ምዕራፍ 37 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
ባሕሩን ተሻግሮ መጓዝ
በምሳሌ ካስተማረበት ቀን በኋላ፥ በመሸ ጊዜ፥ ሕዝቡ አሁንም ኢየሱስን እያጋፋ ለማረፍ ጊዜ ስላልሰጠው፥ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦
«ባሕሩን ተሻግረን ወደ ማዶ እንሂድ።» እነርሱም ታንኳይቱን አዘጋጅተው ኢየሱስን አሳፈሩት። ከሕዝቡም አንዳንዶቹ ከኢየሱስ ጋር ለመሆን እጅግ ስለ ጓጉ በሌሎች ታንኳዎች ገብተው ከእርሱ ጋር ተጓዙ። ኢየሱስ ቀኑን ሙሉ ሲያስተምር ውሎ እጅግ ደክሞ ነበርና በታንኳይቱ በስተኋላ ትራስ ተንተርሶ ተኛ። በቀዘፋው ወጥ እንቅስቃሴና በማዕበሉ ለስላሳ ድምፅ ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ወሰደው፤ ታንኳይቱም በባሕሩ ላይ ወደ ፊት ትሄድ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሌሊት ሆነ፤ ደቀ መዛሙርቱም በጨለማው ውስጥ መቅዘፋቸውን ቀጠሉ።
በገሊላ ባሕር ላይ ብዙ ጊዜ ማዕበል በድንገት ይነሣል። ውኃው ለጥቂት ጊዜ ፍጹም ፀጥ ብሎ ይቆይና በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በነፋስ ተገርፎ ይናወጣል። ኢየሱስ ተኝቶ ሳለም እንዲሁ ሆነ። ታላቅ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ከፍ ብሎ እየተንከባለለ ወደ ታንኳይቱ ይገባ ነበር፤ ኢየሱስ ግን በሰላም ተኝቶ ነበር።
ከዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ቢያንስ አራቱ፥ ምናልባትም ከዚያ የሚበልጡት፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። እንዲህ ያለው ድንገተኛ ማዕበል ምን ያህል አደገኛ እንደ ሆነ ያውቁ ነበር፤ ታንኳይቱም በውኃ ስትሞላና ልትሰምጥ ስትጀምር ባዩ ጊዜ ፈሩ። ወደ ኢየሱስም ቀርበው አነቁትና «መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ጠፋን! እርዳን፥ አለዚያ እንሰጥማለን!» ብለው ጮኹ።
የሸራው ሲጥጥታ፥ የነፋሱ ጩኸትና የማዕበሉ ግርፋት ያለው ማዕበል ኢየሱስን አላነቃውም ነበር፤ የፈሩት ደቀ መዛሙርቱ ጩኸት ግን ከእንቅልፉ አነቃው። ዙሪያውን ተመለከተ፤ የሚገፋውን ማዕበል አየና ይህን ቃል ብቻ ተናገረ፦
«ዝም በል፥ ፀጥ በል!»
ወዲያውም ነፋሱ ተወ፤ ማዕበሉም ለሰለሰ፤ በባሕሩም ላይ ፍጹም ፀጥታ ሆነ። ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦
«እንዲህ የምትፈሩ ስለ ምን ነው? በእኔ ያላችሁ እምነት እንዲህ ጥቂት ነውን?»
መምህራቸው ነቅቶም ሆነ ተኝቶ ከእነርሱ ጋር እስካለ ድረስ ደኅና እንደ ሆኑ ማወቅ በተገባቸው ነበር። በዚህ አዲስ የኢየሱስ የኃይል ማስረጃ ተደነቁና እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦
«ነፋሱንና ማዕበሉን የሚያዝዝ፥ እነርሱም ቃሉን የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው!»
