የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ደጉ የመቶ አለቃ

ምዕራፍ 31 · 2 ደቂቃ ንባብ · 2 ደቂቃ ማዳመጥ

ደጉ የመቶ አለቃ

በቅፍርናሆም ከተማ የሮም ሠራዊት ሹም የሆነ አንድ የመቶ አለቃ ነበረ፤ ከእርሱም በታች አንድ መቶ ወታደሮች ያሉበት ጭፍራ ነበረ። ይህ ሰው ከአይሁድ ወገን አልነበረም፤ ከአሕዛብ ወገን ነበረ እንጂ። «አሕዛብ» የሚለው ስም አይሁድ ከራሳቸው ዘር ውጭ ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሰጡት ስም ነበረ። አይሁድ ከራሳቸው በቀር በዓለም ያለውን ሕዝብ ሁሉ አሕዛብ ብለው ይጠሩት ነበር።

ይህ የመቶ አለቃ ደግ ሰው ነበረ፤ አይሁድንም እጅግ ይወድድ ነበር፤ በእነርሱ በኩል ስለ እውነተኛው አምላክ ሰምቶ እርሱን ማምለክ ተምሮ ነበርና። አይሁድን ስለ ወደደ በገዛ ገንዘቡ ምኵራብ ሠርቶ በስጦታ ሰጣቸው። ኢየሱስ በሰንበት ቀናት ያስተምርበት የነበረው ምኵራብ ይኸው ራሱ ሳይሆን አይቀርም።

የመቶ አለቃው እጅግ የሚወድደው አንድ ብላቴና አገልጋይ ነበረው፤ ይህም ልጅ በሽባ በሽታ እጅግ ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር። የመቶ አለቃው ኢየሱስ ድውዮችን መፈወስ እንደሚችል ሰምቶ ነበር፤ ስለዚህ «ሽማግሌዎች» የሚባሉትን የምኵራቡን አለቆች ወደ ኢየሱስ ሄደው እጁን በልጁ ላይ ጭኖ ይፈውሰው ዘንድ ወደ ቤቱ እንዲመጣ እንዲለምኑት ጠየቃቸው። ሽማግሌዎቹም ኢየሱስ ከዚያ በኋላ በተራራ ላይ ሰብኮ ወደ ቅፍርናሆም እንደ ገና በመጣ ጊዜ ወዲያው አነጋገሩት። ከእነርሱ ጋር ወደ መቶ አለቃው ቤት ሄዶ አገልጋዩን እንዲፈውስ ለመኑት፤ ደግሞም እንዲህ አሉ፦

«ሰውየው የሚገባው ሰው ነው፤ ልትረዳውም ይገባል፤ ከአሕዛብ ወገን ቢሆንም ሕዝባችንን ይወድዳልና፤ ምኵራባችንንም እርሱ ሠራልን።»

ኢየሱስም «እመጣና እፈውሰዋለሁ» አለ።

ነገር ግን ኢየሱስ ወደ መቶ አለቃው ቤት ሲሄድ፥ ሽማግሌዎቹና ሌላ ድንቅ ፈውስ ለማየት ተስፋ ያደረጉ ብዙ ሕዝብም አብረውት ሳሉ፥ የመቶ አለቃው ወዳጆች ተገናኙትና ይህን መልእክት አደረሱለት፦

«ጌታ ሆይ፥ ወደ ቤቴ ለመምጣት አትድከም፤ እንደ አንተ ያለ ታላቅ በቤቴ ጣራ በታች ሊገባ አይገባኝምና፤ ወደ አንተ የላክሁትም እኔ ራሴ ላነጋግርህ ስለማይገባኝ ነው። ነገር ግን ባለህበት ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ለሌሎች ሥልጣንና ትእዛዝ የምገዛ ሰው ብሆንም፥ ፈቃዴን የሚፈጽሙ ወታደሮች ከእኔ በታች አሉኝ። አንዱን ‹ሂድ› ብለው ይሄዳል፤ ሌላውን ‹ና› ብለው ይመጣል። ባሪያዬንም ‹ይህን አድርግ› ብለው ያደርጋል። አንተም ደግሞ ለማዘዝና ለመታዘዝ ሥልጣን አለህ። ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።»

ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ በዚህ ሰው እምነት ተደነቀ። ይከተለው ወደ ነበረውም ሕዝብ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፦

«እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል ሁሉ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም። ደግሞም እላችኋለሁ፥ እንደዚህ ሰው ያሉ ከእስራኤል ወገን ያልሆኑ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በእግዚአብሔር መንግሥት ይቀመጣሉ። ከእስራኤል ልጆች ግን ብዙዎች ስላላመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከቶ አይገቡም፤ በውጭ ወዳለው ጨለማ ይጣላሉ እንጂ።»

ኢየሱስም ከመቶ አለቃው ቤት ለመጡት እንዲህ አለ፦

«ተመልሳችሁ ለዚህ ሰው በስሜ ‹እንዳመንህ ይሁንልህ› በሉት።»

እነርሱም ወደ መቶ አለቃው ቤት ሄዱ፤ ለሞት ተቃርቦ የነበረውንም አገልጋይ ከሽባው ነጻ ሆኖ ወደ ፍጹም ጤናው ተመልሶ አገኙት።


ቀዳሚ ቀጣይ