ምዕራፍ 33 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ
ኃጢአተኛዪቱ ሴት ይቅር ተባለች
ኢየሱስ በደቡብ ገሊላ በኩል ሲያልፍ ሳለ በአንድ ስፍራ ስምዖን የሚባል አንድ ፈሪሳዊ ምሳ እንዲበላ ወደ ቤቱ ጋበዘው። ፈሪሳውያን፥ እንደምታስታውሱት፥ በጣም ሃይማኖተኞች እንደ ሆኑ የሚታሰቡ ሰዎች ነበሩ፤ በመንገድም ይሁን በቤታቸው በየቀኑ በተወሰኑ ሰዓቶች ስለ መጸለይ፥ በተወሰኑ ቀናት ስለ መጾም፥ ማለትም ምግብ ስላለመብላት፥ በየሳምንቱ ሦስት ጊዜ ወደ ምኵራብ ስለ መሄድ የወጡትን ሥርዓቶች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ነበርና፤ ለሰው እንዲታዩም ብዙ ነገር ያደርጉ ነበር፤ ሆኖም ከሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ብዙ ጊዜ ኀይለኞችና ጨካኞች ነበሩ። ደጎች ይመስሉ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሚመስሉት ደጎች አልነበሩም። ፈሪሳውያን በየስፍራው በልባቸው የኢየሱስ ጠላቶች ነበሩ። ይከታተሉት ነበር፤ ነገር ግን በወዳጅነት መንፈስ አልነበረም።
ይህ ፈሪሳዊ ስምዖን ባያምንበትም ኢየሱስን ሊያውቀውና ሊያነጋግረው ፈለገ። ነገር ግን ኢየሱስ ረቢ፥ ማለትም መምህር፥ የሆነ ተራ አናጢ ብቻ ስለ ሆነ በማዕረግ ከእርሱ ያነሰ እንደ ሆነ አሰበ፤ ስለዚህም አላከበረውም። አንድ ታላቅ ሰው ወደ ቤት በመጣ ጊዜ አገልጋዮቹ ጫማውን አውልቀው እግሩን ያጥቡ ነበር፤ ጠጕሩንም አበጥረው በራሱ ላይ ሽቱ ዘይት ያፈስሱ ነበር። ስምዖን ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም ለኢየሱስ አላደረገለትም። ወደ ቤቱ ብቻ ጋበዘው፤ በመንገድ በመሄዱ አቧራ ለለበሰው እግሩ መታጠቢያ ውኃ እንኳ ሳይሰጠው በማዕዱ ላይ የሚቀመጥበትን ስፍራ አመለከተው።
በዚያች አገር ሰዎች በምግብ ጊዜ በወንበር ላይ አይቀመጡም ነበር። በማዕዱ ዙሪያ መደገፊያዎች ወይም ድንክ አልጋዎች ይደረጉ ነበር፤ እንግዶቹም ግማሽ ተኝተው ግማሽ ተቀምጠው፥ ራሳቸውን ወደ ማዕዱ እግራቸውንም ከማዕዱ ወደ ውጭ አድርገው በእነርሱ ላይ ይደገፉ ነበር። ማዕዱን ይደርሱበትና ምግብ ወይም መጠጥ ራሳቸው ይወስዱ ነበር። የሚበላው ሥጋ እጅግ ጥቂት ነበረ፤ በማዕድ ላይ ከመቅረቡም በፊት ሁልጊዜ በትንንሹ ይቈረጥ ነበር፤ ስለዚህ እንግዶቹ ቢላዋ ወይም ሹካ አያስፈልጋቸውም ነበር። ከእያንዳንዱ የምግቡ ክፍል በኋላ አንድ አገልጋይ የውኃ ሳህንና ፎጣ ይዞ በመዞር የእንግዶቹን እጅ ያጥብ ነበር።
ኢየሱስ፥ ምናልባትም ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር፥ በምሳው ጊዜ በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ሰዎች በነጻነት ይገቡና ይወጡ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አንዲት ሴት ገብታ ዙሪያዋን ተመለከተች፤ ኢየሱስንም አይታ ወደ ተደገፈበት መደገፊያ ሄደች። በእጅዋም ሽቱ ዘይት የሞላበት ማሰሮ ነበረ። መክደኛውን ለማውጣት ሳትቆይ ማሰሮውን ሰበረችና ዘይቱን በእግሩ ላይ አፈሰሰችው። በረጅሙ በተዘረጋው ጠጕርዋ እግሩን አበሰች፤ በላያቸውም አለቀሰች፥ ብዙ እንባዋን በእግሩ ላይ እያፈሰሰች፤ ደጋግማም ሳመቻቸው።
የዚያ ስፍራ ሰዎች ሁሉ ይህች ሴት ማን እንደ ሆነች ያውቁ ነበር፤ የኖረችውንም ኑሮ ያውቁ ነበር። እርስዋ ደግ ሴት አልነበረችም፤ ኃጢአተኛ ነበረች እንጂ፤ የተከበሩ ሰዎችም ሁሉ ይንቁአት ነበር። ፈሪሳዊው ስምዖን ኢየሱስ እንደዚህች ያለችው ሴት እንድትነካው ስለ ፈቀደ ተደነቀ። በግልጥ ባይናገረውም በልቡ እንዲህ ብሎ አሰበ፦
