ምዕራፍ 42 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
አምስት እንጀራ የያዘው ብላቴና
ንጉሡ ሄሮድስ ቅዱሱን ነቢይ መጥምቁን ዮሐንስን እንደ ገደለው የሚገልጸው ወሬ የሰሙትን ሁሉ በድንጋጤ አንቀጠቀጣቸው። ወሬውም በገሊላ መንደሮች የስብከት ሥራቸውን ሊፈጽሙ ለተቃረቡት ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ደረሰ። ሄሮድስ ይዞ ወደ ወኅኒ እንዳያስገባቸው ፈሩ፤ ነገር ግን ከራሳቸው ይልቅ ስለ መምህራቸው እጅግ ተጨነቁ። ኢየሱስን ለሕዝቡ ያስታወቀውን ዮሐንስን ከገደለ በኋላ ሄሮድስ አሁን ኢየሱስን ራሱን ሊገድለው ይሞክር ይሆናል ብለው ፈሩ።
ሁሉም ፈጥነው ወደ ቅፍርናሆም መጡ፤ በዚያም ኢየሱስን አገኙት፤ የጐበኙአቸውን ስፍራዎች፥ ሰዎችን በመፈወስና በመርዳት የሠሩትን ሥራ፥ ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት በየስፍራው የሰጡትን መልእክት ነገሩት። ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ዙሪያ ያለው ሕዝብ ከቀድሞው ሁሉ ይልቅ በዝቶ አገኙት፤ ይህም የሆነው የእነዚህ ደቀ መዛሙርት ስብከት ሰዎች ስለ ኢየሱስ እንዲያስቡ አነሣሥቶ ብዙዎች ቤታቸውን ትተው እንዲፈልጉት ስላደረጋቸው ብቻ አልነበረም፤ ከአይሁድ በዓላት ሁሉ የሚበልጠው የፋሲካ በዓል ሊከበር ቀርቦ ነበርና የቅፍርናሆም ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ባሉ ሰዎች ተጨናንቃ ነበር፤ ይህ በዓል በዚያች ከተማ ብቻ ይከበር እንደ ነበረና ሕዝብም በዓሉን ለማክበር ከምድሪቱ ክፍል ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ እንደ ነበረ ታውቃላችሁ።
የሚመጡና የሚሄዱ ሰዎች፥ ኢየሱስንም የሚፈልጉና በሽታቸውን እንዲፈውስላቸው ኃይሉን የሚሹ እጅግ ብዙዎች ስለ ነበሩ፥ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ። ሕዝቡ ዘወትር ይጋፉአቸው ነበር። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦
«ኑ፥ ታንኳውን ይዘን ባሕሩን ተሻግረን ከሕዝቡ ርቀን ወደ አንድ ጸጥ ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ጥቂት እንረፍ።»
ወደ ታንኳውም ገብተው ባሕሩን ቀዝፈው መሻገር ጀመሩ። ነገር ግን ሕዝቡ ሲሄዱ አዩአቸው፤ ብዙዎችም ሊከተሉአቸው ሞከሩ። ታንኳ ያላቸው ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተሳፈሩበት ታንኳ ሲሄድበት ባዩት አቅጣጫ በታንኳዎቻቸው ተከተሉ። ሌሎቹ ደግሞ፥ እጅግ ብዙ ሕዝብ፥ በባሕሩ ራስ ዙሪያ እየተራመዱና እየሮጡ፥ የዮርዳኖስን ወንዝ ወደ ገሊላ ባሕር በሚገባበት ስፍራ በእግራቸው ተሻገሩ፤ የኢየሱስንም ታንኳ ከዓይናቸው ሳያርቁ፥ ኢየሱስ በሰሜን ምሥራቅ ዳርቻ በነበረችው በቤተ ሳይዳ ከተማ አጠገብ ሲወርድ ሊቀበሉት በባሕሩ ዳር ደርሰው ጠበቁት። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ በሰላም ነበር፤ ቤተ ሳይዳ ከንጉሥ ሄሮድስ ግዛት ውጭ ሆና የሄሮድስ ወንድም ፊልጶስ በሚገዛው ምድር ነበረችና።
ኢየሱስ በቤተ ሳይዳ አጠገብ ከታንኳው ወርዶ ወደ ባሕሩ ዳር በወጣ ጊዜ፥ በዚያ እጅግ ብዙ ሕዝብ አገኘ፤ ከሴቶችና ከልጆች ሌላ ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ወንዶች ነበሩ። ኢየሱስ ምን ያህል እንደ ጓጉና እርሱን በማግኘታቸው ምን ያህል ደስ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ የፍቅርና የርኅራኄ ልቡ ወደ እነርሱ ተሳበ። ያመጡአቸውንም አንዳንድ ድውዮች ፈወሰ፥ ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገራቸው።