ከቅፍርናሆም ወደ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ይጓዙ ነበር፤ ሰባት ማይል ያህል ከቀዘፉ በኋላ ጌራሳ የምትባል መንደር ወዳለችበት ወደ ባሕሩ ምሥራቃዊ ዳርቻ ደረሱ። ይህ አካባቢ በአቅራቢያው ካለችው ጋዳራ ከምትባል ታላቅ ከተማ የተነሣ «የጌርጌሴኖን አገር» ይባል ነበር። ይህም ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ ላለው አገር ሁሉ የተሰጠ ስም የሆነው የዲካፖሊስ ክፍል ነበር። ዲካፖሊስ የሚለው ቃል «ዐሥሩ ከተሞች» ማለት ነው፤ በዚያም ምድር ዐሥር ታላላቅ የሮም ከተሞች ስለ ነበሩ አገሩ ሁሉ «የዐሥሩ ከተሞች አገር» ተባለ።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ታንኳዎቻቸውን በጌራሳ ዳርቻ ያስጠጉት እጅግ በማለዳ ሳይሆን አይቀርም። ገና ወደ ዳርቻው ሲደርሱ አንድ ሰው ሊገናኛቸው ከኮረብታው እየሮጠ ወረደ፤ ከአድራጎቱም አስከፊነት ርኵሳን መናፍስት ከሚገዙአቸው ከእነዚያ ምስኪኖች አንዱ መሆኑን አዩ። ይህ ሰው ልብስ አይለብስም ነበር፤ በቤትም አይኖርም፤ ነገር ግን ለመቃብርነት በሚያገለግሉት በኮረብታው ዋሻዎች ውስጥ ይኖር ነበር። በገመድና በሰንሰለት ሊያስሩት ሞክረው ነበር፤ ክፉው ኃይል በያዘው ጊዜ ግን እስራቱን ሁሉ ይበጥስ፥ ሰንሰለቱንም እንኳ ይቈርጥ ነበር። ሁልጊዜም በመቃብሮች መካከል ይኖር ነበር፤ እየጮኸ፥ እያቃሰተና ራሱን በሹል ድንጋይ እየቈሰለ ይኖር ነበር።
ይህ ዕብድ ሰው ወደ ኢየሱስ ሮጦ በእግሩ ላይ ወደቀ። ኢየሱስም ያለበትን ሁኔታ እንዳየ በሰውየው ውስጥ ያለውን ርኵስ መንፈስ እንዲህ አለው፦
«አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ!»
መንፈሱም ለኢየሱስ እየጮኸ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? እንዳታሠቃየን በእግዚአብሔር አምልሃለሁ!»
ኢየሱስም የዚህ ሰው ሁኔታ ርኵሳን መናፍስት ከሚገዙአቸው ከብዙዎቹ እንኳ እጅግ የከፋ መሆኑን አየ። መንፈሱንም «ስምህ ማን ነው?» አለው።
ርኵሱ መንፈስም «ስሜ ሌጌዎን ነው» ብሎ መለሰ፤ ይህም በሰውየው ውስጥ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ርኵሳን መናፍስት፥ ሙሉ ሠራዊት፥ አሉ ማለቱ ነበር፤ «ሌጌዎን» የሚለው ቃል ሠራዊት ማለት ነውና።
አጋንንቱ፥ ማለትም ርኵሳን መናፍስቱ፥ ወደ ሩቅ እንዳይሰዳቸው ኢየሱስን ለመኑት። በኮረብታውም ጫፍ ላይ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር። አይሁድ እሪያ እንዲያረቡም ሆነ ሥጋውን እንዲበሉ አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ስለዚህ ይህ የእሪያ መንጋ አይሁድ አሕዛብ ብለው የሚጠሩአቸው የባዕድ ሰዎች ሳይሆን አይቀርም።
