የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ለምጻሙና ሽባው ሰው

ምዕራፍ 26 · 4 ደቂቃ ንባብ · 5 ደቂቃ ማዳመጥ

ለምጻሙና ሽባው ሰው

ኢየሱስ ከቅፍርናሆም ከተማ ወጥቶ በገሊላ ባሕር በምዕራብ ዳርቻና በአጠገቡ ባሉ ተራሮች ላይ ያሉትን መንደሮች ሁሉ ጐበኘ። ሥራዎቹን እንዲያዩና ቃሉን እንዲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን ወይም ተከታዮቹን ይዞአቸው ሄደ። በዚህ ጕዞ ብዙ ሕዝብ ሊሰሙት መጡ፤ በየስፍራውም ልዩ ልዩ በሽታን ሁሉ ፈወሰ፤ ሰዎችን ይገዙ የነበሩትንም ርኵሳን መናፍስት አወጣ።

በአንድ ስፍራ ለምጽ በሚባል አስከፊ በሽታ ሰውነቱ ሁሉ የተሸፈነ፥ «ለምጻም» የሚባል ሰው ወደ ኢየሱስ መጣ። መንካት በሽታውን ያመጣል ብለው ይፈሩ ስለ ነበረ ለምጻምን ማንም አይነካውም፥ ወደ እርሱም እንኳ አይቀርብም ነበር። ለምጻም ከቤቱ ተባርሮ ከከተማው ውጭ ባለ ሰፈር ከሌሎች ለምጻሞች ጋር ይኖር ነበር። ማንም ሲቀርብ ባየ ጊዜ በሩቅ መቆም፥ እስትንፋሱ ማንንም እንዳይደርስ አፉን በልብሱ መሸፈን፥ ማንም በሽታውን እንዳይይዝም «ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!» ብሎ መጮኽ ነበረበት። ኢየሱስ በሚሰብክበት ጊዜ በምድሪቱ ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፤ ዛሬም በዚያች አገር ለምጻሞች ይታያሉ።

ኢየሱስን ያየው ይህ ለምጻም የደፈረውን ያህል ወደ እርሱ ቀረበ። በኢየሱስ ፊት ተንበረከከ፤ ራሱንም መሬት አስነክቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦

«ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ለምጼን ልታርቅልኝና ሥጋዬን ልታነጻ ትችላለህ።»

ኢየሱስ ለምጻሙን ለመንካት አልፈራም። ወደ እርሱ ሄዶ እጁን በላዩ ጫነ። ከዚያም እንዲህ አለ፦

«እወድዳለሁ፤ ንጻ!»

ወዲያውም የዚህ ሰው ለምጽ ሁሉ ለቀቀው። ቈዳው የሰምና የሞት የሚመስል ንጣቱን ተወ፤ ዓይኖቹ በሩ፤ የተበላሹ እጆቹ ፍጹም ሆኑ፤ ድምፁም ከእንግዲህ ባዶና የተሰነጠቀ አልነበረም። ከእንግዲህ ለምጻም አልነበረም፤ ፍጹም ጤነኛ ሰው ሆነ እንጂ።

ኢየሱስም «ስለ መዳንህ ለማንም አትንገር፤ ነገር ግን በቤተ መቅደስ ወዳለው ካህን ሄደህ እንደ ነጻህ አሳየው፤ ለእግዚአብሔርም የምስጋና መሥዋዕት አቅርብ። ጤነኛ መሆንህን የሚያሳይ ጽሕፈት ካህኑ ይስጥህ፤ ከዚያም ወደ ቤትህ ሂድ» አለው።

ኢየሱስ ይህ ሰው ስለ መዳኑ ለብዙ ሰዎች ቢናገር ልዩ ልዩ በሽታ ያለባቸው ሊፈወሱ የሚፈልጉ ሕዝብ በብዛት ስለሚመጡ ወንጌልን ለመስበክ ጊዜም ዕድልም እንደማያገኝ ያውቅ ነበር፤ ታላቁ ዓላማውም በሽታን መፈወስ ሳይሆን ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚወስደውን መንገድ ማስተማር ነበር። ከበሽታ ከመፈወስ ይልቅ ከኃጢአት መዳን ይሻላል።

ይህ ሰው ግን በመዳኑ እጅግ ደስ ስላለው ዝም ማለት አልቻለም። በሄደበት ሁሉ ስለ ድንቅ መዳኑ ለሰዎች ተናገረ፤ በሕዝቡም መካከል ኢየሱስን የማየት ታላቅ ፍላጎት አስነሣ፤ ስለዚህ ሕዝቡ እጅግ ስለ በዙ ኢየሱስ ከእንግዲህ መስበክ አልቻለም፤ ወደ ከተሞችም መሄድ አልቻለም። ሁሉም ከአንዳች ሕመም ለመፈወስ ወይም ኢየሱስ ሌሎችን ሲፈውስ ለማየት ይጓጓ ነበር። ኢየሱስ ጥቂት ሰዎች ወደሚኖሩበት ገጠር ለመሄድ ተገደደ፤ በዚያም እንኳ ሕዝቡ ከብዙ ስፍራ እየመጡ ፈለጉት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ አሁን መኖሪያው ወደ ሆነችው ወደ ቅፍርናሆም እንደ ገና መጣ። ሕዝቡም መመለሱን እንደ ሰሙ ሊያዩት፥ ሊሰሙትና ከበሽታቸው ሊፈወሱ በብዙ ሆነው ተሰበሰቡ። ክፍሎቹ ሁሉ በሰዎች በተሞሉበት በአንድ ቤት በረንዳ ላይ ቆመ፤ በፊቱም የቤቱን አደባባይ እስከ መጨረሻው ማዕዘን ድረስ የሞሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። በዚህ ሕዝብ መካከል በኢየሱስ ለማመን የተዘጋጁ አንዳንዶች ነበሩ፤ ነገር ግን ኢየሱስ ማን እንደ ሆነ፥ ምን እንደሚያስተምርና ምን እንደሚሠራ ለማየት ከይሁዳ የመጡ አንዳንድ ሰዎችም ነበሩ። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ አላመኑም፤ በእርሱ ላይ አንዳች ስሕተት ለማግኘት ግን በዚያ ነበሩ። የአይሁድን ሕግ ሥርዓቶች ሁሉ በጥንቃቄ ስለሚጠብቁ ከሌሎች እንበልጣለን የሚሉ «ፈሪሳውያን» የሚባሉ ወገን ነበሩ፤ በልባቸው ግን ከበጎነት የራቁ ነበሩ፤ ኢየሱስንም እጅግ ይቃወሙት ነበር።

