የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በባሕሩ ዳር ታሪክ ነጋሪው

ምዕራፍ 35 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

በባሕሩ ዳር ታሪክ ነጋሪው

ኢየሱስ በደቡባዊው ገሊላ በኩል ካደረገው ጕዞ ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡን በአዲስ መንገድ፥ ታሪክ በመንገር፥ ማስተማር ጀመረ። ታሪክ ማዳመጥ የማይወድ የለም፤ ግልጹ እውነት ሳይሳካ ሲቀር ታሪክ አንዳንድ ጊዜ እስከ ልብ ዘልቆ ይገባል። ኢየሱስ በኖረበት በምሥራቅ አገር ታሪክ ነጋሪዎች ሁልጊዜ እጅግ ብዙ ነበሩ። ዛሬም እንኳ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየዞሩ ታሪክ የሚናገሩ ሰዎች በየቦታው ይገኛሉ፤ ሕዝቡም በዙሪያቸው ተሰብስቦ ከጠዋት እስከ ማታ ታሪካቸውን ያዳምጣል።

ነገር ግን ኢየሱስ የነገራቸው ታሪኮች ከምሥራቅ አገር ታሪክ ነጋሪዎች ታሪኮች እጅግ የተለዩ ነበሩ። ታሪኮቹ የሚነገሩት አንድ ታላቅ እውነት ለማስተማር ነበር፤ ስለዚህም «ምሳሌዎች» ተባሉ። ምሳሌ ማለት ከሕይወት ጋር የሚስማማ ታሪክ ነው፤ ይኸውም ተረት ሳይሆን እውነት ሊሆን የሚችል ታሪክ ነው፤ በውስጡም የእውነት ትምህርት የያዘ ነው።

አንድ ቀን ኢየሱስ ከቅፍርናሆም ከተማ ወጥቶ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ቆመ። የጻፎችና የፈሪሳውያን ተቃውሞ ሁሉ ተራውን ሕዝብ ከኢየሱስ ሊያርቀው አልቻለምና ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰበሰበ። በኢየሱስ ዙሪያ የተጋፋው ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለ ነበረ፥ እንደ ቀድሞው ወደ ታንኳ ገባና ደቀ መዛሙርቱን ከዳር ጥቂት ገፋ እንዲያደርጉት ነገራቸው። ከዚያም ቍልቍለቱን የባሕር ዳርቻ የሞላውን ታላቅ ሕዝብ ፊት ለፊት እያየ በታንኳው ውስጥ ተቀመጠ። ሕዝቡንም እንዲህ አላቸው፦

«ስሙ! እነሆ፥ ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ። ዘሩንም ሲበትን አንዳንዱ መሬቱ ተረግጦ በጠነከረበት መንገድ ላይ ወደቀ። ወፎችም ወርደው ቅንጣቶቹን ሁሉ እስኪለቅሙ ድረስ ዘሩ በመንገዱ ላይ ቀረ፤ ስለዚህም አንዱም አልበቀለም።»

«አንዳንዱም ዘር ከድንጋይ በላይ ስስ አፈር ብቻ ባለበት ስፍራ ወደቀ። በዚያም አፈሩ ስስ ስለ ነበረ ቅንጣቶቹ ቶሎ በቀሉ። ሙቀቱ በመጣ ጊዜ ግን ፀሐይ ለጋዎቹን ተክሎች አቃጠለቻቸው፤ እርጥበትም በጥልቅ መሬት ውስጥ ሥርም ስላልነበራቸው ሁሉም ጠወለጉ።»

«ከዘሩም ሌላው በኵርንችትና በቍጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እህሉ የሚያድግበትም ስፍራ አልነበረም። በሕይወት ቆየ፤ ነገር ግን በዙሪያው ባሉት የእሾህ ቍጥቋጦዎች ተጨናንቆ ታንቆ ስለ ነበረ ዛላ አላወጣም።»

«ከዘሩ ግን ሌላው ለስላሳ፥ ለምና መልካም በሆነ መሬት ላይ ወደቀ። በዚያም አድጎ ብዙ ፍሬ አፈራ። አንዳንዱ ቅንጣት ከተዘራው ሠላሳ እጥፍ፥ አንዳንዱ ስድሳ እጥፍ፥ አንዳንዱም መቶ እጥፍ ሰጠ።»

ኢየሱስ የምሳሌውን ትምህርት ለሕዝቡ አልነገራቸውም። «የሚሰማ ጆሮ ያለው የተናገርሁትን ይስማ» ብቻ አለ። ይህንም ሲል ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ማሰብና ትርጕሙን ራሳቸው መርምረው ማግኘት ይገባቸዋል ማለቱ ነበር።

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻውን በሆነ ጊዜ እንዲህ አሉት፦

«ለሕዝቡ ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? ዘር ስለሚዘራው ሰው በዚህ ታሪክ ምን ልታስተምር ወደድህ?»

ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦

«እኔን ለተከተላችሁ ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጥልቅ ነገሮች ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ልትመረምሩአቸው ትሻላችሁና። ለብዙዎች ግን እነዚህ እውነቶች በምሳሌ ይነገራሉ፤ ታሪኩን ይሰማሉና፥ ትርጕሙን ግን ለማግኘት አይሞክሩም። ዓይን አላቸው ግን አያዩም፤ ጆሮም አላቸው ግን አይሰሙም። በልባቸው ሊያስተውሉና ኃጢአታቸው ይሰረይላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ሊመለሱ አይወዱምና። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እንግዲህ አሁን የዘሪውን ምሳሌ ትርጕም ስሙ።»

«ዘሪው የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ነው፤ ዘሩም እርሱ የሚናገረው ቃል ነው።»

«በመንገድ ዳር፥ በተረገጠው መንገድ ላይ የወደቀው ዘር፥ የሚሰሙትን ነገር ግን እውነትን ወደ ልባቸው የማያስገቡትን ያመለክታል። ያን ጊዜ ክፉው መጥቶ እንደ ወፎቹ እውነቱን ይነጥቃል፤ ስለዚህም ይረሱታል።»

«በጭንጫማ መሬት ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን ሰምተው በደስታ ወደ ልባቸው የሚቀበሉት የሚመስሉ ናቸው፤ ነገር ግን በራሳቸው ሥር የላቸውም፤ ተስፋ መቍረጥ ወይም መከራ ባገኛቸው ጊዜ ወይም የእውነት ጠላቶች ባጋጠሙአቸው ጊዜ ወዲያው ፊታቸውን ይመልሳሉ፤ በጎነታቸውም አይጸናም።»

«በእሾህና በኵርንችት መካከል የተዘራው ቃሉን የሚያዳምጡ ናቸው፤ ነገር ግን የኑሮ ጭንቀት፥ የገንዘብ ምኞትና የዓለም ተድላ በልባቸው ያለውን ቃል ያጨናንቁታል፤ ወንጌሉም የሚጠቅማቸው ጥቂት ብቻ ነው።»

«በመልካም መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ወንጌሉን ሰምተው የሚያስተውሉት ናቸው፤ ቃሉን በቅንና በመልካም ልብ ተቀብለው የሚጠብቁትና በሕይወታቸው ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።»


ቀዳሚ ቀጣይ