የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስና ጠላቶቹ

ምዕራፍ 34 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስና ጠላቶቹ

ኢየሱስ በደቡባዊው ገሊላ በኩል ካደረገው ጕዞ በኋላ፥ ይህም በምድሪቱ ካደረጋቸው የስብከት ጕዞዎች ሁለተኛው ነበር፥ እንደ ገና ወደ ቅፍርናሆም መጣ። ያዳመጡትና ቃሉን አብዝተው ሊሰሙ የናፈቁ ብዙ ሕዝብ ከእርሱ ጋር መጡ። ኢየሱስን ያገኘ ሁሉ በፍቅር ወደ እርሱ ይሳብ ከእርሱም ጋር ሊሆን ይመኝ ነበርና። የሰሙት ሁሉ ማለት ይቻላል ይወዱት ነበር፤ ሁሉም ግን አይደሉም። በሙሴ ሕግ ሕዝቡን የሚያስተምሩ ጻፎችም፥ እውነተኛ ያልሆነ የማስመሰል ሃይማኖት የያዙ ፈሪሳውያንም ኢየሱስን እየባሰ ይጠሉት ነበር፤ በሕዝቡም ፊት ክፉ ይናገሩበት ነበር። ክፉ መንፈስ አለበት፥ ድንቅ ሥራ የሚሠራበትም ኃይል ከክፉው ከሰይጣን የመጣ ነው ይሉ ነበር።

አንድ ቀን ክፉ መንፈስ ያደረበት አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀረበ፤ መንፈሱም ማየቱንም መስማቱንም ወስዶበት ነበርና ማየትም መስማትም መናገርም አይችልም ነበር። ኢየሱስም በሰውዬው ውስጥ ያለውን ክፉ መንፈስ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦

«አንተ ክፉ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ፤ ደግሞም ከቶ ወደ እርሱ አትግባ!»

ክፉ መንፈሱም ከሰውዬው ሥጋ ወጣ፤ እርሱም ለጥቂት ጊዜ እንደ ሞተ ሰው በመሬት ላይ ተጋደመ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ፈጽሞ ድኖ፥ ማየትና መስማት መናገርም ችሎ ተነሣ። ይህን ፈውስ ያዩ ሁሉ በመደነቅ ተሞሉ፤ ብዙዎችም «ነቢያት ይመጣል ንጉሣችንም ይሆናል ብለው ተስፋ የሰጡት የዳዊት ልጅ ይህ አይደለምን?» አሉ።

ፈሪሳውያንና ጻፎች ግን ይህን ድንቅ በሰሙ ጊዜ «ይህ ሰው ክፉ መናፍስትን የሚያወጣው የክፉ መናፍስት ሁሉ አለቃ በውስጡ ስላለና ይህን ኃይል ስለሚሰጠው ነው» አሉ።

ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ፦

«እርስ በርሳቸው በሚዋጉ በሁለት ወገን የተከፈለች መንግሥት ሁሉ ፈጥና ትፈርሳለች፤ ሰዎቹ የሚጣሉበትም ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጥኖ ይጠፋል። ክፉው ሰይጣን ክፉ መናፍስትን የሚያወጣ ከሆነ፥ የሰይጣን መንግሥት እርስ በርስዋ ተለያይታለችና ፈጥና ትወድቃለች። እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይል ክፉ መናፍስትን ከሰዎች የማወጣ ከሆንሁ፥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ እንዳለ እርግጠኞች ሁኑ።»

ነገር ግን ኢየሱስ ክፉ መናፍስት አድሮበታል የሚለው ይህ ወሬ በሕዝቡ መካከል ተሰራጨ፤ አንዳንዶችም አመኑት። ወሬውም በዚያን ጊዜ ገና በሙሉ ልብ ያላመኑበት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሱስ ወንድሞች ደረሰ፤ ወደ እናቱ ወደ ማርያምም ደርሶ በፍርሃት ሞላት። ልጅዋ ያለ ዕረፍት እየሠራና እንዲህ ያለ ከባድ የጭንቀት ሸክም እየተሸከመ አእምሮውን ስቶ ይሆናል ብላ ፈራች። አንዳንዶችም «አበደ!» እያሉ፥ የኢየሱስ ቤተ ሰቦች ወደ ቤት ወስደው ሕዝቡን እንዳያውክ ሊከለክሉት ይገባል አሉ።

ማርያምና ልጆችዋ ኢየሱስ ለሕዝቡ እየተናገረና ድውዮችን እየፈወሰ ወደ ነበረበት ቤት መጡ። በደጁ ዙሪያ የነበረው ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለ ነበረ ወደ ቤቱ መግባት አልቻሉም፤ ስለዚህ የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ በውጭ በመንገድ ላይ እንዳሉና ሊያነጋግሩት እንደሚፈልጉ ወደ ውስጥ መልእክት ላኩ። ለኢየሱስም እንዲህ ብለው ነገሩት፦

«እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል።»

እርሱ ግን ለነገረው መልሶ «እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?» አለው።

ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዞሮ እጁን ዘርግቶ እንዲህ አለ፦

«እነሆ እናቴና ወንድሞቼ! በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነው!»

ኢየሱስ ይህን ሲል እናቱ ለእርሱ ውድ ብትሆንም ትምህርቱን ለመከተል የተዘጋጁት ከዚያ ይበልጥ ውዶች ናቸው ማለቱ ነበር።

ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ለኢየሱስ እንዲህ አሉት፦

«መምህር ሆይ፥ ከእግዚአብሔር እንደ መጣህ የሚያሳይ ምልክት አሳየን።»

በፊታቸው ተአምር፥ አንድ ድንቅ ነገር፥ እንዲሠራ ፈለጉ። ኢየሱስ ግን ከታላላቅ ሥራዎቹ አንዱንም ለመታየት ብቻ ብሎ ከቶ አያደርግም ነበር። ድውዮችን የፈወሰውና ክፉ መናፍስትን ያወጣው በመከራ ላሉ ሰዎች ከማዘን የተነሣ ነበር እንጂ ኃይሉን ለማሳየት አልነበረም። ለእነዚህ ሰዎችም እንዲህ አላቸው፦

«ሰዎች ምልክት የሚሹበት ዘመን ክፉና ታማኝነት የጐደለው ዘመን ነው። አሁን ምልክት አልሰጣችሁም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ምልክት ታያላችሁ፤ ምንም እንኳ ባታምኑበት። እርሱም የነቢዩ የዮናስ ምልክት ይሆናል። ዮናስ በታላቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀን እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እኔ የሰው ልጅ ሦስት ቀን ከመሬት በታች እሆናለሁ፤ እንደ ዮናስም ሕያው ሆኜ እወጣለሁ።»

«ዮናስ የሰበከላቸው የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔር በዓለም ላይ በሚፈርድበት ቀን ይነሣሉ፤ ከዚህም ዘመን ሰዎች እንደሚሻሉ ያሳያሉ፤ ዮናስ በሰበከላቸው ጊዜ ከኃጢአታቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን ፈልገዋልና። እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፤ ነገር ግን አይሰሙትም!»

«ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ዘመን ሰዎች ጋር ትነሣለች፤ ታማኞች እንዳልሆኑም ታረጋግጥባቸዋለች። የሰሎሞንን የጥበብ ቃል ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፤ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ፤ እናንተ ግን አትሰሙትም።»


ቀዳሚ ቀጣይ