የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ዘፈንና ዋጋው

ምዕራፍ 41 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ዘፈንና ዋጋው

ኢየሱስ በገሊላ ሲያስተምርና ሲሰብክ በነበረበት ዓመት ሙሉ ማለት ይቻላል፥ መጥምቁ ዮሐንስ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በሙት ባሕር አጠገብ ማኬሮስ በተባለ ገለልተኛ ስፍራ በሄሮድስ ወኅኒ ታስሮ ነበር። ዮሐንስ ለሄሮድስ የወንድሙን ሚስት ወስዶ የራሱ ሚስት ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነ በነገረው ጊዜ፥ የንጉሥ ሄሮድስ ንግሥት ሄሮድያዳ ስለ ተቈጣችበት ዮሐንስ ወደ ወኅኒ እንደ ተጣለ ታስታውሳላችሁ። ሄሮድያዳ ዮሐንስን ጠልታ ብዙ ጊዜ ልታስገድለው ሞከረች፤ ሄሮድስ ግን ዮሐንስን እጅግ ያከብረው ነበርና እንዲገደል አልፈቀደም።

በመጨረሻ ግን ሄሮድያዳ ያሰበችውን የምትፈጽምበት አጋጣሚ መጣላት። ንጉሥ ሄሮድስ በተወለደበት ቀን፥ ወኅኒ ብቻ ሳይሆን ቤተ መንግሥትም በነበረው በማኬሮስ፥ ለመኳንንቱ፥ ለሠራዊቱ አለቆችና ለመንግሥቱ ታላላቅ ሰዎች ታላቅ ግብዣ አደረገ። በዚህ ግብዣ የሄሮድያዳ ልጅ የሆነች አንዲት ወጣት ብላቴና ገብታ በተሰበሰቡት ፊት ዘፈነች። ሄሮድስና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንግዶች በብላቴናይቱ ዘፈን እጅግ ደስ ስለ ተሰኙ ንጉሡ እጅግ የሞኝነት ቃል ገባላት። እንዲህም አላት፦

«የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ።» ከዚህም አልፎ በመሐላ እንዲህ ብሎ ማለላት፦ «የመንግሥቴ እኩሌታ ስንኳ ቢሆን የምትመርጪውን ሁሉ እሰጥሻለሁ።»

ብላቴናይቱ ወደ እናትዋ ሄዳ፦ «ምን ልለምነው?» አለቻት።

ሄሮድያዳም በጥላቻ ድምፅ፦ «የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ ለምኚ» አለች።

ብላቴናይቱም ፈጥና ወደ ንጉሡ ገብታ፦ «የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን ልትሰጠኝ እወዳለሁ» አለች።

ንጉሡም እጅግ አዘነ፥ ተቈጣም። ብላቴናይቱ ይህን እንድትመርጥ ያደረጋት ሚስቱ ሄሮድያዳ እንደ ሆነች ያውቅ ነበርና ቃሉን ቢያጥፍ በወደደ ነበር። ነገር ግን ቃሉን ስለ ሰጠና በግብዣው ላይ በነበሩት መኳንንት ሁሉ ፊት ቃሉን መመለስ ስላሳፈረው፥ ፈቃድዋ እንዲፈጸም ሳይወድ ለጠባቂዎቹ ትእዛዝ ሰጠ። እነርሱም ወደ ወኅኒው ገብተው በመንግሥቱ ሁሉ ከሰው ሁሉ የሚበልጠውንና እጅግ የከበረውን የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በተሳለ ሰይፍ ቈረጡ። ራሱንም በወጭት አድርገው ለወጣቲቱ ብላቴና ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወሰደችው። እንዲህ ኢየሱስ «ነቢይ፥ ከነቢይም የሚበልጥ» ብሎ የጠራው ሰው የአንዲት ዘፋኝ ልጃገረድና የክፉ እናትዋን ምኞት ለማርካት ተገደለ!

ከዮሐንስ ጋር እስከ መጨረሻ የተጣበቁትና በወኅኒ ይጐበኙት የነበሩት ጥቂት ተከታዮቹ ራስ የሌለውን በድኑን ወስደው ቀበሩት። ከዚያም ወደ ኢየሱስ ሄደው የዮሐንስን ሞት አሳዛኝ ታሪክ ሁሉ ነገሩት።

ሄሮድስ ግን ከመጥምቁ ዮሐንስ ገና አልተገላገለም ነበር። ብዙም ሳይቆይ በዮሐንስ ስፍራ ስለ ተነሣው ስለ አዲሱ ነቢይ ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ አስደናቂ ወሬ ይሰማ ጀመር። ኢየሱስ አስደናቂ ኃይል እንደሚያሳይ፥ ድውዮች እንደሚፈወሱ፥ ለምጻሞች እንደሚነጹ፥ ዕውሮች እንደሚያዩ፥ ከሁሉም ይልቅ የሚያስደንቀው ደግሞ ሙታን ወደ ሕይወት እንደሚነሡ ሰማ።

ሰዎች እርስ በርሳቸው፦ «ይህን ተአምራት ሁሉ የሚያደርግ ይህ ታላቅ ነቢይ ማን ነው?» ይባባሉ ነበር።

አንዳንዶቹ፦ «ይህ እንደ ገና ወደ ምድር የመጣው የጥንቱ ነቢይ ኤልያስ ነው» አሉ።

ሌሎችም፦ «ኤልያስ ካልሆነ ኤርምያስ ወይም ከጥንት ነቢያት አንዱ ሊሆን ይችላል» አሉ።

ሄሮድስ ግን ስለ ክፉ ሥራው ሕሊናው ይወቅሰው ነበርና በአስፈሪ ፍርሃት ተሞላ። እንዲህም አለ፦

«ይህ ማን እንደ ሆነ አውቃለሁ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት መጥምቁ ዮሐንስ ነው። እንደ ገና ሕያው ሆኖ ተነሥቶአል። ይህ ሁሉ አስደናቂ ነገር የሚሆነው በእርሱ ምክንያት ነው!»

እንዲህ የመጥምቁ የዮሐንስ ደም የፈሰሰበት ራስ እንደ አስፈሪ መንፈስ በንጉሡ በሄሮድስ ዓይን ፊት ተነሣ!


ቀዳሚ ቀጣይ