የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
በመጠመቂያው አጠገብ የነበረው ሽባ

ምዕራፍ 28 · 3 ደቂቃ ንባብ · 4 ደቂቃ ማዳመጥ

በመጠመቂያው አጠገብ የነበረው ሽባ

ሌላ በዓል በኢየሩሳሌም የሚከበርበት ጊዜ ደረሰ፤ ኢየሱስም ባለፈው ዓመት እንዳደረገው ሊያከብረው ወጣ። ዮሐንስ በወንጌሉ በጻፈው ታሪክ ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ስላልተጠቀሱ በዚህ ጕዞ ከእርሱ ጋር ነበሩ ወይም አልነበሩም እንደ ሆነ አናውቅም።

ኢየሱስ በከተማይቱ በነበረበት ጊዜ በአንድ ሰንበት ቀን ከቤተ መቅደሱ ብዙም በማይርቅ በአንድ የሕዝብ መታጠቢያ አጠገብ አለፈ። ይህም ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ ሊታጠቡበት የሚችሉበት ታላቅ ኵሬ ወይም የውኃ ማጠራቀሚያ ነበረ፤ በአጠገቡም ቅስት ያለው ጣሪያ የተሠራላቸው አምስት መመላለሻዎች ነበሩ። ኢየሱስ ወደ ኵሬው በመጣ ጊዜ እነዚህ መመላለሻዎች በደዌ በሚሠቃዩ ሰዎች ተጨናንቀው ነበር። አንዳንዶቹ ዕውሮች፥ አንዳንዶቹ አንካሶች ነበሩ፤ ሌሎቹም እግራቸው ወይም እጃቸው የሰለለና ሽባ የሆነ ነበሩ።

በዚህ መታጠቢያ ውስጥ ያለው ውኃ በተወሰነ ጊዜ ይፈላና ከፍ ይል ነበር፤ ከዚያም ተመልሶ ይወርድና ጸጥ ይል ነበር። ሕዝቡ ይህ የውኃ መፍላት የሚሆነው ማንም የማያየው መልአክ ወርዶ ኵሬውን ስለሚያናውጥ እንደ ሆነ ያምኑ ነበር። ደግሞም ውኃው በሚፈላበት በዚያ ጊዜ የታመመ ሰው ሁሉ በኵሬው ውስጥ ቢታጠብ እንደሚድን ያምኑ ነበር። ውኃቸው በሽታን የሚፈውስ ብዙ ምንጮች እንዳሉ እናውቃለን፤ ይህም ኵሬ ጤናን ከሚሰጡ ከእነዚህ ምንጮች አንዱ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ በዚያ በመታጠቢያው አጠገብ በምንጣፍ ላይ ተኝቶ ያለ፥ አርባ ዓመት ለሚያህል ጊዜ መራመድ ያቃተውና ረዳት የሌለው አንድ ሰው አየ። ሁሉን የሚያውቀው ኢየሱስ ይህ ሰው ብዙ ዘመን ታሞ እንደ ኖረ አወቀ። እንዲህም አለው፦

«ልትድን ትወዳለህን?»

ይህ ሰው ከዚያ በፊት ኢየሱስን አይቶት አያውቅም ነበር፤ ማን እንደ ሆነም አላወቀም።

«ጌታ ሆይ፥» ብሎ መለሰ፥ «ውኃው በሚናወጥበት ጊዜ ወደ መታጠቢያው የሚያስገባኝ ሰው የለኝም፤ እኔ እየተሳብሁ ወርጄ ወደ ውኃው ልገባ ስሞክር መራመድ የሚችል ሌላ ሰው ቀድሞኝ ይገባል።»

ኢየሱስም እንዲህ አለው፦

«ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ!»

ሽባው ሰው እንዲህ ያለ ቃል ከቶ ሰምቶ አያውቅም ነበር፤ ነገር ግን ቃሉ እንደ ተነገረ አዲስ ኃይል በሰውነቱ ውስጥ ሲሰራጭ ተሰማው። በሠላሳ ስምንት ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ቆመ፤ ምንጣፉንም አንሥቶ ጠቀለለውና በትከሻው ላይ አደረገው። ከዚያም ሸክሙን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ይሄድ ጀመር።

