ምዕራፍ 38 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
የታመመችው ሴት ስለ መዳንዋና የሞተችው ልጅ ወደ ሕይወት ስለ መመለስዋ
በቅፍርናሆም ዳርቻ ብዙ ሕዝብ ቆሞ ወደ ባሕሩ በትኵረት ይመለከት ነበር። ባለፈው ምሽት ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በታንኳዎቻቸው ከዳርቻው ተነሥተው ወደ ባሕሩ ሲጓዙ አይተው ነበር፤ አሁን ደግሞ እስኪመለሱ ይጠብቁ ነበር። በውኃው አጠገብም አንድ ሰው ቆሞ ነበር፤ ፊቱም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንዳለ ያሳይ ነበር፤ ወደ ባሕሩም በየአቅጣጫው በጭንቀት ይመለከት ነበር።
የዚህ ሰው ስም ኢያኢሮስ ነበር። እርሱም ምኵራብ በሚሉት በከተማይቱ የጸሎት ቤት ላይ የተሾመ ዋና ሽማግሌ ነበር። በቤቱም የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ የሆነች ታናሽ ልጁ እጅግ ታማ ተኝታ ነበር፤ በማንኛውም ሰዓትም ልትሞት ትችል ነበር። ኢያኢሮስ ኢየሱስ ልጁ ሳትሞት በጊዜ ወደ ዳርቻው ቢደርስ ሕይወትዋን ሊያድን እንደሚችል ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ተስፋና ፍርሃት ተቀላቅለውበት ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ በዳርቻው ቆሞ ይጠብቅ ነበር፤ ነገር ግን ዘግይቶ እንዳይመጣ ይፈራ ነበር።
በመጨረሻም ትልቂቱ ታንኳ ከሌሎች ትናንሽ ታንኳዎች ጋር ስትታይና ስትቀርብ አየ። ኢየሱስም ገና ከታንኳይቱ ሳይወርድ ኢያኢሮስ በፊቱ በግንባሩ ተደፍቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦
«መምህር ሆይ፥ በተቻለህ ፍጥነት ወደ ቤቴ ና! ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለች፤ እባክህ፥ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት።»
ኢየሱስም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያጋፉት ተከተሉት፤ አንዳንዶቹ በችግሩ ላለው ለኢያኢሮስ ርኅራኄና ተስፋ ያሳዩ ነበር፤ አብዛኞቹ ግን ኢየሱስ ከድንቅ ሥራዎቹ አንዱን ሲያደርግ ለማየት ይፈልጉ ነበር። በሕዝቡም ዳር በበሽታ የመነመነችና እንደ ሞተ ሰው የገረጣች አንዲት ምስኪን ሴት ቆማ ነበር። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደምዋን ያፈሰሰ የሚፈስ ቍስል ነበረባት። ብዙ ባለ መድኃኒቶች ሊረዱአት ሞክረው ባይሳካላቸውም ኢየሱስ ቍስልዋን ሊፈውስ እንደሚችል ታምን ነበርና ወደ እርሱ ለመሄድ እጅግ ጓጓች። ገንዘብዋን ሁሉ አንዱን ከሌላው እየተከተለች ለባለ መድኃኒቶች ጨርሳ ነበር፤ ከእነርሱ ግን አንዱም አልጠቀማትም፤ እርስዋም ሁልጊዜ እየባሰባት ሄደች። ኢየሱስ በዚህ ታላቅ ሕዝብ መካከል ነበር፤ ይህች ሴትም እጅግ ደካማ ነበረች፤ ነገር ግን ብርቱ ጥረት አድርጋ ወደ ኢየሱስ መቅረብ ቻለች፤ ልታናግረው ሳይሆን በአጠገቡ በሚሄዱት ሰዎች መካከል እጅዋን ሰድዳ ልብሱን ለመንካት ነበር።
ድንገትም በልብዋ ታላቅ ተስፋ ተነሣ። በልብዋም «የመምህሩን ልብስ ብቻ ብዳስስ እንደምድን በእውነት አምናለሁ!» አለች።
በሚንቀጠቀጥ እጅዋም ዘርግታ የኢየሱስን መደረቢያ ዳሰሰች። ወዲያውም እንግዳ ኃይል ወደ ሰውነትዋ ሲገባ ተሰማት፤ ቍስልዋም እንደ ተፈወሰ አወቀች። ደኅና ሆነች፤ በረታችም!
በዚያን ቅጽበት ኢያኢሮስ ኢየሱስን ሊያቻኩለው ሲሞክር ሳለ ኢየሱስ ከመሄድ ቆመ። ቆሞም ዙሪያውን ተመለከተና «ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው?» አለ።
ደቀ መዛሙርቱ በአጠገቡ ነበሩ፤ ጴጥሮስም እንዲህ ብሎ መለሰ፦
«መምህር ሆይ፥ ሕዝቡ በዙሪያህ ሆኖ ያጋፋሃል፤ ሰዎችም ሁልጊዜ እየነኩህ ሳለ ‹ማን ዳሰሰኝ?› ትላለህን?»
