ምዕራፍ 3 · 5 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ
በጌታ ምድር የነበሩ ሕዝብ
በኢየሱስ ዘመን በፍልስጤም ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ማለት ይቻላል የአይሁድ ዘር ነበሩ። ኢየሱስ ከመምጣቱ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት አብርሃም የሚባል አንድ ታላቅ ሰው በዚያ አገር ይኖር ነበር። ለዚህ ሰው እግዚአብሔር ልጆቹና ከእነርሱም በኋላ የልጆቻቸው ልጆች ለብዙ ዘመናት በዚያ አገር እንዲኖሩና እንዲወርሱት ተስፋ ሰጠው። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ይባል ነበር፤ የይስሐቅም ልጅ ያዕቆብ ይባል ነበር። የፍልስጤም ሰዎች ሁሉ ከያዕቆብ ቤተ ሰብ የተገኙ ነበሩ፤ ኢየሱስም በመጣ ጊዜ እንደሚጠሩት እነዚህ የያዕቆብ ዘሮች በቍጥር ብዙ ሚሊዮኖች ሆነው ነበር፤ ከፍልስጤምም ሌላ በሌሎች አገሮች ይገኙ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከሌላው አገር ሁሉ ይልቅ በፍልስጤም የሚኖሩት ይበዙ ነበር።
የአብርሃም የልጅ ልጅ ያዕቆብ ደግሞ እስራኤል ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ስለዚህም ከእርሱ የተገኙት ሕዝብ ሁሉ እስራኤላውያን ተባሉ። ያዕቆብ ወይም እስራኤል አሥራ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱም አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ተገኙ። ነገር ግን ይሁዳ የሚባለው አንዱ ልጅ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ የበዙ ዘሮች ወይም ከእርሱ የተገኙ ሰዎች ነበሩት፤ በፍልስጤም ከነበሩት ሰዎችም አብዛኞቹ ከይሁዳ ቤተ ሰብ ስለ ነበሩ፥ ሁሉም አይሁድ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ትርጓሜውም ከይሁዳ የተገኙ ወይም የተወለዱ ማለት ነው። ስለዚህ ኢየሱስ የተገኘበት ሕዝብ አንዳንድ ጊዜ እስራኤላውያን፥ ይበልጥ ግን አይሁድ ተብሎ ይጠራ ነበር። ሌላም ስም፥ «ዕብራውያን» የሚል ስም ነበራቸው፤ ነገር ግን እንደ ሁለቱ ስሞች፥ እንደ እስራኤላውያንና እንደ አይሁድ፥ በብዛት አይጠራበትም ነበር።
ኢየሱስ ከመምጣቱ አስቀድሞ ለብዙ ዓመታት አይሁድ በፍልስጤም አገር ገዦች ነበሩ፤ በጥንቱ ዘመን እንደ ዳዊትና እንደ ሰሎሞን፥ በኋላም እንደ ንጉሥ ኢዮርብዓምና እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ያሉ ከራሳቸው ወገን የሆኑ ነገሥታት ነበሩአቸው። ነገር ግን በኢየሱስ ዘመን አይሁድ በገዛ አገራቸው ገዦች መሆናቸው ቀርቶ ነበር። ፍልስጤም በዚያን ጊዜ በሜዲትራኒያን ባሕር ዙሪያ ያሉትን አገሮች ሁሉ ይገዛ የነበረው የሰፊው የሮም መንግሥት ትንሽ ክፍል ነበረች። አለቃውም በኢጣሊያ በሮም የሚኖር ንጉሠ ነገሥት ነበረ። ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ አውግስጦስ ነበረ። እርሱም በዚያን ጊዜ ሽማግሌ ነበረ፤ ኢየሱስም ከተወለደ ብዙም ሳይቆይ ሞተ። ከእርሱ በኋላ የነገሠው ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ ይባል ነበር፤ ኢየሱስ በፍልስጤም በኖረባቸው ዓመታት አብዛኛውን ጊዜ የገዛውም እርሱ ነበረ።
ነገር ግን ኢየሱስ በመጣ ጊዜ በሮም ንጉሠ ነገሥት ሥር የፍልስጤምን አገር የሚገዛ ሌላ ንጉሥ ነበረ። ስሙ ሄሮድስ ነበረ፤ እጅግ ክፉ ሰው ቢሆንም እጅግ ብልህና ብርቱ ሰው ስለ ነበረ ታላቁ ሄሮድስ ተባለ። የፍልስጤምን አገር ይገዛ ነበር፤ እርሱ ግን በተራው በሮም ያለውን የንጉሠ ነገሥቱን የአውግስጦስን ትእዛዝ ይፈጽም ነበር። ሄሮድስም ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ እጅግ ሽማግሌ ነበረ፤ ብዙም ሳይቆይ ሞተ።