ይህ የሆነው በሰንበት ቀን እንደ ነበረ ታስታውሳላችሁ። አይሁድ ሰንበትን በመጠበቅ እጅግ ጥንቁቆች ነበሩ። እግዚአብሔር ከብዙ ዓመታት በፊት ለአባቶቻቸው «የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ» ብሎ ነበር። አይሁድ ግን በዚህች ትእዛዝ ላይ ብዙ የማይጠቅሙ ሥርዓቶችን ጨምረው ነበር። በዚያ ቀን እሳት ማንደድ አይችሉም ነበር፤ ይህ ሥራ መሥራት ነውና፤ ብዕርም መያዝ አይችሉም ነበር፤ ይህ ሸክም መሸከም ነውና። እነዚህ ትንንሽ ሥርዓቶች በእግዚአብሔር የተሰጡ አልነበሩም፤ በጻፎች ወይም በሕግ መምህራን የተሠሩ ነበሩ እንጂ።

አንዳንድ ሰዎች ይህ ሰው የምንጣፉን ጥቅል ተሸክሞ በመንገድ ሲሄድ አዩት። እንዲህም አሉት፦

«ቁም! ዛሬ ሰንበት እንደ ሆነ አታውቅምን? አልጋህን ልትሸከም መብት የለህም።»

ሰውዬው ግን ሸክሙን አላስቀመጠም። እንዲህም አለ፦ «አርባ ዓመት ያህል ሽባ ነበርሁና አንድ ሰው በኵሬው አጠገብ ረዳት አጥቼ ተኝቼ አየኝ። ይህ ሰው አዳነኝ፤ ‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ› ያለኝም እርሱ ነው።»

አይሁድም «በሰንበት ቀን አልጋህን እንድትሸከም የነገረህ ይህ ሰው ማን ነው?» አሉት።

የተፈወሰው ሰው ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም ነበር፤ ብዙ ሰዎች በአጠገቡ ቆመው ነበርና፥ ኢየሱስም ሰውየውን ከፈወሰ በኋላ ማንም ሳያስተውለው ሄዶ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰውዬው ስለ ፈውሱ እግዚአብሔርን ለማመስገን ወደ ቤተ መቅደስ ወጣ፤ በዚያም ፈዋሹን አገኘው፥ ስሙንም ለመጀመሪያ ጊዜ አወቀ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው፦

«ለብዙ ዓመታት ረዳት አልባ ካደረገህ ደዌ አሁን ተፈትተሃል። ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ከእንግዲህ ወዲህ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አትሥራ።»

ሰውዬውም ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። የአይሁድ አለቆች፥ ካህናቱ፥ ጻፎቹና ፈሪሳውያን፥ ይህን ሰው በሰንበት ስላዳነውና በዚያም ቀን ምንጣፉን እንዲሸከም ስለ ነገረው በኢየሱስ ላይ እጅግ ተቈጡ። አለቆቹም ሰንበትን የሚሽር ነው፥ ማንም ቃሉን ሊሰማ አይገባም እያሉ ሕዝቡን በኢየሱስ ላይ ሊያነሣሡ ሞከሩ።

ኢየሱስ ግን «አባቴ ለሰዎች መልካም እያደረገ በየቀኑ ይሠራል፤ እኔም እርሱ የሚያደርገውን ብቻ አደርጋለሁ» አላቸው።

ይህን ሲል እግዚአብሔር በሳምንቱ ቀናት ሁሉ ፀሐዩንና ዝናቡን እንደሚልክ፥ ሣሩና እህሉ አበባውም በሌሎች ቀናት እንደሚያድጉ በሰንበትም እንዲያድጉ እንደሚያደርግ ሊያሳያቸው ፈለገ፤ ደግሞም ለእርሱና ለሰው ሁሉ በሰንበት ቀን መልካም ሥራ መሥራት፥ ሰዎችን መርዳትና ደዌያቸውን መፈወስ ትክክል እንደ ሆነ ሊያስረዳቸው ፈለገ።

ነገር ግን ቃሉ አይሁድን ይበልጥ አስቈጣቸው፤ እግዚአብሔርን አባቱ ብሎ በመጥራቱ (እንደ እነርሱ አባባል) ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎአልና። ቢችሉ ኖሮ ይገድሉት ነበር፤ በእርሱ ላይ የነበራቸው ጥላቻ እንዲህ ታላቅ ነበረ።

ኢየሱስ በዚህ ጕዞ በኢየሩሳሌም ብዙ አልቈየም። ከበዓሉ በኋላ ብዙም ሳይቈይ እንደ ገና በቅፍርናሆም ወዳለው ቤቱ ሄደ።


ቀዳሚ ቀጣይ