይህን ሊያደርግ አልወደደም። ብቻቸውን ሊሆኑ ወደሚችሉበት ስፍራ ከሕዝቡ ለይቶ ወሰደው። ጣቶቹንም በሰውየው ጆሮዎች አገባ፤ ከዚያም አንዱን ጣቱን በገዛ ምላሱ አርጥቦ በእርሱ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም አሻቅቦ እየቃተተ «ተከፈት» አለ። የሰውየው ጆሮዎችና ምላሱ ወዲያው ተፈቱ፤ መስማትና አጥርቶ መናገር ቻለ። ኢየሱስ ሰውየውንና ወዳጆቹን ስለ ፈውሱ ለማንም እንዳይናገሩ ከለከላቸው፤ እነርሱ ግን ትእዛዙን ተላልፈው በየስፍራው አወሩት። ይህን ሰው ያዩ ሁሉ ተገረሙ፤ ስለ ኢየሱስም «ሁሉን ደኅና አድርጎአል! ደንቆሮችን እንኳ እንዲሰሙ ዲዳዎችንም እንዲናገሩ ያደርጋል!» አሉ።

ሕዝቡ ከኢየሱስ ሳይለዩ ሦስት ቀን ተከተሉት። በዚያን ጊዜ ሰዎቹ ይዘውት የመጡት ምግብ ሁሉ ተበልቶ አልቆ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ችግራቸው ምንም ሳያስቡ ከኢየሱስ ጋር ቈዩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦

«ስለዚህ ሁሉ ሕዝብ ልቤ ይራራል፤ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና፥ የሚበሉትም የላቸውም። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ ስፍራ መጥተዋል፤ በመንገድ እንዳይዝሉ ብዬ ተርበው ሳሉ ላሰናብታቸው አልወድም።»

ደቀ መዛሙርቱም «ከተማ በአጠገቡ በሌለበት እንደዚህ ባለ ምድረ በዳ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንጀራ ከወዴት እናገኛለን?» ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስም «ስንት እንጀራ አላችሁ?» ብሎ ጠየቀ።

እነርሱም «በጠቅላላው ሰባት እንጀራ አለን፤ ከእርሱም ጋር ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች» ብለው መለሱ።

ኢየሱስም ሕዝቡ ሁሉ በመሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ በተቀመጡም ጊዜ እንጀራውንና ዓሣውን አንሥቶ ስለ እነርሱ የሰማዩን አባቱን አመሰገነ። ከዚያም እንጀራውን፥ ደግሞም የደረቀውን ዓሣ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ፤ እያንዳንዱም የፈለገውን ያህል በላ።

ከምግቡ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ትልልቅ መሶቦች ይዘው እየዞሩ ከተረፈው ምግብ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የመገባቸው ሰዎች ከሴቶችና ከልጆች ሌላ አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ሁሉም ከጠገቡ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው፤ ከዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ የገሊላን ባሕር ተሻገረ።


ቀዳሚ ቀጣይ