ምዕራፍ 45 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ በባዕድ አገር
ኢየሱስ በቅፍርናሆም ምኵራብ ባስተማረው «የሕይወት እንጀራ» በተባለው ስብከቱ፥ በገሊላ ሕዝብ መካከል የሚሠራውን ሥራ ፈጸመ። በዚያች አገር ከአንድ ዓመት በላይ ኖሮ ነበር፤ በየክፍሏ ሁሉ ተዘዋውሮ ነበር፤ በአብዛኞቹ መንደሮችዋና ከተሞችዋ ተናግሮ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱንም በሌሎች ብዙ ስፍራዎች እንዲሰብኩ ልኮ ነበር። በገሊላ የነበረ ሰው ሁሉ ኢየሱስን ሰምቶት ወይም ስለ እርሱ ሰምቶ ነበር። በእርሱና በወንጌሉ ካላመኑ፥ ያላመኑት ስላልፈለጉ ነው።
አሁን በኢየሱስ ፊት ሌላ ጠቃሚ ሥራ ነበረ። ይህም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማሠልጠን ነበር። እነዚህ ሰዎች፥ በኋላ ሐዋርያት የተባሉት፥ አንድ ዓመት ያህል ከእርሱ ጋር ነበሩ። ስብከቱን አድምጠው ነበር፤ ትምህርቶቹንም ብዙ ጊዜ ደጋግመው ሰምተው ነበር፤ ኢየሱስ በተለያዩ ስፍራዎች ያንኑ ትምህርት ለሕዝቡ ይሰጥ ነበርና፤ ዐሥራ ሁለቱም እነዚያን ትምህርቶችና ምሳሌዎች በየስፍራው ይሰሙ ነበር፤ ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ቃሉን በልባቸው እስኪያጠኑትና ኢየሱስን ራሱን ላልሰሙት ሌሎች ሰዎች እንደ መልእክቱ አድርገው እስኪያደርሱት ድረስ እንዲሰሙት ወዶ ነበርና።
በማቴዎስ፥ በማርቆስ፥ በሉቃስና በዮሐንስ በተጻፉት በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ ይህን ያህል ብዙ የኢየሱስ ትምህርቶችና ምሳሌዎች የምናገኝበት አንዱ ምክንያት፥ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ብዙ ጊዜ ስለ ሰሙአቸው፥ ስለ ተማሩአቸውና ለሌሎች ሊነግሩአቸው ስለ ቻሉ ነው፤ በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ከምድር ካለፈ ቢያንስ ከሠላሳ ዓመት በኋላ እንኳ ቃሉ ይታወስ ነበር፥ ሊጻፍም ቻለ።
ነገር ግን እንደ ተራራው ስብከትና እንደ ምሳሌዎቹ ካሉት ከኢየሱስ የአደባባይ ትምህርቶች ሌላ፥ ለሕዝቡ ሊሰጡ የማይችሉ ሌሎች ታላላቅ የወንጌል እውነቶች ነበሩ፤ ሕዝቡ ለእነርሱ ገና አልተዘጋጀም ነበርና፥ ሊያስተውሉአቸውም አይችሉም ነበርና። ተራው ሕዝብ ስለ «የሕይወት እንጀራ» በተናገረው ቃል እንዴት ግራ እንደ ተጋባ እናያለን። ኢየሱስ ጥልቅ የሆኑትን የወንጌሉን እውነቶች ያስተምራቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ገለል አድርጎ መውሰድ እንደሚያስፈልገው አየ። በገሊላ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ብቻውን ሊሆን አይችልም ነበር፤ ወደ የትም ቢሄድ ሊፈወሱ የሚመጡ ብዙ ሕመምተኞች፥ ደግሞም በክፉ መናፍስት ኃይል የተያዙትን ሰዎች እየመሩ ኢየሱስ መናፍስቱን እንዲያወጣ የሚለምኑ ሌሎች ሰዎች ሁልጊዜ ይኖሩ ነበርና። ደግሞም በየስፍራው ጥያቄዎቻቸውን ይዘው የሚመጡ፥ ተአምራትን የሚጠይቁና ሕዝቡን በኢየሱስ ላይ ለማነሣሣት የሚሞክሩ ፈሪሳውያንና ጻፎች ነበሩ። ኢየሱስ በየትም ቢሆን ሁልጊዜ ሕዝብ በዙሪያው ይሰበሰብ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ሊያውቁአቸው የሚገቡ አንዳንድ እውነቶችን ሊያስተምራቸው ጊዜ አላገኘም።
