የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ቀራጩ እንዴት ደቀ መዝሙር ሆነ

ምዕራፍ 27 · 2 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ቀራጩ እንዴት ደቀ መዝሙር ሆነ

ኢየሱስን ለማየትና ለመስማት ከምድሪቱ ክፍሎች ሁሉ የሚሰበሰቡት ሕዝብ እጅግ ብዙ ስለ ነበሩ በቅፍርናሆም ከተማ ብዙዎቹን ሊያስተናግድ የሚበቃ ስፍራ አልተገኘም። ምኵራቡ እጅግ ትንሽ ነበረ፤ በከተማይቱም ውስጥ ያን ያህል ብዙ ሕዝብ የሚሰበሰብበት ሜዳ አልነበረም። ስለዚህ ኢየሱስ በየቀኑ ከከተማይቱ ወጥቶ ወደ ባሕሩ ዳር ይሄድ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በጴጥሮስ ጀልባ፥ አንዳንድ ጊዜም በዳሩ ላይ ይቀመጥ ነበር፤ ሕዝቡ ሁሉ ደግሞ ሰማያዊው ሰማይ በላያቸው፥ ሰማያዊው ሐይቅም በፊታቸው ሆኖ በሣር በተሸፈነው ኮረብታ ላይ ይቆሙ ነበር፤ ኢየሱስም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይናገርና ሰው ሁሉ ከኃጢአቱ ተመልሶ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረግ ወደ መንግሥቱ እንዴት እንደሚገባ ያሳይ ነበር።

ኢየሱስ በእነዚህ ሕዝብ መካከል ቆሞ ቃሉን ሁሉ በጥንቃቄ የሚያዳምጥ አንድ ሰው አስተዋለ። ይህ ሰው ሌዊ-ማቴዎስ ይባል ነበር። እርሱ «ቀራጭ» የሚባል የመንግሥት ሹም ነበረ፤ ሥራውም የሮም ገዢዎች በሕዝቡ ላይ የጣሉትን ግብር መሰብሰብ ነበር። የምድሪቱ ገዢዎች ለነበሩት ለሮማውያን ሰው ሁሉ ገንዘብ እንዲከፍል ይገደድ ነበር። ሕዝቡ ምድሪቱን በሥልጣናቸው ሥር የያዙትን ሮማውያንን ይጠሉ ነበር፤ እነዚህንም ቀራጮች ይጠሉ ነበር፤ ቀራጮቹ ብዙ ጊዜ ራስ ወዳድና ዓመፀኞች ነበሩና፤ ሕዝቡን ከሚገባው በላይ ያስከፍሉ፥ ድሆችን ይዘርፉና ገንዘቡን ለሮም ግምጃ ቤት ከመክፈል ይልቅ ብዙውን ለራሳቸው ይወስዱ ነበር። ከእነዚህ ቀራጮች ብዙዎቹ ጨካኞችና ራስ ወዳዶች ስለ ነበሩ ሁሉም እንደ ክፉዎች ይቈጠሩ ነበር። «ቀራጮችና ኃጢአተኞች» ይባሉ ነበር፤ ሕዝቡም ይንቋቸው ነበር።

አንድ ቀን ኢየሱስ ሌዊ-ማቴዎስ ከሕዝቡ የግብር ገንዘብ እየተቀበለ በጠረጴዛው ተቀምጦ በነበረበት መቅረጫ በኩል ያልፍ ነበር። ኢየሱስም ቀራጩን ተመልክቶ «ና፥ ተከተለኝ!» አለው። ሌዊ-ማቴዎስም ወዲያው ተነሣ፤ በጠረጴዛው ላይ ያለውን ገንዘብ ጸሐፊዎቹና ረዳቶቹ እንዲጠብቁ ትቶ ኢየሱስን ተከተለ። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቀራጭ መሆኑ ቀረ፤ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆነ፤ በሄደበትም ሁሉ ተከተለው፤ ቃሉንም እየሰማ በአእምሮውና በትዝታው ጠበቀው። ከብዙ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ከሰዎች መካከል ከሄደ በኋላ ማቴዎስ ኢየሱስ የተናገረውንና ያደረገውን የሚተርክ መጽሐፍ ጻፈ። ያ መጽሐፍ የአዲስ ኪዳን የመጀመሪያው መጽሐፍ የማቴዎስ ወንጌል ነው፤ ማቴዎስም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትምህርትና ሥራ ያስታወሰውን ይተርካል። ስለዚህ ቀራጩ ማቴዎስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆኑ ከኢየሱስ ዘመን በኋላ ለኖሩት ሰዎች፥ በዘመናት ሁሉ ያን ወንጌል ላነበቡት ሁሉ፥ ዛሬም በዓለም ሁሉ ለሚያነቡት ሚሊዮኖች መልካም ሆነ። ይህ ሰው በዚያ ቀን የክርስቶስን ጥሪ ፈጥኖ ባይታዘዝ ኖሮ ያ ክቡር መጽሐፍ ፈጽሞ ባልተጻፈ ነበር።

ማቴዎስ ባልንጀሮቹ ቀራጮች ኢየሱስን እንዲያገኙትና ቃሉን እንዲሰሙ ፈለገ። በቤቱ ለኢየሱስ ራት አዘጋጀ፤ በዚያ የአገሩ ክፍል ያሉትን ቀራጮች ሁሉ እንዲመጡ ጠራ። ብዙዎቹም መጡ፤ ከወዳጆቻቸውም ጋር ከኢየሱስ ጋር ለራት ተቀመጡ። የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት ፈሪሳውያን ኢየሱስ ቀራጮቹ ሁሉ ከብበውት በማዕድ ተቀምጦ ሲያዩ በንቀት ተመለከቱ። የኢየሱስንም ደቀ መዛሙርት እንዲህ አሉአቸው፦

«መምህራችሁ ከእነዚያ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ጋር ስለ ምን ይበላል?»

ይህንም ቃል ለኢየሱስ ነገሩት፤ እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰ፦

«ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞችና ብርቱዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም። እኔ የመጣሁት ራሳቸውን እንደ ጻድቃን የሚቈጥሩትን ልጠራ አይደለም፤ ኃጢአተኞች መሆናቸውን አውቀው መዳን የሚፈልጉትን ነው እንጂ። ነገር ግን እነዚያ ፈሪሳውያን እግዚአብሔር ‹በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ከሚያቀርቡት ይልቅ ቸርነትንና ምሕረትን የሚያደርጉትን እወዳለሁ› ያለበትን ቃል ትርጕም ይማሩ።»

ይህም ፈሪሳውያንን ራሳቸውን የሚመለከት ነበር፤ እነርሱ ስለ መጾምና ጸሎት ስለ ማድረስ፥ በቤተ መቅደስም መባ ስለ ማቅረብ ጠንቃቆች ቢሆኑም ብዙ ጊዜ ዓመፀኞችና በድሆች ላይ ጨካኞች ነበሩና።


ቀዳሚ ቀጣይ