ታላቁ ሄሮድስ በሞተ ጊዜ መንግሥቱ በአራት ክፍል ተከፈለ። ከእነዚህ ክፍሎች እያንዳንዱ የራሱ ንጉሥ ነበረው፤ ከእነዚህም ነገሥታት ሦስቱ የሄሮድስ ልጆች ነበሩ። ሄሮድስ አንቲጳስ በሰሜን ምዕራብ ገሊላን በደቡብ ምሥራቅም ፔሪያን ይገዛ ነበር፤ ሄሮድስ ፊልጶስ በሰሜን ምሥራቅ ባለው አገር ላይ ነበረ፤ ሄሮድስ አርኬላዎስ ደግሞ በደቡብ ያለውን ታላቁን ክፍል ይገዛ ነበር። ከእነዚህ ትንንሽ ነገሥታት አንዳቸውም ደጎች አልነበሩም። የአባታቸው ክፋት ነበረባቸው፤ የመግዛት ችሎታው ግን አልነበራቸውም። ከእነርሱ አንዱ አርኬላዎስ እጅግ ክፉ ስለ ነበረ ሕዝቡ ሁሉ በሮም ያለውን ንጉሠ ነገሥት አገዛዙን እንዲወስድበት ለመኑ። ንጉሠ ነገሥቱም ይህን አደረገ፤ በእርሱም ፋንታ አገሩን እንዲያስተዳድር ከሮም አንድ ሰው ላከ። ኢየሱስ ሲያስተምር በዚህ የአገሩ ክፍል ላይ ስለ ነበረው የሮም ገዥ ሰምተሃል። ስሙ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ነበረ፤ እንደምታስታውሰውም ኢየሱስን በመስቀል ላይ እንዲሞት አሳልፎ የሰጠው እርሱ ነበረ።
በዚያን ጊዜ የፍልስጤም አገር «አውራጃዎች» በሚባሉ አምስት ክፍሎች ተከፍሎ ነበር። ከእነዚህ አውራጃዎች ታላቁ በደቡብ ያለው ይሁዳ ነበረ፤ እርሱም በምሥራቅ በሙት ባሕርና በዮርዳኖስ ወንዝ፥ በምዕራብም በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል ነበረ። ከይሁዳ በስተ ሰሜን ሰማርያ የሚባል ትንሽ አውራጃ ነበረ፤ በዚያም አይሁድ ያልሆኑ ሳምራውያን የሚባሉ ሕዝብ ይኖሩ ነበር። አይሁድ ሳምራውያንን ይጠሉ ነበር፤ ሳምራውያንም በተራቸው አይሁድን ይጠሉ ነበር። ሰማርያ የተለየ ገዥ ሳይኖራት እንደ ይሁዳ ክፍል ትተዳደር ነበር። እነዚህ ሁለቱ አውራጃዎች በመጀመሪያ በአርኬላዎስ፥ በኋላም በሮም ገዥ ሥር የነበሩት ናቸው።
በፍልስጤም ሰሜን፥ ከዮርዳኖስ ወንዝና ከገሊላ ባሕር በስተ ምዕራብ፥ የገሊላ አውራጃ ነበረ፤ ይህም ኢየሱስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ማለት ይቻላል የኖረበት ተራራማ አገር ነው። የዚህ አውራጃ ገዥ ሄሮድስ አንቲጳስ ነበረ። እርሱም በገሊላ ባሕር አጠገብ በሠራትና በሮም ንጉሠ ነገሥት በጢባርዮስ ስም ጥብርያዶስ ብሎ በሰየማት ከተማ አብዛኛውን ጊዜ ይኖር ነበር።
ከዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ፥ በገሊላ ትይዩ፥ ሌላ አውራጃ ነበረ። በብሉይ ኪዳን ዘመን ይህ አገር ብዙ ደኖች ያሉበት አገር ስለ ነበረ «ጫካማ ምድር» ማለት የሆነውን ባሳን በሚል ስም ይጠራ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን ገዥው ከሄሮድስ ልጆች ሁሉ የሚሻለው፥ ያም ሆኖ እጅግ ደግ ያልነበረው ሄሮድስ ፊልጶስ ስለ ነበረ፥ ብዙውን ጊዜ «የፊልጶስ አውራጃ» ተብሎ ይጠራ ነበር።
ከፊልጶስ አውራጃ በስተ ደቡብ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝም በስተ ምሥራቅ፥ ፔሪያ የሚባል አውራጃ ነበረ፤ ይህ አካባቢ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ወይም ባሻገር ስለ ነበረ፥ ትርጓሜው «ማዶ» የሆነ ስም ተሰጠው። በኢየሱስ ሕይወት ዘመን ፔሪያ እንደ ገሊላ በሄሮድስ አንቲጳስ ይገዛ ነበር። ኢየሱስ ይህን አውራጃ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጎብኝቶአል፤ በዚህም ሰው ሁሉ የሰማውን የአባካኙን ልጅ ምሳሌ ተናገረ።
