የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የሕይወት እንጀራ

ምዕራፍ 44 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

የሕይወት እንጀራ

ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን በአምስቱ እንጀራ ካጠገበበት ቀን በኋላ በነበረው ጠዋት፥ ሕዝቡ ኢየሱስን ዳግመኛ ለማየት ተስፋ አድርገው እንደ ገና ተሰበሰቡ፤ አንዳንዶቹም ተአምሩ ወይም ድንቁ ሥራ እንደ ገና እንዲደረግ ይጠብቁ ነበር። በፊተኛው ማታ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በታንኳቸው ወደ ባሕሩ ሲወጡ አይተው ነበር፤ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር እንዳልሄደ አስተውለው ነበር። ኢየሱስ ገና በዚያ ያለ መስሎአቸው በዙሪያው ሁሉ ፈለጉት፤ ደቀ መዛሙርቱን በማዕበሉ ውስጥ ሊረዳቸው በሌሊት በባሕሩ ላይ እንደ ሄደ አላወቁም ነበርና። ኢየሱስን ባላገኙት ጊዜ በቅፍርናሆም ወዳለው ቤቱ ተመልሶ መሆን አለበት ብለው አሰቡ። በዳርቻው ላይ ሌሎች ታንኳዎችን አገኙ፥ በእነርሱም ባሕሩን ተሻግረው ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ።

ኢየሱስንም በቅፍርናሆም ምኵራብ አገኙትና «መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?» አሉት።

ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ «እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ ያያችኋቸውን የኃይል ምልክቶች ስለ ተመለከታችሁ አይደለም፤ ነገር ግን የሰጠኋችሁን እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው። ለዘላለም ሕይወት ለሚኖረው እንጂ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ያንንም እንጀራ የሰው ልጅ ይሰጣችኋል፤ አብ የኃይሉን ማኅተም በእርሱ ላይ አትሞአልና።»

ኢየሱስ ሊሰጣቸው የሚችለው እውነት መብል ለሥጋ ከሚሆነው ይልቅ ለነፍስ እንደሚበልጥ እንዲያስተውሉ ወደደ፤ ይህ እውነት ፈጽሞ የማያልፈውን የእግዚአብሔርን ሕይወት ይሰጣልና።

«እግዚአብሔር እንድንሠራው የሚወደውን ሥራ በምን መንገድ ልንሠራ እንችላለን?» ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስም መልሶ፥ «እግዚአብሔር እንድትሠሩት የሚወደው ሥራ ይህ ነው፤ መልእክተኛው አድርጎ ወደ እናንተ በላከው እንድታምኑ ነው» አለ።

ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦ «እንግዲያስ ከእግዚአብሔር እንደ መጣህ የሚያረጋግጥ ምልክት አሳየን፤ ያን ጊዜ እናምንብሃለን። ምን ሥራ ትሠራለህ? አባቶቻችን ከሙሴ ጋር በምድረ በዳ ሳሉ ሙሴ የሰጣቸውን መና በሉ። ‹ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው› ተብሎ እንደ ተጻፈ ታስታውሳለህ።»

አያችሁ፥ ሕዝቡ ኢየሱስ የእንጀራውን ተአምር እንደ ገና በማድረግና በዚያው ዓይነት ተጨማሪ እንጀራ በመስጠት ኃይሉን ዳግመኛ እንዲያሳያቸው ፈልገው ነበር።

ኢየሱስም መልሶ፥ «በእውነት እላችኋለሁ፥ ከሰማይ እንጀራ ለአባቶቻችሁ የሰጣቸው ሙሴ አይደለም፤ አባቴ ጌታ እግዚአብሔር ነው እንጂ። አባቴም አሁን እውነተኛውን እንጀራ ከሰማይ ይሰጣችኋል። የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና» አለ።

እነርሱም፥ «ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን!» አሉት።

ኢየሱስም መልሶ፥ «ሕይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ። ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፥ በእኔ የሚያምንም ከቶ አይጠማም። ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ አይታችሁኛል፥ ዳሩ ግን አላመናችሁብኝም። አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም። የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለመፈጸም ከሰማይ አልወረድሁምና፤ የእርሱም ፈቃድ ይህ ነው፤ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ ስንኳ እንዳላጠፋ፥ ነገር ግን በታላቁ የመጨረሻ ቀን ወደ ሕይወት እንዳስነሣቸው ነው። ልጅን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ነውና፤ እኔም ራሴ በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ» አለ።

ኢየሱስን የሰሙት አይሁድ፥ «ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ» ስላለ ያንጐራጕሩበት ጀመር።

«ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? አባቱንና እናቱን እናውቃቸዋለን። ‹ከሰማይ ወርጃለሁ› እንዴት ይላል?»