ርኵሳን መናፍስቱም ከሰውየው በወጡ ጊዜ ወደ እነዚህ እሪያዎች ይገቡ ዘንድ ኢየሱስን ጠየቁት፤ ኢየሱስም ፈቀደላቸው። አጋንንቱ ወይም ርኵሳን መናፍስቱም ሰውየውን ራቁቱን ነገር ግን ድኖ በምድር ላይ ተጋድሞ ትተው ወጡ። ወደ እሪያው መንጋም ገቡ፤ እሪያዎቹም ወዲያው ተዋከቡ፤ ሊገቱም አልተቻለም። በአንድነት ተሰብስበው በኮረብታው ገደል እየተጣደፉ ወደ ውኃው ገቡ። በዚያም ሁሉም ሰጠሙ፤ ቍጥራቸውም ሁለት ሺህ ያህል ነበር። እሪያዎቹን የሚጠብቁትም ሰዎች በአቅራቢያው ወዳለችው ከተማ ሮጠው የሆነውን ሁሉ ለሕዝቡ ነገሩ፤ አጋንንቱ በዚህ እንግዳ ትእዛዝ ሰውየውን ትተው እንደ ወጡ፥ ወደ እሪያዎቹ መንጋ እንደ ገቡና በውኃ ውስጥ እንዳሰጠሙአቸው ነገሩአቸው። የከተማይቱም ሰዎች የሆነውን በዓይናቸው ለማየት ወጡ። ብርቱዎቹ ርኵሳን መናፍስት አድረውበት የነበረውን ሰው አሁን ልብሱን ለብሶ፥ ልቡም ተመልሶለት፥ ረጋ ብሎና ሰላም አግኝቶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አዩት።
እነዚህ የጌርጌሴኖን ሰዎች ስለ ኢየሱስና ስላደረጋቸው ስለ ብዙ መልካም ሥራዎቹ ምንም እንደማያውቁ ግልጽ ነው። ኃይሉን እጅግ ፈሩ፤ ኢየሱስ በሚያስደንቅ ሁኔታ የረዳውንም ሰው ለማየት እንኳ ሳይሹ ያጡአቸውን እሪያዎች ብቻ አሰቡ። ኢየሱስም ከአገራቸው እንዲሄድና ወደ ከተማቸው እንዳይመጣ ለመኑት። ኢየሱስ ድውዮቻቸውን በመፈወስ፥ ለዕውሮች ዓይን፥ ለደንቆሮችም ጆሮ በመስጠት፥ ከትምህርቱ የምሥራች በተጨማሪ ምን ያህል በረከት ሊያመጣላቸው ይችል እንደ ነበር አስቡ! እነርሱ ግን እነዚህን መልካም ስጦታዎች ባለማወቃቸው ኢየሱስ እንዲተዋቸው ለመኑት።
ኢየሱስም እንደ ቃላቸው አደረገ። በኀዘን ተመልሶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወረደና ወደ ታንኳይቱ ገባ። ከርኵሳን መናፍስቱ ነፃ የወጣው ሰውም ከኢየሱስ ጋር ይሄድ ዘንድ አጥብቆ ለመነው። ምናልባት በእርሱ ውስጥ የነበሩት አጋንንት እሪያዎቻቸውን ስለ ገደሉ የከተማይቱ ሰዎች እንዳይቈጡት ፈርቶ ይሆናል፤ ወይም ብርቱ ረዳቱ በአጠገቡ ሳይኖር ብቻውን ቢቀር ርኵሳን መናፍስቱ ተመልሰው ይመጡበታል ብሎ አስቦ ይሆናል። ከጌታው ጋር ቢሆን ደኅና እንደሚሆን ያውቅ ነበርና ኢየሱስ ወደሚሄድበት ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሄድ ዘንድ ደጋግሞ ለመነ።
ኢየሱስ ግን ልመናውን አልፈቀደለትም። ሰውየውንም እንዲህ አለው፦
«ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው።»
ሰውየውም በዲካፖሊስ አገር ሁሉ እየዞረ ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት ላገኘው ሁሉ ተናገረ። ይህንም በሰሙ ጊዜ ሁሉም ተደነቁ፤ ብዙዎቹም ኢየሱስን ከማባረር ይልቅ ተቀብለውት ቢሆን ኖሮ ብለው እንደ ተመኙ አያጠራጥርም።