ቀኑ ሊመሽ ጀመረ፤ ፀሐይም ከገሊላ ኮረብቶች በስተ ጀርባ ልትጠልቅ በተቃረበች ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን እንዲህ አሉት፦
«መሽቶአል፥ ብዙም ሳይቆይ ሌሊት ይሆናል። እነዚህ ብዙ ሰዎች በድንገት ስለ መጡ የሚበሉትን ምንም ይዘው አልመጡም። ወደ ቤተ ሳይዳ ከተማና በዙሪያዋ ወዳሉ መንደሮች ሄደው ምግብ እንዲገዙና የሚያድሩበትን ስፍራ እንዲያገኙ አሰናብታቸው። እንደምታየው ያለንበት ምግብም ማደሪያም የሌለበት ምድረ በዳ ነው።»
ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱን፦ «ሊሄዱ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው» አላቸው።
እነርሱም፦ «እያንዳንዳቸው ጥቂት ጥቂት እንዲያገኙ ወደ ከተማ ሄደን በሠላሳ ዶላር እንጀራ እንግዛላቸውን?» አሉት።
ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ዘወር ብሎ፦ «ፊልጶስ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ሁሉ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እናገኛለን?» ብሎ ጠየቀው።
ኢየሱስ ይህን የተናገረው የፊልጶስን እምነት ሊፈትን ነበር፤ እርሱ ራሱ የሚያደርገውን አስቀድሞ ያውቅ ነበርና። ፊልጶስም በሜዳው ላይ የተሰበሰበውን ሕዝብ ተመልክቶ፦ «ለእያንዳንዳቸው ትንሽ ቍራሽ እንኳ ለመስጠት የሠላሳ ዶላር እንጀራ አይበቃም» ብሎ መለሰ።
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፦ «ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ» አላቸው።
በዚያን ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ሌላው፥ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፥ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፦ «አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ትናንሽ ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይጠቅማል?» አለው።
ኢየሱስም፦ «ወደ እኔ አምጡአቸው» አለ።
ስለዚህ ይህን ብላቴና የምሳ መሶቡን እንደ ያዘ ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ በመሶቡም ውስጥ እናቱ አምስት ትልልቅ ስስ የገብስ ቂጣና ሁለት ትናንሽ ጨው የተነከሩ ዓሦች አስቀምጣለት ነበር።
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፦ «ወደ ሕዝቡ መካከል ሂዱና በእያንዳንዱ ክፍል አምሳ ወይም መቶ ሰዎች እየሆኑ በየክፍሉ እንዲሰለፉና በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ ንገሩአቸው» አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ ሁሉ አምሳ አምሳና መቶ መቶ እየሆኑ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው በመሬት ላይ ተቀመጡ። በለመለመው ሣር ላይ በረድፍና በአራት ማዕዘን ተሰልፈው ልዩ ልዩ ቀለም ያለው ልብሳቸውን ለብሰው ሲቀመጡ የአበባ ማሳ መሰሉ።
