ምዕራፍ 32 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ
ኢየሱስ የቀብርን ሰልፍ እንዴት እንዳቆመ
ኢየሱስ ቀደም ብሎ በባሕሩ አጠገብ ባሉት ተራሮች መካከል የሚገኙትን መንደሮች እንደ ጐበኘ፥ አሁን ደግሞ ለመስበክ በደቡባዊው የገሊላ ክፍል በኩል ጕዞ ጀመረ። ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትና እየሄደ ሲሄድ እየበዛ ከሚሄደው የተከታዮች ብዛት ጋር ሆኖ ከቅፍርናሆም ወጣ። በታቦር ተራራ አጠገብ አለፉ፤ ፀሐይ ልትጠልቅ ሲቀርብም በሌላ ተራራ፥ በሞሬ ኮረብታ፥ ግርጌ ወደምትገኝ ወደ አንዲት ትንሽ ከተማ ደረሱ። ይህች ስፍራ ናይን ትባል ነበር። ኢየሱስና ተከታዮቹ ከከተማይቱ በር ውጭ የቀብር ሰልፍ እንዲያልፍ ቆም አሉ። ከፊት ለፊት ሴቶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያለቀሱ፥ እጆቻቸውን ወደ ላይና ወደ ታች እያወዛወዙ ስለ ሞተው ጐበዝ የልቅሶ ዜማ ያዜሙ ነበር። አስከሬኑ በረጃጅም የበፍታ ጨርቆች ተጠቅልሎ በቃሬዛ ላይ ተኝቶ ነበር፤ ተሸካሚዎችም ይሸከሙት ነበር። ከኋላውም አንዲት አሮጊት ሴት፥ የጐበዙ እናት፥ ትሄድ ነበር፤ እርስዋም መበለት ነበረች፤ አንድያ ልጅዋንም ልትቀብር ትሄድ ነበር፤ ከእርስዋም ጋር ልጅዋን በማጣትዋ ለመበለቲቱ ያላቸውን ኀዘን የሚያሳዩ ከከተማይቱ ሰዎች ብዙዎች ነበሩ።
ኢየሱስም ይህችን የምታለቅስ እናት ባያት ጊዜ እጅግ አዘነላትና «አታልቅሽ» አላት። ወደ ፊትም ቀርቦ አስከሬኑ የተኛበትን ቃሬዛ ነካ። የተሸከሙት ሰዎችም መልኩ ኃይልን በሚያሳየው በዚህ እንግዳ መምጣት ተደንቀው ቆሙ። ኢየሱስም በሞተው ጐበዝ አጠገብ ቆሞ እንዲህ አለ፦
«አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ!»
ወዲያውም ጐበዙ ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ። ኢየሱስም እጁን ይዞ ለእናቱ ሰጣት። እርስዋም በእቅፍዋ ተቀበለችው፤ የቀዘቀዘውም ሰውነቱ አሁን በሕይወት ሞቆ፥ የፈዘዙትም ዓይኖቹ አሁን አብርተው አገኘችው። በዚያ ቀን የሞተው ልጅዋ እንደ ገና ሕያው ሆነ።
ይመለከቱ የነበሩት ሰዎችም በእውነት ድንቅ ሥራ እንደ ተሠራ አሁን ተሰማቸው። ከእነርሱ ብዙዎቹ ኢየሱስን ቀድሞ አይተውት ያውቁት ነበር፤ ያላዩትም እንኳ ስለ እርሱ ሰምተው ነበርና «ይህ ያ ከናዝሬት የመጣው ታላቅ መምህር መሆን አለበት!» አሉ። ብዙዎቹ በፊቱ በግንባራቸው ተደፉ፤ አንዳንዶቹም «ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል» አሉ፤ ሌሎቹም «በእውነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ!» አሉ።
ኢየሱስ የሞተውን ሰው ከሞት እንዳስነሣ የሚናገረው ወሬ በምድሪቱ ሁሉ፥ በዙሪያዋም ወዳሉት አገሮች እንኳ ተሰማ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስን ለማየትና ቃሉን ለመስማት የሚፈልጉ ሰዎች እየበዙ ሄዱ።
ኢየሱስ ከተሞቹን እየጐበኘ፥ ሕዝቡን እያስተማረና ድውዮችን እየፈወሰ በደቡብ ገሊላ በቀስታ ሲጓዝ ሳለ ሁለት ሰዎች ሊያዩት ፈልገው መጡ። እነዚህ ሰዎች ሄሮድስ ባስገባው ወኅኒ ውስጥ ገና የነበረው የመጥምቁ ዮሐንስ ተከታዮች ነበሩ። ዮሐንስ በወኅኒው ሆኖ ኢየሱስ ስለሚሠራው ሥራና ስለሚያስተምረው ትምህርት ሰማ። ምናልባት ዮሐንስ ኢየሱስ እንዲሁ እንደ መምህር በምድሪቱ ወዲያና ወዲህ ከመዞር ይልቅ መንግሥቱን ወዲያው ያቆማል ብሎ ይጠብቅ ነበር ይሆናል። ደግሞም ምናልባት ዮሐንስ በወኅኒ ተዘግቶ ተስፋ ቈርጦና ተጠራጥሮ ይሆናል። በቀደሙት ቀናት ለሕዝቡ ሁሉ ኢየሱስ የሚመጣው ንጉሥ እንደ ሆነ፥ እርሱም የጫማውን ጠፍር ለመፍታት እንኳ እንደማይገባው ያህል ከእርሱ እጅግ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናግሮ ነበር። አሁን ግን እነዚህ ሁለት ሰዎች ከዮሐንስ ዘንድ ይህን ጥያቄ ወደ ኢየሱስ ይዘው መጡ፦
«መጥምቁ ዮሐንስ እንድንጠይቅህ ወደ አንተ ላከን—የሚመጣው፥ ተስፋ የተሰጠው የእስራኤል ንጉሥ አንተ ነህን? ወይስ ሌላውን እንጠብቅ?»
ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ ወዲያው አልመለሰም። ለጊዜው ጥያቄው እንዳልተጠየቀ ሆኖ፥ እነዚህን ሁለት ሰዎች ቆመው እንዲቆዩ ትቶ በዙሪያው ወዳሉት ሰዎች ዘወር አለ።
በመድኃኒታችን እግር አጠገብ ብዙ የሚሠቃዩ ሰዎች ነበሩ፤ ወዳጆቻቸው በአልጋ ላይ ያመጡአቸው ድውዮች፥ ማየትን የሚለምኑ ዕውሮች፥ እጆቻቸውን ወደ እርሱ የሚዘረጉ ደንቆሮዎችና ዲዳዎች፥ አስከፊ ቍስል የሞላባቸው ለምጻሞች፥ ርኵሳን መናፍስት ያደሩባቸው ቅበዝባዦች ነበሩ። ኢየሱስ የእነዚህን ሁሉ የተቸገሩ ሰዎች ችግር ፈጸመላቸው። እጁን በድውዮች ላይ ጫነ፤ እነርሱም ተፈውሰው ተነሡ፤ የዕውሮችን ዓይንና የደንቆሮዎችን ጆሮ ዳሰሰ፤ ማየትንና መስማትንም ሰጣቸው፤ ለእያንዳንዱ ለምጻም አዲስ፥ ንጹሕና ፍጹም ሰውነት ሰጠው፤ ርኵሳን መናፍስትንም በቃሉ አወጣ። ከዚያም በኋላ እንደ ልማዱ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ሰው ሁሉ እንዴት ወደ እርሱ ሊገባ እንደሚችል ለሕዝቡ ተናገረ።
በመጨረሻ የጠዋቱ የፈውስና የትምህርት ሥራው በተፈጸመ ጊዜ ከመጥምቁ ዮሐንስ ወደ መጡት ወደ እነዚህ ሁለት መልክተኞች ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፦
«ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን በወኅኒው ላለው ለዮሐንስ አውሩለት። ቀድሞ ዕውሮች የነበሩ አሁን ያያሉ፤ አንካሶች አሁን ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ርኵሳን መናፍስት ያደሩባቸው ሰዎች ከኃይላቸው ነጻ ወጥተዋል። ሙታን ከሞት እንደ ተነሡ ደግሞ ሰምታችኋል፤ ለድሆችም ወንጌል ሲሰበክ አድምጣችኋል። ሂዱና ያያችሁትንና የሰማችሁትን ይህን ሁሉ ለዮሐንስ ንገሩት። ከዚያም ዮሐንስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያስብ፤ ይመጣል ብሎ ተስፋ የሰጠው እኔ እንደ ሆንሁ ወይም እንዳልሆንሁ ይፍረድ።»
መጥምቁ ዮሐንስን ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው የእስራኤል ንጉሥና የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ ወደ ሙሉ እምነት ለመመለስ ይህ «ሄዳችሁ እኔ መድኃኒት እንደ ሆንሁ ለዮሐንስ ንገሩት» ብሎ መልስ ከመላክ እጅግ የተሻለ መንገድ ነበረ። ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው ጌታ እንደ ሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሁን በእጁ ስለሚኖሩ የዮሐንስ እምነት ይበልጥ ይጸናል።
እነዚህ ከመጥምቁ ዮሐንስ የመጡ መልክተኞች ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ለሕዝቡ ይናገር ጀመር። አንዳንዶች ዮሐንስ ይህን ጥያቄ ወደ ኢየሱስ በመላኩ ደካማነትን እንዳሳየና ሐሳቡን እንደ ለወጠ አስበው ይሆናል። ኢየሱስም ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦
«ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? አይደለም፤ ይህ ዮሐንስ በነፋስ የሚናወጥ ደካማ ሸምበቆ አልነበረም። የመሳፍንትን ልብስ የለበሰና ጣፋጭ ምግብ የሚበላ ሰውን ልታዩ ወጣችሁን? አይደለም፤ ያ በምድረ በዳ ቁርበት የለበሰው ሰው እንደዚያ ያለ የመሳፍንት ዓይነት ሰው አልነበረም። እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ለማየት ወደ ነገሥታት ቤተ መንግሥት ትሄዳላችሁ። እንግዲያስ በእርግጥ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን፥ ከእግዚአብሔር የተላከን ሰው ነውን? አዎን እላችኋለሁ፥ መጥምቁ ዮሐንስ በእውነት ነቢይ ነበረ፤ ከነቢይም የሚበልጥ ነበረ። ለንጉሡ ራሱ መንገድን ያዘጋጅ ዘንድ የተላከ የንጉሡ መልክተኛ ነበረ። በእውነት ለሁላችሁ እላችኋለሁ፥ ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ሰው ወደዚህ ዓለም ከቶ አልተወለደም። ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉ የሚያንሰው ከዮሐንስ እንኳ ይበልጣል።»
ኢየሱስ ይህን ሲል፥ ወንጌልን የሰሙ ሁሉ ሊገቡ እንደሚችሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የቻሉት ሰዎች ለመንግሥቱ መንገድን ከሚያዘጋጁት ከታላላቆቹ እንኳ ይበልጣሉ ማለቱ ነበረ።