ኢየሱስ ግን «አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና» አለ።
ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ቆሞ ዙሪያውን ሲመለከት ሴቲቱ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ወጣች፤ እንዳስቀየመችውም ፈርታ እየተንቀጠቀጠች በእግሩ ላይ ወደቀች። ምን ያህል መከራ እንደ ተቀበለች፥ ልብሱንም እንዴት እንደ ዳሰሰችና እንደ ተፈወሰች ነገረችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦
«ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ።»
ነገር ግን ኢየሱስ ለእነዚህ ጥቂት ጊዜያት በዘገየ ጊዜ ኢያኢሮስ እየጨመረ በሚሄድ ጭንቀት በአጠገቡ ቆሞ ነበር፤ ለእርሱና ለምትሞተው ልጁ እያንዳንዱ ደቂቃ ውድ ነበርና። በዚያን ጊዜም ከቤቱ አንድ ሰው በሕዝቡ መካከል ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦
«ልጅህ ሞታለች፤ መምህሩን ከዚህ በላይ እንዲመጣ መለመንህ ምን ይጠቅማል? አሁን እርሱም እንኳ ሊረዳት አይችልም።»
እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በናይን የመበለቲቱን ልጅ ከሞት እንዳስነሣ አልሰሙም ነበር፤ ያች መንደር ከቅፍርናሆም ቢያንስ ሃያ አምስት ማይል ትርቅ ነበርና።
ኢየሱስ ግን ያዘነውን አባት እንዲህ ብሎ አበረታታው፦ «አትፍራ፤ እመን ብቻ፥ እርስዋም ገና ትድናለች።»
ወደ ኢያኢሮስ ቤትም ሄዱ፤ ሕዝቡም ተከትለው ወደ ውስጥ ሊገቡ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ከለከላቸው። ከልጅቱ አባትና ከሦስቱ ደቀ መዛሙርቱ ከጴጥሮስ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ወደ ቤት እንዲገባ አልፈቀደም።
ቤቱም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረውና በዚያ ምድር ዛሬም እንደሚደረገው እያለቀሱና ዋይ ዋይ እያሉ፥ እምቢልታ እየነፉና ታላቅ ጩኸት እያሰሙ በነበሩ ሰዎች ተሞልቶ ነበር። በከተማው ያሉ ሁሉ ስለ ሞቱና ስለ ቤተ ሰቡ ኀዘን እንዲያውቁ፥ ሰው ሞቶ ወደ ተኛበት ቤት መጥተው እንዲጮኹና በታላቅ ድምፅ እንዲያለቅሱ ወንዶችና ሴቶች ይከፈላቸዋል።
ኢየሱስም በቤቱ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች «እንዲህ የምትንጫጩት ስለ ምን ነው? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም» አላቸው።
ኢየሱስ በዚህ ቃል ወዳጆቻችን ሲሞቱ በኀዘን መሞላት እንደማይገባን ማለቱ ነበር፤ ሞት እግዚአብሔር እስኪያነቃቸው ድረስ እንቅልፍ ብቻ ነውና። ይህን ግን አላስተዋሉም፤ ልጅቱም እንደ ሞተች ያውቁ ነበርና መጽናናትን እንቢ አሉ።
ኢየሱስ እነዚህን የተከፈላቸውን አልቃሾች ሁሉ ከቤቱ እንዲወጡ አዘዛቸው። አባትዋንና እናትዋን ከሦስቱ የተመረጡ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ይዞ የሞተችው ልጅ በአልጋ ላይ ወደ ተኛችበት ክፍል ገባ። በሬሳዋም አጠገብ ቆሞ ትንሽ እጅዋን በእጁ ይዞ እንዲህ አለ፦
«አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ፥ እልሻለሁ!»
ልጅቱም ወዲያው ቆመች፤ ዙሪያዋን ተመለከተች፤ መመላለስም ጀመረች። ያ አባትና ያች እናት ከእንግዲህ የሞተች ሳትሆን ሕያውና ጤነኛ የሆነችውን ትንሽ ልጃቸውን በእቅፋቸው ሲያቅፉ ምንኛ ደስ አላቸው! ሁሉም በመገረም ተሞሉ። ስለዚህ ታላቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሊነግሩ ፈልገው ነበር፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦
«ለልጅቱ የምትበላውን ስጡአት፤ ነገር ግን ወደ ሕይወት ስለ መመለስዋ አትናገሩ። ይህን ለማንም አትንገሩ።»