ኃያሉ የሮም መንግሥት በፍልስጤም ላሉት አይሁድ ቅንና ፍትሐዊ አስተዳደር ቢሰጣቸውም፥ የአይሁድ አገዛዝ አልነበረም፤ አይሁድም በባዕዳን ሥልጣን ሥር ደስ አላላቸውም። ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ እነርሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ ሆኑ፥ ከራሳቸው ወገን በሆኑ ነገሥታት ሥር ራሳቸውን የመግዛት መብት እንዳላቸውም ይሰማቸው ነበር። ደግሞም ከእስራኤል ከዳዊት ዘር የሆነ፥ ዓለምን የሚገዛ ንጉሥ እንደሚወጣ የነቢያትን ተስፋዎች በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ያነቡ ነበር።
አይሁድ ተስፋ ያደርጉትና ይጠብቁት የነበረውን ይህን ታላቅ ንጉሥ «መሲሕ» ብለው ይጠሩት ነበር፤ ይህም በአይሁድ ቋንቋ የግሪክ ቃል ከሆነው «ክርስቶስ» ከሚለው ቃል ጋር አንድ ትርጓሜ ያለው ቃል ነው፤ ትርጓሜውም «የተቀባው»፥ ማለትም «ንጉሡ» ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ታሪክ ነቢዩ ሳሙኤል ሳኦልን የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ እንዲሆን እንደ ቀባው፥ ማለትም በራሱ ላይ ዘይት እንዳፈሰሰ፥ ከዚያም በኋላ ብላቴናውን ዳዊትን በዚያው ምልክት ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን እንደ መረጠው ታስታውሳለህ። «ኢየሱስ ክርስቶስ» ስንል፥ ኢየሱስ ስሙ ነው፤ «ክርስቶስ» ደግሞ ማዕረጉ ነው፤ ትርጓሜውም «ንጉሡ ኢየሱስ» ማለታችን ነው።
አይሁድ መሲሕ ብለው የጠሩት ይህ ተስፋ የተሰጠበት ንጉሥ በየስፍራው የሰዎችን ልብ የሚገዛው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሆነ እናውቃለን፤ አይሁድ ግን ይህ እንደ ሄሮድስ ወይም እንደ ንጉሠ ነገሥቱ እንደ ጢባርዮስ ያለ፥ ነገር ግን ከእነርሱ የሚሻልና ጥበበኛ የሆነ፥ በዋናው ከተማቸው በኢየሩሳሌም በቤተ መንግሥት የሚኖርና አገሮችን ሁሉ ለፈቃዱ የሚያስገዛ ንጉሥ ማለት መሰላቸው። ይህ ተስፋ አይሁድን በሮም ሥልጣን ሥር እጅግ ዕረፍት የሌላቸውና ደስታ የራቃቸው አደረጋቸው። ምድርን ለማሸነፍ የሚመራቸውን የዚህን ኃያል የአይሁድ ንጉሥ መምጣት ሁልጊዜ ይጠባበቁ ነበር።
አይሁድ በአምልኮአቸው ከሌላው ዓለም ሁሉ የተለዩ ነበሩ። ሌላው ሕዝብ ሁሉ የእንጨትና የድንጋይ አማልክት ነበሩት፤ የሚሰግዱላቸውና መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸው ምስሎች ነበሩ። በዚያ ዓለም ባሉ ከተሞች ሁሉ በሰው እጅ ለተሠሩ ለእነዚህ ጣዖታት ቤተ መቅደሶችና መሠዊያዎች ነበሩ። በአይሁድ አገር ግን ምስሎች፥ የጣዖት ቤተ መቅደሶች፥ በሰው እጅ ለተሠሩ አማልክትም መሥዋዕቶች አልነበሩም። አይሁድ በፍልስጤምም ሆኑ በሌሎች አገሮች፥ የማይታየውን አንዱን አምላክ፥ እኛም የምንጸልይለትን አምላክ ያመልኩ ነበር። በዋናው ከተማቸው በኢየሩሳሌም እግዚአብሔር የሚመለክበት የተዋበ ቤተ መቅደስ ነበረ፤ በየአይሁድ ከተማና መንደርም ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ፥ የዳዊትን መዝሙሮች ለመዘመር፥ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት ለማቅረብና ስለ እግዚአብሔር ሕግጋት አብረው ለመነጋገር የሚሰበሰቡባቸው የጸሎት ቤቶች ነበሩ። እነዚህ የጸሎት ቤቶች «ምኩራቦች» ይባሉ ነበር፤ አይሁድ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምኩራቦች ይገኙ ነበር። አይሁድ የሌሎችን ሕዝቦች የጣዖት አምልኮ በታላቅ ንቀት ይመለከቱ ነበር፤ ከአባታቸው ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ ጌታ እግዚአብሔርን ብቻ በማምለካቸውም ይመኩ ነበር።