ኢየሱስ ሲናገር ሳለ አራት ሰዎች ሽባ የሆነን ሰው በአልጋ ተሸክመው መጡ፤ ሽባ ሰውን ረዳት የሌለው የሚያደርግ፥ እጁን መጠቀም፥ መራመድም ሆነ ብቻውን መቆም የማያስችል በሽታ ነው። ይህን ሰው እንዲፈወስ ወደ ኢየሱስ ለማምጣት እጅግ ጓጉተው ነበር፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ ቤቱ፥ በፊቱ ወዳለውም ግቢ እንኳ መግባት አልቻሉም። ቢሆንም ይህን ሽባ ሰው በሆነ መንገድ ወደ ኢየሱስ ለማድረስ ቈርጠው ነበር። ወደ ቤቱ ጣራ ወጡ፤ ሕመምተኛውንም ወደ ላይ ሳቡት። ከዚያም በታች ባሉት ሰዎች ራስ ላይ ስለሚወድቀው አቧራና ቆሻሻ ግድ ሳይሰጣቸው ጣራውን ነደሉ። በቂ ቀዳዳ ባበጁ ጊዜ በብርድ ልብስ ተጠቅልሎ በፍራሽ ላይ የተኛውን ሰው በኢየሱስ ፊት ለፊት አወረዱት። ይህ ሁሉ በኢየሱስ ያላቸውን እምነት አሳየ። ሽባውን ሊፈውሰው እንደሚችል አመኑ፤ ወደ መድኃኒቱም ፊት ለማቅረብ ማንኛውንም ድካም ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ።

ኢየሱስም ሰውየውን ተመልክቶ እንዲህ አለው፦

«አንተ ልጅ፥ አይዞህ፤ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ!»

ከእነዚህ ፈሪሳውያን፥ ከኢየሱስ ጠላቶች፥ አንዳንዶቹ በአጠገቡ ተቀምጠው ነበር፤ እነዚህንም ቃላት በሰሙ ጊዜ ጮኸው ባይናገሩትም በልባቸው እንዲህ አሰቡ፦

«ይህ ምንኛ ክፉ ቃል ነው! ይህ ሰው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ይናገራል! ኃጢአትን ለማስተሰረይ ማንም ሰው መብት የለውም፤ ይህ የእግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህ ሰው የእግዚአብሔር ኃይል እንዳለው ማስመሰሉ እንዴት ያለ ክፋት ነው!»

ኢየሱስ ወደ ልባቸው ማየት ይችል ስለ ነበረ አሳባቸውን አወቀ። እንዲህም አላቸው፦

«ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ‹ኃጢአትህ ተሰረየችልህ› ከማለት ወይስ ‹ተነሥተህ ሂድ› ከማለት ማናቸው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ ሆኜ በምድር ሳለሁ ኃጢአትን የማስወገድ ኃይል እግዚአብሔር እንደ ሰጠኝ አሳያችኋለሁ።»

ከዚያም በአልጋው ላይ ወደ ተኛው ሽባ ዘወር ብሎ በሥልጣን ድምፅ እንዲህ አለው፦

«እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ!»

በቅጽበት ለሽባው አዲስ ሕይወት መጣለት። በሙሉ ብርታት በእግሩ ቆመ፤ ብርድ ልብሱን ጠቀለለ፤ ተኝቶበት የነበረውን ፍራሽ አንሥቶ በትከሻው ተሸከመ፤ መንገድ ለመስጠት በተከፈተለት ሕዝብ መካከልም አልፎ ወጣ። ሰውየውም ስለ መዳኑ እግዚአብሔርን እያመሰገነ በመንገዶች አልፎ ወደ ቤቱ ሄደ።

ኢየሱስ በዚህ የፈውስ ሥራ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር የማለት መብት ያለው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አሳየ። የኢየሱስ ጠላቶች እነዚህ ፈሪሳውያን የሚሉት ነገር አላገኙም፤ ሕዝቡ በኢየሱስ እንዳመኑ ስላዩ ግን በልባቸው ከቀድሞው ይበልጥ ጠሉት። ይህን ፈውስ ያዩትን ሰዎች አእምሮ መደነቅ ሞላው፤ የእስራኤልን አምላክ አመሰገኑ፤ እርስ በርሳቸውም «ዛሬ ድንቅ ነገር አየን!» ተባባሉ።


ቀዳሚ ቀጣይ