የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
የሰንበት ጌታ

ምዕራፍ 29 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

የሰንበት ጌታ

ኢየሱስ ሰንበትን የሚሽር ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጥያቄ ወደ ገሊላ ከተመለሰ በኋላ ብዙም ሳይቈይ እንደ ገና ተነሣ። በአንድ ሰንበት ቀን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በእህል እርሻ መካከል ያልፍ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ተርበው ስለ ነበር እየሄዱ የስንዴውን እሸት ቀጠፉ፥ በእጃቸውም አሹት፥ ገለባውንም እፍ ብለው አስወግደው ፍሬውን በሉ። የእስራኤላውያን ሕግ በእህል እርሻ አጠገብ የሚያልፍ ሰው ሁሉ ሊበላ የሚወደውን ያህል እንዲወስድ ይፈቅድ ነበር፤ ወደ ቤቱ ግን ምንም እንዳይወስድ ይከለክል ነበር።

ሰንበትን በመጠበቅ ሥርዓታቸው እጅግ ጥንቁቆች ለነበሩት ለፈሪሳውያን ግን እህሉን መቅጠፍ በማጭድ እንደ ማጨድ፥ በእጅ መያዝ ሸክም እንደ መሸከም፥ በእጅ ማሸትም እንደ ማበራየት ነበረ፤ እነዚህንም በሳምንቱ በሰባተኛው ቀን ማድረግ ሰንበትን መሻር ነበረ። እነዚህ ሥርዓቶች በእግዚአብሔር የተሰጡ ሳይሆኑ በጻፎች የተሠሩ ነበሩ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ለእነርሱ ምንም ግድ እንዳይሰጡ አስቀድሞ አስተምሮአቸው ነበር።

ፈሪሳውያን ቢቻላቸው ኢየሱስንና ተከታዮቹን ክፉ ሊባል የሚችል ነገር ሲያደርጉ ወይም ሲናገሩ ለመያዝ ዘወትር ይጠባበቁአቸው ነበር። ኢየሱስንም እንዲህ አሉት፦

«ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ቀን የተከለከለውን ሲያደርጉ ታያለህን? የእህሉን እሸት ይቀጥፋሉ፥ በእፍኝ ይዘው በእጃቸው ያሹታል።»

ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፦ «ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል በሸሸ ጊዜ ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን? ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደ ገባ፥ ለእግዚአብሔርም መባ ሆኖ በገበታው ላይ የተቀመጠውን፥ ከካህናት በቀር ማንም ሊበላው ያልተፈቀደውን የተቀደሰውን እንጀራ እንደ ወሰደ፥ ራሱም በልቶ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች እንደ ሰጣቸው አላነበባችሁምን? ደግሞም በቤተ መቅደስ ያሉ ካህናት ለመሥዋዕት እንስሳትን ማረድ፥ በመሠዊያው ላይ እንጨት መደርደርና ሌሎችንም ብዙ ነገሮች፥ ሥራን ሁሉ እንደሚሠሩ አታውቁምን? ቢሆንም እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ስለ ሆኑ በደል አይሆንባቸውም፤ የሚያስፈልግ ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ቅዱስ ቀን ሊደረግ ይችላልና። ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም። እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፤ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።»

በሌላ ሰንበት ቀን ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለማምለክና ቃሉን ለመስበክ ወደ ጸሎት ቤት ገባ። በዚያም እጁ የሰለለችና የማትሠራ አንድ ሰው ነበረ። ፈሪሳውያንም ኢየሱስ ይህን ሰው በሰንበት ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር። እንዲፈውሰው ተስፋ ያደርጉ ነበር፤ ይህም ለዚያ ድሀ ሽባ ሰው ስለ አዘኑ ሳይሆን በኢየሱስ ላይ የሚናገሩትን ነገር ለማግኘት ስለ ጓጉ ነበር።

ኢየሱስ እጁ የሰለለችውን ሰው «ተነሥተህ ወደ መካከል ና» አለው። ሰውዬውም በሁሉም ፊት ቆመ፤ ኢየሱስም ጠላቶቹን ትኵር ብሎ እየተመለከተ እንዲህ አለ፦

«በሰንበት ቀን በጎ ማድረግ ወይስ ክፉ ማድረግ፥ ነፍስን ማዳን ወይስ እናንተ ለማድረግ እንደምትሞክሩት ሰውን ለመግደል መሞከር ሕግን መተላለፍ ነውን? ከእናንተ አንድ በግ ብቻ ያለው ሰው በሰንበት ቀን ጕድጓድ ውስጥ ወድቆ ቢያገኘው ይዞ አያወጣውምን? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት የርኅራኄንና የእርዳታን ሥራ መሥራት ተገቢ ነው።»

ልባቸው እጅግ ደንዳና ስለ ሆነ እያዘነና እየተከፋ ጠላቶቹን ዙሪያውን በቍጣ ተመለከታቸው። እነርሱም አንድ ቃል የሚናገሩት አጡ፤ ጥቂት ከጠበቀም በኋላ እጁ ወደ ሰለለችው ሰው ዘወር ብሎ እንዲህ አለው፦

«እጅህን ዘርጋ!»

ሰውዬውም ክንዱን ዘረጋ፤ የሰለለችውም እጅ ወዲያውኑ ዳነች፥ በረታችም፤ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች። ኢየሱስ ሄደ፤ ፈሪሳውያን ግን በእርሱ ላይ ቍጣ ሞላባቸው። ኢየሱስን የሚገድሉበትን መንገድ እየፈለጉ እርስ በርሳቸው ተማከሩ፤ ንጉሡ ኢየሱስ እንዲገደል እንዲያዝዝ ሊያግባቡት ይችሉ እንደ ሆነም ለማየት የገሊላ ገዥ የነበረውን የንጉሥ ሄሮድስን ወዳጆች ጠሩ።

ኢየሱስ ግን የጠላቶቹን ዕቅድ ከምንም ሳይቈጥር ማስተማሩንና ድውዮችን መፈወሱን ቀጠለ። የፈወሳቸውንም ሰዎች ወጥተው ስለ እርሱ ለሌሎች እንዳይናገሩ፥ ነገር ግን በቤታቸው በጸጥታ እንዲቀመጡ ነገራቸው፤ ሊሰሙት የሚመጡት ሕዝብ አስቀድሞ ብዙ ነበሩና፥ ከዚያ ይበልጥ እንዲበዙ አልፈለገም። ከምድሪቱ ክፍሎች ሁሉ፥ ደግሞም ከእስራኤል ምድር ውጭ ካሉ ስፍራዎች፥ በሰሜን ከጢሮስና ከሲዶና አገር፥ በደቡብም ከኤዶምያስ ወይም ከኢዶምያስ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰቡ። በኢየሱስ ዙሪያ ተጨናነቁ፥ ያጋፉትም ነበር፤ ስለዚህ ለዕረፍትና ለጸጥታ ወደ ባሕሩ ይወስዱት ዘንድ ትንሽ ታንኳ በአጠገቡ እንዲያቆዩለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።


ቀዳሚ ቀጣይ