የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የተላኩት ዐሥራ ሁለቱ ሰባኪዎች

ምዕራፍ 40 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

የተላኩት ዐሥራ ሁለቱ ሰባኪዎች

ኢየሱስ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ከመካከለኛው ክፍል በቀር በገሊላ ክፍሎች ሁሉ ማለት ይቻላል ሰብኮ ነበር፤ ያ መካከለኛው ክፍል በልጅነቱ የኖረባት የናዝሬት አካባቢ ነበር። ከይሁዳ ከመጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በናዝሬት ለመናገር በሞከረ ጊዜ፥ ሕዝቡ እርሱን ሊሰሙት እንዳልፈቀዱ ታስታውሳላችሁ፤ ረቢ ወይም ጸሐፊ ሳይሆን ተራ ሠራተኛ ብቻ የነበረ ሰው ምንም ሊያስተምራቸው አይችልም ብለው አስበው ነበርና።

ነገር ግን ኢየሱስ እነዚያን የናዝሬት ሰዎች ይወዳቸው ነበር፤ ከወንዶቹ ብዙዎቹ በልጅነቱ ከእርሱ ጋር በትምህርት ቤት ነበሩና፤ የገዛ እኅቶቹም ከልጆቻቸው ጋር በዚያ ይኖሩ ነበር፤ እነዚያም ወንዶችና ሴቶች ልጆች የወንድምና የእኅት ልጆቹ ነበሩ። ሁሉንም ሊያያቸው ናፈቀ፤ ስለዚህ እንደ ገና ወደ ናዝሬት ሄዶ ሕዝቧ በዚህ ጊዜ ይሰሙት እንደ ሆነ ሊያይ ቈረጠ። በቀድሞው ጕብኝቱ ብቻውን ነበር፤ የናዝሬትም ሰዎች በቍጣቸው እጅግ ገደላማ ከሆነ ኮረብታ ላይ ወርውረው ሊገድሉት ሞክረው ነበር፤ አሁን ግን ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱና ከስፍራ ወደ ስፍራ የሚከተሉት ሌሎች ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ። በዚህ ጕብኝት የናዝሬት ሰዎች በዙሪያው ስላሉት ስለ ብዙ ወዳጆቹ ሊጎዱት አልደፈሩም።

እንደ ቀድሞው ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ መንደሩ የጸሎት ቤት ሄዶ ሰበከ። ሕዝቡም እንደ ገና በቃሉ እየተደነቁ አደመጡት፤ ነገር ግን እንደ ገና እንዲህ አሉ፦

«ይህ ለእኛ ማረሻና መቈፈሪያ ጠረጴዛም ይሠራልን የነበረው አናጢው አይደለምን? እንዴት ሊያስተምረን ይችላል?»

ሕዝቡ ስላላመኑበት ከታላላቅ ሥራዎቹ ጥቂቶችን ብቻ ሊያደርግ ቻለ። በእርግጥ በጥቂት ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው፤ ነገር ግን ብዙ ዓመታት በመካከላቸው በኖረባቸው ሰዎች የልብ ድንዳኔ ከመደነቅ በቀር ሌላ ሊያደርግ አልቻለም።

ኢየሱስ በሐዘን ልብ ናዝሬትን ትቶ በመካከለኛው ገሊላ ባሉት መንደሮች እየዞረ በጸሎት ቤቶች ያስተምርና ልዩ ልዩ በሽታን ይፈውስ ነበር። ሕዝቡ ምን ያህል ድሆች እንደ ሆኑ፥ ስለ እውነት ምን ያህል ጥቂት እንደሚያውቁና ምን ያህልም እንደሚናፍቁት ባየ ጊዜ፥ እጅግ አዘነላቸው። ለኢየሱስ እረኛ እንደሌላቸው እንደ ጠፉና እንደ ተቅበዘበዙ በጎች መሰሉት። ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፦

«መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው። መከሩን እንዲሰበስቡለት ሠራተኞችን እንዲልክ የመከሩን ጌታ አጥብቃችሁ ለምኑት።»

ኢየሱስ በገሊላ የሚሠራው ሥራ ጊዜ ሊፈጸም መቃረቡን ያውቅ ነበር። ገና ያልሰበከባቸው ሌሎች የእስራኤል ምድር ክፍሎች ነበሩ፤ እነርሱንም ሊጐበኝ ወደደ። ደግሞም ከእርሱ በቀር ማንም ያላወቀውን ነገር ያውቅ ነበር፤ ይኸውም በአንድ ዓመት ውስጥ ከምድር እንደሚወሰድና ደቀ መዛሙርቱም ሥራውን እንዲቀጥሉና የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ለሕዝብ ሁሉ እንዲሰብኩ ብቻቸውን እንደሚቀሩ ነው። ስለዚህ «ሐዋርያት» ብሎ የሰየማቸውን ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ሊልካቸውና እርሱ ሊጐበኛቸው ጊዜ ባላገኘባቸው በገሊላ መንደሮች በመስበክ ሥራቸውን እንዲጀምሩ ሊያደርግ ቈረጠ።

ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን በአንድነት ጠራቸው፤ እርስ በርሳቸውም እንዲረዳዱ ሁለት ሁለት አድርጎ ከፋፈላቸው። በሽታዎችን እንዲፈውሱና ክፉ መናፍስትን ከሰዎች እንዲያወጡ ከገዛ ኃይሉ ሰጣቸው። ስለ ሥራቸውም፥ ወደ ማን እንዲሄዱና እንዴት እንዲሠሩ ትእዛዝ ሰጣቸው። እንዲህም አለ፦

«ከአሕዛብ፥ ማለትም ከባዕድ ሰዎች ከተማ ወደ አንዲቱም አትሂዱ፤ ከሳምራውያንም መንደሮች ራቁ። አሁን ሥራችሁ ከእስራኤል ቤት ከጠፉት በጎች መካከል ነው። በምድሪቱ ሁሉ ወዳሉት አይሁድ ሂዱ፥ የእግዚአብሔርም መንግሥት እንደ መጣችና ሊገቡባትም እንደሚችሉ ንገሩአቸው። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ ክፉ መናፍስትን ከሰዎች አውጡ። የእግዚአብሔርን ስጦታ በከንቱ ተቀብላችኋልና ዋጋ ሳትቀበሉ በከንቱ ስጡ።»

«ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ለመንገድም ስንቅ የምትይዙበት ከረጢት፥ ሁለት እጀ ጠባብም፥ ጫማም አትያዙ፤ ነገር ግን በእግራችሁ ነጠላ ጫማ ብቻ አድርጋችሁ ሂዱ። የእግዚአብሔር ሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና፥ ይሰጠውማል።»

«ወደ መንደር በገባችሁ ጊዜ አንድ ደግ ሰው ጠይቁ፥ ወደ ቤቱም ሂዱ፥ በዚያም መንደር እስካላችሁ ድረስ በዚያ ተቀመጡ። ከቤት ወደ ቤት እየዞራችሁ አትጐብኙ። ወደ ቤት ስትገቡ ‹ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን› በሉ። በዚያ ቤት የሚኖሩ ሰዎች ለሰላማችሁ የሚገባቸው ቢሆኑ ሰላም ይሰጣቸዋል፤ የማይገባቸው ቢሆኑ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል። በማናቸውም ስፍራ ሕዝቡ ባይሰሙአችሁና ባይቀበሉአችሁ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ ለምልክት ነጠላ ጫማችሁን አውልቃችሁ የዚያን ስፍራ ትቢያ ከእርሱ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን እግዚአብሔር እሳትን ካዘነበባቸው ከሰዶምና ከገሞራ ከተሞች ይልቅ እናንተን ላልተቀበሉ ከተሞች የከፋ ይሆንባቸዋል።»

«እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል ትላካላችሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ። ነገር ግን ክፉ ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋልና ከእነርሱ ተጠበቁ፤ በፍርድ ቤቶቻቸውም ትገረፋላችሁ፤ ተከታዮቼ ስለ ሆናችሁም ወደ ገዥዎችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ። ለፍርድ ባቀረቡአችሁ ጊዜ ምን እንድትናገሩ ወይም እንዴት እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት በሚያስፈልጋችሁ ጊዜ ይሰጣችኋልና። በእናንተ የሚናገር በሰማያት ያለው የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።»

ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ሌላ ብዙ ቃል ተናገረ፤ በመመሪያውም መጨረሻ ይህን አለ፦

«እናንተን የሚቀበልና የሚሰማችሁ ሁሉ እኔን መምህራችሁን እንደ ተቀበለ ነው፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን አባቴን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል። ደግ ሰውንም ደግ ሰው ስለ ሆነ የሚቀበል የደግ ሰውን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ደቀ መዝሙሬ ስለ ሆነ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ እንኳ የሚሰጥ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።»

ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ትእዛዙን ከሰጠ በኋላ እንዲሰብኩ ላካቸው፤ እርሱ ራሱም የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ለሕዝቡ እየነገረ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሄደ።


ቀዳሚ ቀጣይ