የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ለዕውሮች ማየት፥ ለዲዳውም መናገር

ምዕራፍ 39 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

ለዕውሮች ማየት፥ ለዲዳውም መናገር

ኢየሱስ ታናሺቱን ልጅ ከሞት ካስነሣበት ቤት ሲወጣ ሁለት ዕውሮች አገኙት፤ ወደ ቅፍርናሆም የመመለሱ ወሬ ተሰምቶ ነበርና፥ እነዚህም ሁለት ሰዎች ማየትን ለማግኘት ጓጉተው ኢየሱስን ለመፈለግ ወዲያው ወጡ። በመንገድም ኢየሱስን እየተከተሉ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያሉ ጮኹ፦

«የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን!»

ኢየሱስ ዳዊት ከብዙ ዘመን በፊት ራስ ከሆነለት ቤተ ሰብ እንደ መጣ ታውቃላችሁ። ሕዝቡም ሁሉ ከዳዊት የተወለደ ስለ ሆነ የዳዊትን ዙፋን እንዲወርስና እንደ ዳዊትም በምድሪቱ ሁሉ ላይ ንጉሥ እንዲሆን ይጠብቁት ነበር። ኢየሱስ ንጉሥ እንደሚሆን ያመኑት ሰዎች ብዙ ጊዜ «የዳዊት ልጅ» ብለው ይጠሩት ነበር።

እነዚህ ሁለት ዕውሮች ኢየሱስ ወደሚኖርበት ቤት እስኪገባ ድረስ ወደ እርሱ እየጮኹ ተከተሉት፤ ያም ቤት ስምዖን ጴጥሮስ ይኖርበት የነበረው ቤት ሳይሆን አይቀርም። ዕውሮቹም ኢየሱስን ተከትለው ወደ ቤቱ ገቡ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦

«የምትፈልጉትን ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን?»

እነርሱም «አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ እንደምትችል እናምናለን» ብለው መለሱለት።

ኢየሱስም እጆቹን በዓይኖቻቸው ላይ ጫነ፤ በመጀመሪያ በአንደኛው ሰው፥ ቀጥሎም በሁለተኛው ላይ። ዓይኖቻቸውንም ሲዳስስ «እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ» አላቸው።

ወዲያውም ዓይኖቻቸው ተከፈቱ፤ ማየትም ቻሉ። ኢየሱስም በብርቱ ተናገራቸው፤ «ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ» ብሎ የተለየ ትእዛዝ ሰጣቸው።

ሁልጊዜ የፈውስ ተአምራትን የሚሹ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው እንዲኖሩ አልፈለገም፤ የሰዎችን ሰውነት ከመፈወስ ይልቅ ለነፍሶቻቸው የሚሰብክበት የሚበልጥ ሥራ እንዳለው ተሰምቶት ነበርና። እነዚህ ሰዎች ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገላቸውን ድንቅ ነገር ላገኙት ሁሉ ተናገሩ። ቢከለክላቸውም እንኳ ስለዚህ ቢናገሩ የሚያስደንቅ አልነበረም፤ ቀድሞ ዕውሮች ሆነው የሚያውቁአቸው ሁሉ አሁን ማየት በመቻላቸው በመልካቸው ላይ የሆነውን ታላቅ ለውጥ አይተው ይህ እንዴት እንደ ሆነ ይጠይቁአቸው ነበር፤ ስለዚህ ለሰዎች ከመናገር መቈጠብ ቀላል አልነበረም። ነገር ግን ወሬው በተነገረበት ስፍራ ሁሉ በሽታ ያለባቸው፥ ዕውሮች፥ ደንቆሮችና ዲዳዎች ወይም አንካሶች ኢየሱስን አግኝተው ለመዳን በመሻት ተሞሉ።

እነዚህ ሁለት ሰዎች ከዕውርነታቸው ተፈውሰው ኢየሱስን ትተው ከሄዱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሌላ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ። እርሱም ርኵስ መንፈስ ያደረበት ዲዳ ሰው ነበር። ኢየሱስ ርኵሳን መናፍስት በሰዎች ላይ ሰልጥነው ባገኛቸው ጊዜ ሁሉ ልመና ሳይጠብቅ ሁልጊዜ ያወጣቸው ነበር። ይህንም ርኵስ መንፈስ ተናገረው፤ እርሱም ሰውየውን ትቶ ወጣ። ከዚያም ሰውየው ወዲያው መናገር ጀመረ፤ ዲዳ ያደረገው በውስጡ የነበረው ርኵስ መንፈስ ነበርና። ሕዝቡም ሁሉ ተደነቁና እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦

«እንዲህ ያለ ኃይል በእስራኤል ምድር ከቶ ከዚህ በፊት አልታየም!»

የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት ጻፎችና ፈሪሳውያን ግን ቀድሞ እንደ ተናገሩት እንደ ገና እንዲህ አሉ፦

«ይህ ሰው ርኵሳን መናፍስትን የሚያወጣው የርኵሳን መናፍስት አለቃ ሰይጣን ስለሚረዳው ነው።»


ቀዳሚ ቀጣይ