ከዚያም ኢየሱስ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ያዘ። ሁሉም ዝም እንዲሉ እጁን አወዛወዘ፤ ሁሉም ጸጥ ባሉ ጊዜም ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየ፥ ስለ ምግቡ ስጦታ እግዚአብሔርን አመሰገነ፥ ባረከውም። እንደ ትልቅ ስስ ብስኩት ወይም ቂጣ የነበሩትን እንጀራዎች ቈረሰ፤ ለእያንዳንዱ ደቀ መዝሙርም ቍራሽ እንጀራና ቍራሽ የደረቀ ዓሣ ሰጠ። ደቀ መዛሙርቱም ከእንጀራውና ከዓሣው እየቈረሱ ለሕዝቡ እያደሉ በመካከላቸው ተመላለሱ። ሲቈረሱም እንጀራውና ዓሣው በእጃቸው እየበዙ ሄዱ፤ በዚያ ያሉትም ሁሉ በልተው ጠገቡ።
ከዚያም ኢየሱስ፦ «አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ ሄዳችሁ አከማቹ» አለ።
ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት እያንዳንዱ መሶብ ይዞ በሕዝቡ መካከል ተመላለሰ፤ የተረፈውንም ሁሉ ከእነርሱ ሰበሰበ። ወደ ኢየሱስ በተመለሱ ጊዜ ዐሥራ ሁለቱም መሶቦች ከእንጀራውና ከዓሣው በተረፈ ቍርስራሽ ተሞልተው ነበር። በመጀመሪያ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነበር። ከእነዚህም ከሴቶችና ከልጆች ሌላ አምስት ሺህ ወንዶች የፈለጉትን ያህል በልተው ነበር። አሁን ደግሞ የተረፈ ቍርስራሽ የሞላባቸው ዐሥራ ሁለት መሶቦች ተመለሱ፤ ሁሉም ከበሉ በኋላ በመጨረሻ የተረፈው በመጀመሪያ ከነበረው እጅግ የበለጠ ነበር።
ሕዝቡም የሚፈልጉትን ያህል ምግብ ሊሰጣቸው የሚችል ሰው በዚህ እንዳለ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፦ «ንጉሥ እንዲሆንልን የምንፈልገው ይህ ሰው ነው! ሳንሠራ የምንበላውን እንጀራ ሊሰጠን ይችላል። ከሮማውያን አገዛዝ ተላቅቀን ኢየሱስን ንጉሣችን እናድርገው!» ተባባሉ።
ኢየሱስ ሁሉን ያውቅ ነበርና አሳባቸውንና እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩትን አወቀ። ደግሞም እርሱ ንጉሥ እንደ ሆነ ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን እነርሱ እንደሚፈልጉት ያለ ንጉሥ አልነበረም። መንግሥቱ በሠራዊትና በሰይፍ የሚገኝ መንግሥት ሳይሆን በሚወዱት ሰዎች ልብ ውስጥ የሚሆን ነበር። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ሕዝቡ ኢየሱስን ወዲያውኑ ንጉሣቸው አድርገው ሊያነግሡት በመጓጓታቸው ደስ እንዳላቸው አወቀ፤ ይህ ቢሆን ለእነርሱ ለራሳቸው ከፍተኛ ማዕረግና ሹመት ይሆንላቸው ነበርና።
ስለዚህ ኢየሱስ በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን አሰናበታቸው። ምንም እንኳ ባይወዱ ወደ ታንኳው እንዲገቡና ባሕሩን ቀዝፈው ወደ ቅፍርናሆም እንዲሻገሩ ግድ አላቸው። ደቀ መዛሙርቱን ካሰናበተ በኋላ ሕዝቡንም አሰናበተ፤ እነርሱም ደግሞ ሊሄዱ አልወደዱም ነበር፤ ኢየሱስ ንጉሥ እንዲሆን ስለ ምን እንደማይቀበል ሊገባቸው አልቻለምና።
ሁሉም ከሄዱና በዙሪያው ጸጥታ ከሆነ በኋላ፥ ሌሊቱም በገባ ጊዜ፥ ኢየሱስ በአቅራቢያው ወዳለ ተራራ ራስ ወጥቶ ወደ ሰማያዊ አባቱ እየጸለየ ጥቂት ሰዓታትን አሳለፈ። ጸሎት ያስፈልገው ነበር፤ በዚህ እርሱን ለማንገሥ በተደረገው ሙከራ ሰይጣን ሰማያዊ ያይደለ ምድራዊ መንግሥት በመስጠት ኢየሱስን ከኃይሉ በታች ለማድረግ ያደረገውን ሌላ ጥረት አይቶ ነበርና።