የሀርልበት የክርስቶስ ሕይወት ለወጣቶችና ለአዋቂዎች
ኢየሱስ በምኵራብ፥ በቤትና በጎዳና

ምዕራፍ 25 · 3 ደቂቃ ንባብ · 3 ደቂቃ ማዳመጥ

ኢየሱስ በምኵራብ፥ በቤትና በጎዳና

የታላቁ የዓሣ ማጥመድ ወሬ በየቦታው ተነገረ፤ ብዙ ሰዎች ጀልባዎቹ በዓሣ ተሞልተው ወደ ዳር ሲመጡ አይተው ነበርና፤ ከእነዚያም ዓሣዎች ቁርስ የበሉ ሁሉ ስለ ድንቁ ነገር እንደ ተናገሩ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በከፊል በዚህ ወሬ ምክንያት የሰንበት ቀን በደረሰ ጊዜ ይህን አዲስ ረቢ ለማየትና ለመስማት የቅፍርናሆም ምኵራብ በሕዝብ ተጨናነቀ። «ረቢ» አይሁድ በምኵራቦቻቸው ሕጉን ለሚያስተምሩ ሰዎች የሚሰጡት ስም ነበር። ኢየሱስ ያን ማዕረግ የሚያሰጠውን ትምህርት በኢየሩሳሌም ፈጽሞ ባይማርም ሕዝቡ በአብዛኛው «ረቢ» ብለው ይጠሩት ነበር። ሕዝቡ የኢየሱስን ቃል በመደነቅ አዳመጡ፤ ትምህርቱ ሕጉን ከሚያስተምሩት ከጻፎች ትምህርት እጅግ የተለየ ነበርና። እርሱ ስለ ታላላቅ ነገሮች ተናገረ፤ እግዚአብሔር በቅርቡ ስለሚያቆመው መንግሥትና ሕዝቡ ለመምጣቱ እንዴት መዘጋጀት እንዳለባቸው አስተማረ። ደግሞም እንደ ሁሉ ጌታ በሥልጣን ተናገረ፤ አድማጮቹም እነዚህ ቃላት ከእግዚአብሔር የተላከ ሰው ቃላት እንደ ሆኑ ተሰማቸው።

ኢየሱስ በምኵራቡ ሲናገር ሳለ ገብቶ የነበረ አንድ ቍጡ ሰው በታላቅ ጩኸት አገልግሎቱን አቋረጠው። ይህ ሰው ከማንኛውም በሽታ የከፋ በሆነ ክፉ ነገር ይሠቃይ ነበር። በሆነ መንገድ ርኵስ መንፈስ፥ ጋኔን፥ ወደ ሰውነቱ ገብቶ ነበር። ይህ ጋኔን ሰውየውን ይቈጣጠረውና ወደ እብድ ሥራና ንግግር ይነዳው ነበር። በዚህ ሰው አንደበት የሚነገሩት ቃላት የራሱ አልነበሩም፤ በውስጡ ያለው የክፉው መንፈስ ቃላት ነበሩ እንጂ። መንፈሱም በሰውየው ድምፅ ተጠቅሞ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦

«አንተ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ተወን! ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ነህ!»

ኢየሱስ ግን ወዲያው በሰውየው ውስጥ ያለውን ክፉ መንፈስ «ዝም በል፥ ከእርሱም ውጣ!» አለው።

በዚህ ቃል ጋኔኑ ሊገድለው እንደሚፈልግ ሰውየውን በወለሉ ላይ ጣለው፤ ከዚያም ከሞት አፋፍ ላይ ትቶት ድንገት ከሰውየው ወጣ። ቀድሞ እጅግ አስፈሪ ስለ ነበረ ሁሉ ይፈሩት የነበረው ሰው አሁን ፍጹም ጤነኛ እንደ ሆነና ከክፉው መንፈስ ፈጽሞ ነጻ እንደ ወጣ ብዙም ሳይቆዩ አዩ።

