የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በተራራው ላይ

ምዕራፍ 30 · 4 ደቂቃ ንባብ · 6 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በተራራው ላይ

ከቅፍርናሆም በደቡብ ምዕራብ ዐሥራ ሁለት ማይል ያህል፥ ከገሊላ ባሕርም በምዕራብ ስድስት ማይል ርቆ ከብዙ ማይል ርቀት የሚታይ አንድ ተራራ ይገኛል። ዛሬ «ቁርን ሐጢን» ይባላል፤ ትርጓሜውም «የሐጢን ሁለቱ ቀንዶች» ማለት ነው። ይህ ስም የተሰጠው ተራራው በሁለቱ ጫፎቹ አንድ አንድ ራስ ስላለውና በመካከላቸውም ሰፊ ሸለቆ ስላለ ነው፤ ቅርጹም ኮርቻ ወይም ሁለት ሻኛ ያለው ግመል እንዲመስል ያደርገዋል። በዚህ ተራራ አጠገብ ወደ እስራኤል ምድር ክፍሎች ሁሉ ማለት ይቻላል የሚሄዱ መንገዶች ነበሩ፤ ስለዚህ ከየትኛውም ስፍራ ሊደረስበት ይቻል ነበር።

ኢየሱስ ወደዚህ ተራራ እንደሚመጣ ወሬው በምድሪቱ ሁሉ ተሰማ፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ኢየሱስን ለማየት እየጠበቁ በሁለቱ ራሶቹ መካከል ባለው ሸለቆ ተሰበሰቡ። እርሱም ወደ ተራራው መጥቶ ብቻውን ከኮረብቶቹ ወደ አንዱ ራስ ወጣ። ኢየሱስ ሌሊቱን ሁሉ በዚያ ከሰማያዊ አባቱ ጋር በጸሎት አደረ፤ የሚሠራው ታላቅ ሥራ ነበረውና፥ ኢየሱስም ከማንኛውም ታላቅ ሥራ በፊት ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። በነጋም ጊዜ በፊቱ ከነበሩት እጅግ ብዙ ሕዝብ መካከል ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ጠራ፤ እነርሱም ሁልጊዜ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ በሚሄድበት ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ፥ ትምህርቱን እንዲሰሙና በቃላቸው እንዲያጠኑት፥ በሚልካቸውም ጊዜ ቃሉን ለመስበክ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ነበር። እነዚህን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ኢየሱስ በኋላ «ሐዋርያት» ብሎ ጠራቸው፤ ትርጓሜውም «የተላኩ ሰዎች» ማለት ነው፤ ብዙ ጊዜ ግን «ዐሥራ ሁለቱ» ይባሉ ነበር። ደግሞም «ደቀ መዛሙርት» ተብለው ይጠራሉ፤ ምንም እንኳ «ደቀ መዛሙርት» የሚለው ቃል ለኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ የሚነገር ቢሆንም።

ከዐሥራ ሁለቱ ሰዎች አብዛኞቹ ከዚህ በፊት ተጠርተው ለጥቂት ጊዜ ከኢየሱስ ጋር ኖረው ነበር። ሌሎቹ ግን ኢየሱስ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የጠራቸው አዲሶች ነበሩ። ስማቸው ሁለት ሁለት ሆኖ በጥንድ ተዘርዝሮአል። እነርሱም ስምዖን ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ፤ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፤ ፊልጶስና ናትናኤል ተብሎ የሚጠራው ወዳጁ በርተሎሜዎስ፤ ቶማስና ቀድሞ ቀራጭ የነበረው ማቴዎስ፤ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፤ «ቀናተኛ» የተባለው ሌላው ስምዖን፤ በኋላም ከዳተኛ ሆኖ ጌታውን ለጠላቶቹ የሸጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ። ስለ አብዛኞቹ ሰዎች የምናውቀው እጅግ ጥቂት ነው፤ አንዳንዶቹ ግን በኋለኞቹ ዓመታት ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ሥራ ሠሩ። ስምዖን ጴጥሮስ ፈጣን አእምሮና ዝግጁ አንደበት ያለው ሰው ስለ ነበረ ሁልጊዜ በዐሥራ ሁለቱ መካከል መሪ ነበረ፤ ዮሐንስም ከዚያ ዘመን ብዙ ቆይቶ በዓለም ካሉ መጻሕፍት እጅግ ድንቅ ከሆኑት አንዱን «የዮሐንስ ወንጌል»ን ጻፈ።