«ይህ ሰው እንደሚሉት ነቢይ ሊሆን አይችልም፤ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህች ሴት ምን ያህል ርኵስ ፍጡር እንደ ሆነች ባወቀ ነበር፤ እጆችዋም እግሩን እንኳ እንዲነኩ ባልፈቀደ ነበር።»
ኢየሱስም ወደ ልቡ ሊመለከት ይችል ነበርና የፈሪሳዊውን ሐሳብ አወቀ። «ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ» አለው።
ስምዖንም «መልካም፥ መምህር ሆይ፥ ተናገር» ብሎ መለሰ።
ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ «ሁለት ሰዎች ዕዳ የነበረባቸው አንድ አበዳሪ ነበረ። አንዱ አምስት መቶ ብር፥ ሁለተኛውም አምሳ ብር ዕዳ ነበረበት። ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱም ዕዳውን መክፈል አልቻለም፤ ስለዚህ አበዳሪው ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ስምዖን ሆይ፥ ንገረኝ፤ ከእነዚያ ከሁለቱ ሰዎች ይህን ሰው አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?»
ስምዖንም «ብዙ የተተወለት ይመስለኛል» ብሎ መለሰ።
ኢየሱስም «በእውነት ፈረድህ» አለው። ከዚያም ወደ ሴቲቱ ዘወር ብሎ ለስምዖን መናገሩን ቀጠለ፤ «ይህችን ሴት ታያለህን? ወደ ቤትህ በገባሁ ጊዜ ለእግሬ ውኃ ስንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን እነሆ፥ በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። የእንኳን ደኅና መጣህ መሳም አልሳምኸኝም፤ ይህች ሴት ግን ከገባች ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ አፈሰሰችበት። ስለዚህ ስምዖን ሆይ፥ እልሃለሁ፥ ኃጢአትዋ ብዙ ቢሆንም ፍቅርዋ ታላቅ ነውና ተሰርዮላታል፤ ጥቂት የሚሰረይለት ግን ጥቂት ይወዳል።»
ከዚያም ሴቲቱን «ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» አላት።
ከእርሱ ጋር በማዕድ የነበሩትም እርስ በርሳቸው «ኃጢአትን ለማስተሰረይ ሥልጣን አለኝ የሚል ይህ ማን ነው?» እያሉ ያንሾካሹኩ ጀመር።
እርሱ ግን ሴቲቱን «እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ» አላት።
ከዚህ በኋላ መንደሮቹን እየጐበኘ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ለሕዝቡ እየነገረ ሄደ። የመረጣቸው አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ። ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ ኢየሱስ ከልዩ ልዩ በሽታ የፈወሳቸው አንዳንድ ሴቶች ነበሩ። አንድዋ ኢየሱስ ሰባት ርኵሳን መናፍስትን ያወጣላት መግደላዊት ማርያም ነበረች። ሌላይቱ በገሊላ ገዢ በንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ ቤተ መንግሥት ታላቅ ሹም የነበረው ኩዛ የሚባል የአንድ መኰንን ሚስት ዮሐና ነበረች። ሌላይቱም ሶስና ትባል ነበር፤ ከእነዚህም ጋር ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ። ከእነዚህም አንዳንዶቹ ባለ ጠጎች ነበሩ፤ ኢየሱስንም ለመርዳት ከገንዘባቸው በልግስና ይሰጡ ነበር።