በዚያን ጊዜ ሁሉም ተገረሙ፤ ተደነቁም። እርስ በርሳቸውም እንዲህ እያሉ ተነጋገሩ፦

«ይህ ሁሉ ምንድር ነው? ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? እነሆ፥ ይህ ሰው ርኵሳን መናፍስትን በሥልጣን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታል፥ ይወጡማል።»

ሕዝቡ ከምኵራቡ ሲወጡ ስለዚህ የኢየሱስ ታላቅ ሥራ ላገኙት ሰው ሁሉ ነገሩ። እነዚህም ወንዶችና ሴቶች ለሌሎች ነገሩ፤ ብዙም ሳይቆይ የኢየሱስ ኃይል ወሬ በዚያ የምድሪቱ ክፍል ባሉ ከተሞችና መንደሮች ሁሉ ተዳረሰ።

በምኵራብ የነበረው አገልግሎት ካለቀ በኋላ ኢየሱስ ምሳ ሊበላ ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ሄደ፤ ሁለቱ ወንድማማቾች ያዕቆብና ዮሐንስም አብረውት ሄዱ። በቤትም የስምዖን አማት፥ የሚስቱ እናት፥ በብርቱ ትኩሳት ታማ እንደ ተኛች ነገሩት። እርሱም መጥቶ በአልጋዋ አጠገብ ቆመ፤ ወደ እርስዋም ጐንበስ ብሎ ሊያስነሣት እንደሚፈልግ እጅዋን ያዘ። በዳሰሳትም ጊዜ በሰውነትዋ ውስጥ አዲስ ኃይል ሲገባ ተሰማት። ወዲያውም ትኩሳቱ ለቀቃት፤ ፍጹም ድና ከአልጋዋ ተነሣች፤ ምሳውንም ለማዘጋጀትና ለማቅረብ አገለገለች።

ኢየሱስ በዚያ ከሰዓት በኋላ በስምዖን ቤት ቆየ። ፀሐይ ገብታ ሰንበት ባለቀ ጊዜ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለው መንገድ በሕዝብ ተሞልቶ አገኙት። ከከተማይቱ ክፍሎች ሁሉ የታመሙትን ወይም ኢየሱስ በምኵራብ እንደ ፈወሰው ሰው ርኵሳን መናፍስት ያደሩባቸውን አምጥተው ነበር። ከቤቱም በወጣ ጊዜ በእነዚህ ሕመምተኞች ላይ አንድ በአንድ እጁን ጫነባቸው፤ እንደ ዳሰሳቸውም ድነው ይነሡ ነበር። በአንዳንዶቹ ሰዎች ውስጥ ያሉ ርኵሳን መናፍስት ሊናገሩት ሞከሩ። እርሱ ግን አልፈቀደላቸውም፤ ካደሩባቸው ሰዎች ወዲያው እንዲወጡ አዘዛቸው። ኢየሱስን ለመታዘዝ እምቢ ማለት አልደፈሩም፤ ወጥተውም ሄዱ።

በዚያች ሌሊት ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ኢየሱስ ገና ጨለማ ሳለ ከንጋት በፊት ብዙ ቀድሞ ተነሣ፤ ከከተማይቱም ወጣ። ቤቶችም ሰዎችም በአጠገቡ የሌሉበት ጸጥ ያለ ስፍራ አገኘ፤ በዚያም ለብዙ ሰዓታት ወደ አባቱ ጸለየ። በማለዳም እንደ ሌለ ታወቀ፤ ስምዖን ጴጥሮስና ሌሎቹም ሊፈልጉት ወጡ። ባገኙትም ጊዜ «መምህር ሆይ፥ ሰው ሁሉ ይፈልግሃልና ወደ ከተማይቱ ተመለስ!» አሉት።

ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ «የተላክሁት ወደ ከተማችሁ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ስፍራዎችም ጭምር ነው። በቅርብ ወዳሉት ከተሞች ወጥተን እንጐብኛቸው። ከአባቴ የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች በየስፍራው እንድሰብክ ነው።»


ቀዳሚ ቀጣይ