ኢየሱስ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እነዚህን ሰዎች በአጠገቡ እንዲቆሙ ጠራቸው። ከዚያም ከተራራው ራስ በሁለቱ ጫፎች መካከል ወዳለው ሸለቆ ወረደ። የመረጣቸው ዐሥራ ሁለቱ ሰዎች በዙሪያው፥ ከእነርሱም ባሻገር እጅግ ብዙ ሕዝብ ሳሉ ተቀመጠ። ለዐሥራ ሁለቱና ለሚያደምጠው ሕዝብ ኢየሱስ «የተራራው ስብከት» የተባለውን ያን ታላቅ ስብከት ሰበከ። ማቴዎስ ጻፈው፤ እናንተም በወንጌሉ፥ በአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መጽሐፍ፥ በአምስተኛው፥ በስድስተኛውና በሰባተኛው ምዕራፎች ልታነቡት ትችላላችሁ። ኢየሱስ ይህን ታላቅ ስብከት አስታውሶ ዓለም ሁሉ እንዲያነበው ሊጽፍ የሚችለውን ቀራጩን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ እንዲሆን መጥራቱ እንዴት መልካም ነበር! ከዚህ ከተራራው ስብከት ጥቂት ክፍሎችን ብቻ እዚህ እንሰጣለን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ በማጽናኛ ቃል ጀመረ፦

«በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።»

ከዚያም በሰዎች መካከል ምን ሊሆኑ እንደሚገባቸው ለደቀ መዛሙርቱ ተናገረ፦

«እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።»

ምናልባትም በአቅራቢያ በአንድ ኮረብታ ራስ ላይ ተሠርታ በዙሪያው ሁሉ የምትታይ ከተማን እያመለከተ እንዲህ ብሎ ቀጠለ፦

«እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።»

በደሉአቸው ሰዎች ላይ ምን ዓይነት ስሜትና አድራጎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፦

«‹ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ› እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ፤ በሰማያት ያለው የአባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ፤ እርሱ ፀሐዩን በክፉዎችና በደጎች ላይ ያወጣልና፥ ዝናቡንም በጻድቃንና በዓመፀኞች ላይ ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? የምትንቁአቸው ቀራጮች እንኳ ያንኑ ያደርጋሉ። ወዳጆቻችሁንም ብቻ ሰላም ብትሉ ከሌሎች በምን ትበልጣላችሁ? አሕዛብ እንኳ ያንኑ ያደርጋሉና። የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ልትሆኑ ይገባችኋል።»

ደግሞም ሰዎች በሕይወታቸው ሊፈልጉት ስለሚገባቸው ዓላማ ተናገረ፦

«ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።»

«ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ይህ ዓለም ለሚያመልከው አምላክ ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ በእርግጥ ሕይወት ከመብል፥ ሰውነትም ከልብስ ይበልጣል! በላያችሁ የሚበርሩትን ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከወፎች አትበልጡምን?»

«ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ቢሆንም ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም! እንግዲህ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያብበውን ነገም ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እግዚአብሔርን ጥቂት የምትታመኑ ሆይ፥ እናንተንማ ይልቁን አያለብሳችሁምን?»

«እንግዲህ ‹ምን እንበላለን?› ወይም ‹ምንስ እንጠጣለን?› ወይም ‹የምንለብሰውን ልብስ እንዴት እናገኛለን?› ብላችሁ አትጨነቁ። ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ፥ እንደ ፈቃዱም ጽድቅን አድርጉ፤ ያን ጊዜም ይህ ሁሉ ለእናንተ ይሆናል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለእያንዳንዱ ቀን የራሱ ችግር ይበቃዋል።»

ኢየሱስ ስብከቱን ሲፈጽም የተናገረው ይህ ነው፦

«ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።»

«ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።»

ኢየሱስ ይህን ቃል በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በአስተማሩ መንገድ ተገረሙ። እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን እንደ ጌታ በሥልጣን ይናገር ነበር። ብዙዎቹ ጻፎች ሲያስተምሩ በቀደሙት መምህራን ስም ይናገሩ ነበር፤ «ረቢ ዮናታን ይህን አለ»፥ ወይም «ረቢ ሂሌል ያን አለ» ይሉ ነበር። ኢየሱስ ግን «ይህን እላችኋለሁ» እያለ በራሱ ስም ይናገር ነበር።


ቀዳሚ ቀጣይ