ስለዚህ ከገሊላ ወጥቶ ማንም መምጣቱን ወደማያውቅበት ጸጥ ያለ ስፍራ ለመሄድ ቈረጠ። ከገሊላ በስተ ሰሜን ምዕራብ፥ ከሊባኖስ ተራሮች ማዶ፥ በታላቁ የሜዲትራኒያን ባሕር አጠገብ አንድ ጠባብ አገር ነበረ። ይህ አገር በዚያ ይኖሩ ከነበሩት ከፊንቄያውያን የተነሣ ፊንቄ ይባል ነበር፤ ደግሞም ከሁለቱ ዋና ዋና ከተሞቹ የተነሣ «የጢሮስና የሲዶና አገር» ይባል ነበር። በዚያ አገር የሚኖሩት ሰዎች አይሁድ አልነበሩም፤ ከእነርሱም የአይሁድን ቋንቋ የሚናገሩ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። ኢየሱስ ይህ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለብቻው የሚነጋገርበት ጸጥ ያለ ስፍራ ይሆናል ብሎ አሰበ።
ኢየሱስና ዐሥራ ሁለቱ በጸጥታ ቅፍርናሆምን ትተው በተራሮቹ ላይ በእግር ተጉዘው ወደዚህ ወደ ጢሮስና ሲዶና አገር ሄዱ። በዚያም አንድ ቤት አግኝተው ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር አስበው ገቡበት። ኢየሱስ መምጣቱን ማንም እንዲያውቅ አልወደደም፤ ነገር ግን ሊሰወር አልቻለም። የዚያች አገር አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ ወዲያውኑ ወደ ኢየሱስ ሄደች፥ በእግሩም ላይ ተደፍታ መጥቶ ክፉ መንፈስን ከልጅዋ እንዲያወጣ ለመነችው።
ይህች ሴት ከአይሁድ ወገን አልነበረችም። የሶርያና የፊንቄ ድብልቅ ከሆነው «ከነናውያን» ተብሎ ከሚጠራው ሕዝብ የሆነች ባዕድ ሴት ነበረች። በታላቅ ድምፅ ጮኸች፥ መጮኽዋንም አላቋረጠችም፦
«ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ! ታናሺቱ ልጄ ርኵስ መንፈስ ክፉኛ ያሠቃያታል። እባክህ፥ መጥተህ አትረዳትምን?»
ኢየሱስ መጀመሪያ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱ ግን፥ «መምህር ሆይ! ታላቅ ጩኸት እያሰማች ታውከናለችና ይህችን ሴት አሰናብታት!» አሉት። ለእነርሱ ከአሕዛብ ወገን የሆነች አረማዊት ሴት ብቻ ነበረች፤ አይሁድም፥ ኢየሱስን የሚከተሉት እንኳ፥ እንደ እነዚህ ያሉትን ሰዎች ሁሉ እጅግ ይንቁ ነበር። ኢየሱስ አይሁድን ብቻ ሳይሆን አሕዛብንም ደግሞ ሊያድን እንደ ተላከ አላወቁም ነበር።
ኢየሱስ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰው እንደ አይሁዳዊ ያለ እምነት ሊኖረው እንደሚችል ደቀ መዛሙርቱን ሊያስተምራቸው ወደደ። ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦
«የተላክሁት ለእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ብቻ ነው እንጂ ወደ ወገንሽ አይደለም።»
ሴቲቱ ግን እርሱን መከተልዋን አልተወችም። በኢየሱስ ፊት ተንበርክካ፥ «መምህር ሆይ፥ እርዳኝ!» አለች።
እርሱም፥ «ልጆቹ አስቀድመው ይጠግቡ፤ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም» አላት።
ሴቲቱም፥ «እውነት ነው፥ ጌታ ሆይ፤ ቢሆንም ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይለቅማሉ» አለች።
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፥ «አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው። ልመናሽ እንደ ወደድሽ ተፈጸመልሽ። ክፉው መንፈስ ከልጅሽ ወጥቶ ሄዶአል» አላት።
ሴቲቱም የኢየሱስን ቃል አመነች። ወደ ቤትዋ ፈጥና ሄዳ ልጅዋ ድና በአልጋዋ ላይ ዐርፋ አገኘች።