ቃሉን ሊያስተውሉ አልቻሉም፤ የእንጀራውን ተአምር ዳግመኛ ስላላደረገላቸውም ተቈጡበት። ደግሞም ኢየሱስ እነርሱ እንደሚፈልጉት ዓይነት ንጉሥ ሊሆን እንደማይወድ አሁን አወቁ፤ በዙፋን ላይ የሚቀመጥ፥ በቤተ መንግሥት የሚኖር፥ ሮማውያንን የሚያባርር ሠራዊት የሚያሰልፍ፥ አይሁድንም በምድር ላይ ገዥ ሕዝብ የሚያደርግ ንጉሥ ሊሆን አልፈለገም። ቀደም ብለን እንዳየነው ጊዜው የፋሲካ ወራት ነበር፤ በኢየሱስ ዙሪያ ታላቅ ሕዝብ የተሰበሰበበትም አንዱ ምክንያት፥ ሁሉም ሕዝቡን ወደ ኢየሩሳሌም መርቶ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ስፍራውን ይይዛል ብለው ይጠብቁ ስለ ነበር ነው። ነገር ግን ኢየሱስ በዚህ ዓመት እንደ ልማዱ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ በዓሉ አልሄደም፤ ለራሱና ለደቀ መዛሙርቱ ሌላ ዕቅድ ነበረውና።

ኢየሱስን የሚከተለው ሕዝብ እነርሱ እንደሚመኙት ንጉሥ እንደማይሆን፥ እንዲመለከቱትም ድንቅ እንደማያደርግላቸው፥ ቃሉም ሊያስተውሉት የማይችሉት እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉም ማለት ይቻላል ከኢየሱስ ዞር አሉ። ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻ ከእርሱ ጋር ትተዋቸው ሄዱ።

ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፥ «እናንተ ደግሞ ልትተዉኝ ትወዳላችሁን?» አላቸው።

ስምዖን ጴጥሮስም ስለ ሁሉም መልሶ እንዲህ አለ፦ «ጌታ ሆይ፥ አንተን ትተን ወደ ማን እንሄዳለን? የዘላለም ሕይወት የሚሰጡን ቃሎች በአንተ ዘንድ አሉ። እኛም አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደ ሆንህ አምነናል፥ በእርግጥም አውቀናል።»

እነዚህ ሰዎች የኢየሱስን ቃል ሁሉ አላስተዋሉም ነበር፤ ነገር ግን እርሱን መውደድንና የተስፋው ንጉሥ እንደ ሆነ ማመንን ተምረው ነበር። እስከ ሞት ድረስ ከእርሱ ጋር ለመኖር ተዘጋጅተው ነበር።

ኢየሱስም፥ «ዐሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ይሁን እንጂ ከእናንተ መካከል እንኳ የዲያብሎስን ሥራ የሚሠራ አንድ አለ» አለ።

ስለ ማን እንደሚናገር አላወቁም ነበር፤ እርሱ ግን የአስቆሮቱ የስምዖን ልጅ ስለ ሆነው ስለ ይሁዳ ተናገረ፤ ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከአንድ ዓመት በኋላ መምህሩን ለሞት አሳልፎ የሚሰጠው እርሱ ነበር። በዚያን ጊዜ ይሁዳ ራሱ ይህን አያውቅም ነበር። የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችለው ኢየሱስ ግን ይህን አሰቃቂ ሥራ እንደሚሠራ፥ ይሁዳ ራሱ የማያውቃቸውን ምልክቶች በእርሱ ውስጥ አየ።


ቀዳሚ ቀጣይ