የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በባሕሩ ዳር የተነገሩ ሌሎች ታሪኮች

ምዕራፍ 36 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

በባሕሩ ዳር የተነገሩ ሌሎች ታሪኮች

ኢየሱስ በታንኳው ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡም በባሕሩ ዳር ቆመው ሳሉ ለሕዝቡ የነገራቸው ሌላ የምሳሌ ታሪክ ይህ ነው። ይህም የ«ስንዴውና የእንክርዳዱ» ምሳሌ ነው።

«አንድ ሰው በእርሻው መልካም ስንዴ ዘራ፤ ሰዎች ተኝተው ሳሉ ግን ጠላት መጥቶ በመሬቱ ሁሉ ላይ የእንክርዳድ ዘር በተነ። ከዚያም ጠላቱ የዘራው ዘር እንዲበቅል ትቶት ሄደ። የእህሉ ቡቃያ የስንዴ ዛላ ማውጣት በጀመረ ጊዜ ሰዎቹ በእርሻው ውስጥ በየስፍራው እንክርዳዱ በስንዴው መካከል እንዳለ አዩ፤ እንክርዳድ ሁልጊዜ ከመልካም ዘር ይልቅ ፈጥኖ ያድጋልና።»

«የገበሬውም ባሮች ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦»

«‹ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? ታዲያ እንክርዳድ እንዴት ሞላበት?›»

«እርሱም ‹ከጠላቶቼ አንዱ ይህን አደረገ› አላቸው።»

«ባሮቹም ‹እንግዲህ ሄደን ከስንዴው ጋር የበቀለውን እንክርዳድ እንንቀለውን?› አሉ።»

«ገበሬውም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ‹አይሆንም፤ እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን ከእርሱ ጋር ትነቅሉታላችሁ። እስከ መከር ጊዜ ሁለቱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን «ሰብሉን ሁሉ ካጨዳችሁ በኋላ እንክርዳዱን ለዩ፥ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ» እላለሁ።›»

ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ «የሚያድገው እህል» ሌላ ምሳሌ ሰጣቸው። እንዲህም አለ፦ «የእግዚአብሔር መንግሥት ሰው በምድር ላይ ዘርን እንደሚጥል ናት። ዘሪው በየሌሊቱ ተኝቶ ያድራል፤ ዘሩ ግን እርሱ እንዴት እንደሆነ ሳያውቅ ይበቅላል። ምድሪቱ በራስዋ ታፈራለች፤ በመጀመሪያ ቡቃያ፥ ኋላም ዛላ፥ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል። የእህሉ ዛላ ሲበስል ግን መከሩ ደርሶአልና ማጭዱን አስገብቶ ያጭዳል።»

የሚቀጥለው ምሳሌው «የሰናፍጭ ቅንጣት» ነበር። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች። እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፤ ነገር ግን አድጋ ዛፍ እስኪመስል ድረስ ታላቅ ቍጥቋጦ ትሆናለች፤ ትላልቅ ቅርንጫፎችንም ታወጣለች፤ ወፎችም በእነርሱ ላይ ይሰፍራሉ፥ በጥላቸውም ሥር ያርፋሉ።»

ኢየሱስ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ሰጠ፤ እርሱም «እርሾው» ነበር። እንዲህም አለ፦ «የእግዚአብሔር መንግሥት አንዲት ሴት እንጀራ ስትጋግር የምትጠቀምበትን እርሾ ትመስላለች። በብዙ ሊጥ ውስጥ በጣም ጥቂት እርሾ ትለውሳለች፤ እንዲቦካም ብላ ትተወዋለች። ብዙም ሳይቆይ ሊጡ ሁሉ በእርሾው ተለውጦ መልካም እንጀራ ይሆናል። እውነትም ወደ ልባቸው ለሚቀበሉት ሰዎች እንዲሁ ነው።»

ኢየሱስ እነዚህን አምስት ምሳሌዎች፥ «ዘሪውን»፥ «ስንዴውንና እንክርዳዱን»፥ «የሚያድገውን እህል»፥ «የሰናፍጭ ቅንጣትን»ና «እርሾውን» ከነገረ በኋላ ሕዝቡን አሰናብቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ አንድ ቤት ገባ። ከሕዝቡ ተለይተው ብቻቸውን በሆኑ ጊዜም «የ‹ስንዴውና የእንክርዳዱ› ምሳሌ ትርጕም ምን እንደ ሆነ ንገረን» አሉት።

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ «መልካሙን ዘር የሚዘራው እግዚአብሔር ወደ ምድር የላከው የሰው ልጅ ነው። እርሻውም ዓለም ነው። መልካሙ ስንዴ ቃሉን የሚሰሙና የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ናቸው። እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው። የዘራቸውም ጠላት ዲያብሎስ፥ ሰይጣን ነው። መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹም የእግዚአብሔር መላእክት ናቸው። እንክርዳዱ ከመልካሙ እህል መካከል ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ከመንግሥቱም ክፉ የሚያደርጉትንና ጕዳት የሚያመጡትን ሁሉ ይለቅማሉ፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ዋይታ ጥርስ ማፋጨትም ይሆናል። በዚያ ቀን ግን የእግዚአብሔር ልጆች፥ እውነተኛው ስንዴ፥ በሰማዩ አባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ።»

ከዚያም ኢየሱስ ለሕዝቡ ሳይሆን ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት ተጨማሪ ምሳሌዎችን ሰጠ። የመጀመሪያው «የተሰወረው መዝገብ» ነበር። እንዲህም አለ፦ «መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ ሲሠራ ያገኘውን የገንዘብ ክምር ትመስላለች። እርሱም መልሶ ሰወረው፤ ስለ ነገሩም ለማንም ምንም አልተናገረም፤ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠ፤ መዝገቡም የራሱ ይሆን ዘንድ ያን እርሻ በደስታ ገዛ።»

የሚቀጥለው ምሳሌ የ«ዕንቍው» ነበር። «ለሌሎች መልሶ ለመሸጥ ዕንቍዎችን የሚገዛ፥ እነርሱንም ለማግኘት ወደ ብዙ ስፍራ የሚሄድ አንድ ሰው ነበረ። በአንድ ስፍራም ከዚያ በፊት ካያቸው ሁሉ እጅግ የሚበልጥ፥ ዋጋዋ የበዛ ዕንቍ አገኘ። ሄዶም ያለውን ሁሉ ሸጠ፤ በዚያም ገንዘብ ያችን ዕንቍ ገዛ።»

ከእነዚህ ምሳሌዎች የመጨረሻው «መረቡ» ነበር። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ «ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ትልቁንም ትንሹንም፥ መልካሙንም ክፉውንም፥ ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች ታላቅ መረብን ትመስላለች። በሞላችም ጊዜ ወደ ዳር ጐተቱአት። በዚያም ተቀምጠው ዓሣዎቹን ከመረቡ አንድ በአንድ አወጡ። መረመሩአቸውም፤ ለመብል የሚሆኑትን መልካሞቹን ዓሣዎች በቅርጫት ውስጥ አኖሩ፤ የማይጠቅሙትን ግን ጣሉአቸው። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። መላእክት መጥተው ክፉዎቹን ሰዎች ከመልካሞቹ መካከል ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።»

ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ለደቀ መዛሙርቱ ነግሮ ከጨረሰ በኋላ «ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?» አላቸው።

እነርሱም «አዎን፥ አስተውለናል» አሉት።

እርሱም «በእግዚአብሔር መንግሥት ደቀ መዝሙር የሆነ መምህር ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ሰውን ይመስላል» አላቸው።


ቀዳሚ ቀጣይ